ኪንና ባህል ሠዓሊ የመቶ አለቃ ኤልያስ ደስታ (1939-2016)

ሔኖክ ያሬድ

ቀን: June 2, 2024

በኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ታሪክ በተለይ በዘመነ አብዮት ውስጥ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ በሠዓሊነትም በወታደራዊ መኰንንነትም የሚታወቁ ናቸው፣ ሠዓሊ የመቶ አለቃ ኤልያስ ደስታ፡፡

ሠዓሊ የመቶ አለቃ ኤልያስ ደስታ (1939-2016) | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ነፍስ ኄር ሠዓሊ ኤልያስ ደስታ

‹‹ጥበበኛ በጥበብ እግር ይመላለሳል›› እንዲሉ ከስድስት አሠርታት በላይ በሥነ ጥበቡ ዓለም ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት እስከ ኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት፣ ከኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እስከ አሁን ዘመን ድረስ ከጥበብ ሥጋዊ፣ እስከ ጥበብ መንፈሳዊ የሥዕል ዓለም ሲመላለሱ ኖረዋል፡፡

ከአባታቸው ከደጃዝማች ደስታ ገብሩ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ በላይነሽ አሰን ዓርብ የካቲት 7 ቀን 1939 ዓ.ም.፣ በቀድሞ አጠራሩ በወሎ ጠቅላይ ግዛት ደሴ ከተማ የተወለዱት የመቶ አለቃ ኤልያስ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በደሴ እቴጌ መነን፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በወ/ሮ ስሂን ትምህርት ቤቶች አጠናቀዋል፡፡

በ1958 ዓ.ም. በደሴ ከተማ በሚገኘው የፖሊስ ሠራዊት መምሪያ ተመልምለው ሥልጠና በመውሰድ ለሁለት ዓመት እያገለገሉ ሳለ፣ ባላቸው የሥዕል ተሰጥዖ ተመርጠው በአዲስ አበባ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ለአምስት ዓመት ተምረው በ1965 ዓ.ም. በዲፕሎማ በክብር ተመርቀዋል፡፡

የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት እስከ አበቃበት ዓመት (1967) ድረስ በፖሊስ ሠራዊቱ ውስጥ በሥዕል ሙያቸው ያገለገሉት የመቶ አለቃ ኤልያስ፣ ከመንግሥት ለውጥ በኋላ በምድር ጦር በፖለቲካው ዘርፍ በትምህርትና ቅስቀሳ ክፍል ውስጥ ሆነው ኅብረተሰቡን መግለጽ የሚችሉ፣ የኢትዮጵያ አብዮት ጉዞን የሚያሳዩ ሥዕሎችንና ፖስተሮችን ያዘጋጁ ነበር፡፡

ቅድመ አብዮት በመማሪያ ደብተሮች ሽፋን ይታዩ የነበሩት የንጉሣዊ ቤተሰብ ምስሎች/ ፎቶዎች በአብዮቱ ዘመን እንዲቀሩ ሲደረግ፣ በምትካቸው የሠራተኛው መደብን የሚወክሉ ሥዕሎች እንዲሠሩ ነው የተወሰነው፡፡

በ1960ዎቹና በ70ዎቹ አልፎም፣ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃም ሆነ ከዚያም አልፎ ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች የመማሪያ ደብተሮቻቸው ሽፋን ላይ የሚታዩ የሠርቶ አደሮችም ይሁን አርሶ አደሮች ሥዕል ይሥሉ ከነበሩት ቀደምት ሠዓሊያን ኤልያስ አንዱ ነበሩ፡፡

በአንዱ የደብተር የፊት ገጽ ላይ የሚገኘው ሥዕላቸው ታጋይ ሴቶች ተሰልፈው የሚታዩበት ሲሆን፣ የያዙት መፈክርም ‹‹አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመመሥረት እንንቃ እንደራጅ እንታጠቅ›› የሚል ነበር፡፡

4ኛው የኢትዮጵያ አብዮት በዓል በ1971 ዓ.ም. መስከረም 2 ቀን መከበሩን ተከትሎ የተዘጋጀውና በርዕሰ ብሔሩ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለ ማርያምና በኩባ ፕሬዚዳንት ፊደል ካስትሮ ሩዝ የተከፈተው ‹‹ትግልና ድል›› የተሰኘው ዓውደ ርዕይ፣ ከስድስት ኪሎ በላይ በሚገኘው የትምህርት መሣሪያዎች ድርጅት አዳራሽ ሲዘጋጅ ሥዕሎቻቸው ከቀረቡላቸው አንዱ ሠዓሊ ኤልያስ ነበሩ፡፡

የ10ኛው የአብዮት በዓል በ1977 ሲከበርም የአሥሩን ዓመታት የትግልና የድል ውጤቶች የሚያሳየውና በአብዮት በዓሉ ላይ በተገኙት የአፍሪካና የሶሻሊስት አገሮች ፕሬዚዳንቶች የተጎበኘው ዓውደ ርዕይ፣ በያኔው አብዮት አደባባይ አጠገብ ‹‹አብዮት ቅስት››ን አልፎ በሚገኘው ‹‹ድላችን ኤክስፖ›› (አሁን ኤግዚቢሽን ማዕከል) እንዲሁ ሥራዎቻቸው ለዕይታ በቅቶላቸዋል፡፡

በየዘመኑ ከሣሏቸው ጥበባዊ ሥራዎቻቸው መካከል የዓድዋን ጦርነትና ድል የሚያሳይ፣ የአብዮታዊ ኢትዮጵያ የትግል ጉዞ፣ እንዲሁም የሊቀመንበሩ ምስል ይገኙባቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) መንግሥት በ1983 ወርኃ ግንቦት ሲያከትም ከሠራዊቱ በጡረታ የተገለሉት ሠዓሊ ኤልያስ፣ ሥነ ጥበባዊ ሥራዎቻቸውን ከመሥራት አልተቆጠቡም፡፡ ትኩረታቸውን በአመዛኙ ወደ መንፈሳዊና ክርስቲያናዊ ሥዕሎች አድርገዋል፡፡

ለኢትዮጵያ ጥንታዊነት በአብነት ከሚቆሙት ቅርስና ውርሶች አንዱ፣ ትውፊታዊው ሥነ ሥዕል ነው፡፡ የሥዕል ጥበቡ በአመዛኙ ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሚቀዳ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ትውፊታዊ ሥዕል ከዘመናዊው ሥዕል አስተምህሮ ጋር አብሮ እንዲሄድ ካደረጉት መካከል ሠዓሊ ኤልያስ ደስታ ይገኙበታል፡፡

በተለይ የሰበካ ጉባዔ አባል በሆኑበት በአጥቢያቸው በደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ዓውደ ምሕረት ዘወትር የሚታይ ሥዕለ አድኅኖ በመሣል ምዕመናን እንዲገለገሉበት አድርገዋል፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች አብያተ ክርስቲያናት ሲታነፁ በማስተባበርና አብሮ በመሥራት ለውጤት ካበቋቸው መካከል የየረር በአታ ለማርያምና የገፈርሳ ቅዱስ ሚካኤል ይገኙበታል፡፡

በቀበሌያቸው በሚገኘው አንጋፋው የኅብረት በአንድነት ዕድር ዋና ዳኛ በመሆንም አገልግሎታቸውን ከላቀ አፈጻጸም ጋር መከወናቸው ማሳያው፣ በተደጋጋሚ መመረጣቸውና በኅብረተሰቡ ይበልታን ማግኘታቸው ነው፡፡

በገጸ ታሪካቸው እንደተመለከተው፣ በ1960ዎቹ መጨረሻና ተከስቶ በነበረ ችግር ወጣቶችን ራሳቸውን እንዲጠብቁ፣ ለወላጆቻቸው ታዛዥ እንዲሆኑ ከመምከር ባለፈ፣ ከመከራ ላይ ወድቀው የነበሩትን በመታደግ ያሳዩት ቁርጠኝነት በማኅበረሰቡ ዘንድ ዘለቄታዊ ከበሬታን አስገኝቶላቸዋል፡፡

ከቅርብ ዓመት ወዲህ ጤናቸው የታወከው ሠዓሊ የመቶ አለቃ ኤልያስ ደስታ፣ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት እሑድ ግንቦት 18 ቀን 2016 ዓ.ም. በ77 ዓመታቸው አርፈው፣ ሥርዓተ ቀብራቸው ግንቦት 19 ቀን በደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡

ሥነ ጥበበኛው፣ በጥበብ ሠረገላ ሲመላለሱ የኖሩት፣ ሠዓሊ ኤልያስ ደስታ ባለትዳር፣ የ10 ልጆች አባትና የስድስት የልጅ ልጆች አያት ነበሩ፡፡