የማዕድን ሚኒስትሩ ሀብታሙ ተገኝ (ኢንጂነር)

ዜና ጥናት ሳይደረግ የተገነባው የያዩ ማዳበሪያ ፕሮጀክት የአገር ሀብት እንደባከነበት ተገለጸ

ፅዮን ታደሰ

ቀን: June 2, 2024

በኦሮሚያ ክልል ኢሉባቦር ዞን ውስጥ ተገንብቶ የነበረው ያዩ የማዳበሪያ ፕሮጀክት ለፋብሪካው የሚሆን በቂ ሀብት መኖሩ ጥናት ሳይደረግበት ግንባታው በመጀመሩ፣ የአገር ሀብት እንደባከነበት ተገለጸ፡፡

 የማዕድን ሚኒስቴር የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ግንቦት 22 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርብ፣ በቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚገባውን የማዳበሪያ ምርት በአገር ውስጥ ለመተካት ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ 

ከዚህ ቀደም በኦሮሚያ ክልል ኢሉባቦር ዞን ውስጥ ተገንብቶ የነበረው ያዩ የማዳበሪያ ማምረቻ ፋብሪካ ግንባታ ሲጀመር፣ በርካታ አርሶ አደሮች መፈናቀላቸውን በመግለጽ፣ ፋብሪካው ያልተጠናቀቀበትና ወደ ማምረት ያልገባበት ምክንያት ምን እንደሆነ የምክር ቤት አባሉ አቶ ጅሃድ ናስር ጠይቀዋል፡፡ 

‹‹ማዳበሪያ የማናመርተው ለማዳበሪያ ማምረቻ የሚሆን ግብዓት በበቂ ሁኔታ ስለሌለን ጭምር እንጂ የአቅም ማነስ ብቻ አይደለም፤›› ያሉት የማዕድን ሚኒስትሩ ሀብታሙ ተገኝ (ኢንጂነር)፣ በያዩ ፕሮጀክት የተሞከረውም ትክክለኛ ባልሆነና በሌለ ግብዓት በመሆኑ፣ የአገር ሀብትም ሆነ ፋብሪካው ባክኖ እንዲቀር ተደርጓል ብለዋል፡፡

‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህዳሴ ግድቡን ጨምሮ በርካታ የቆሙ ፕሮጀክቶችን ጨርሰዋል፡፡ ነገር ግን የያዩ ፕሮጀክት ሁኔታ እንደዚህ አይደለም፣ ፋብሪካው የተገነባበት መንገድ ልክ አይደለም፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ በስህተት የተገነባና የአገር ብክነት የሆነ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ጥያቄውን ያቀረቡት የምክር ቤት አባል በፕሮጀክቱ ዙሪያ በቢሯቸው በመገኘት ዝርዝር መረጃዎችን መመልከት እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

ሚኒስትሩ በኢሉባቡር ዞን ሌሎች ጥናቶች እየተካሄዱ መሆናቸውን በመግለጽ፣ የያዩ ማዳበሪያ ፕሮጀክት የሚሠራ መሆኑ ቢረጋገጥ ከሚያስገኘው የአገር ጥቅም አንፃር ሊተው የማይችል እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል በክልሎች ያለው የማዕድን አውጭ ኩባንያዎች የፈቃድ አሰጣጥና ቁጥጥር ክፍተት ያለበት እንደሆነ የገለጹት ሀብታሙ (ኢንጂነር)፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ክልሎች ለ378 የድንጋይ ከሰል አምራቾች ፈቃድ ቢሰጡም፣ ከእነዚህ ውስጥ 40 ባለፈቃዶች ብቻ ወደ ሥራ እንደገቡ አስታውቀዋል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ የሚሰጡ ፈቃዶች ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ እንዲገቡ በአግባቡ ማስተዳደር ላይ በክልሎች በኩል ክፍተቶች በመኖራቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ 

የወርቅ ምርትን አስመልክቶ በባህላዊ ላይ ጥገኛ መሆኑ አገሪቱን ዋጋ እያስከፈላት መሆኑን፣ በኩባንያ ደረጃ በወርቅ ማዕድን ላይ የተሰማሩ ሚድሮክ ጎልድና  ኢዛና ማይኒንግ የተሰኙ ኩባንያዎች ብቻ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን ኢዛና የተሰኘው ኩባንያ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ጉዳት ደርሶበት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት 3.023 ቶን ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ መቅረቡንና 274 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ መገኘቱን አክለዋል፡፡

ለወርቅ ምርት አፈጻጸም ዝቅ ማለት የኮንትሮባንድ ንግድ፣ ሕገወጥ ግብይትና የፀጥታ ችግሮች በምክንያትነት ቀርበዋል፡፡ በተጨማሪም በ2016 ዓ.ም. ወደ ምርት ይገባሉ የተባሉ ኩባንያዎች ከሚድሮክ ውጪ በራሳቸው፣ እንዲሁም በፀጥታ ችግሮች ምክንያት ወደ ሥራ አለመግባታቸው በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡ በዘርፉ ያሉትን ችግሮች ለመፍታትም ሚኒስቴሩ የአሥር ዓመት የባህላዊና የአነስተኛ ወርቅ ምርት የሚመራበት ስትራቴጂካዊ ሰነድ ማዘጋጀቱ ተጠቁሟል፡፡ 

ከዚህ ጋር በተያያዘ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን የብረት ምርት በአገር ውስጥ ለመተካት ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተከናወኑ ተግባራት በኢንዱስትሪዎች 250 ሺሕ ቶን ብረት ማምረት ቢቻልም፣ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ29 በመቶ ዝቅ ማለቱ ተገልጿል፡፡ ለአፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆንም የግብዓት እጥረት እንደሆነ በሪፖርቱ የተገለጸ ሲሆን፣ በአማራ ክልል ሰቆጣ አካባቢ ለሚገኘው የብረት ክምችት ሥራ 600 ሜትር የኮር ድሪሊንግ ሥራ ለማከናወን ታቅዶ፣ በፀጥታ ችግር ምክንያት ሥራው መዘግየቱ ተነግሯል፡፡ 

ከዚህ ቀደም ጉዳት እንዳያስከትሉ መወገድ አለባቸው የሚል ጥያቄ ሲቀርብባቸው የነበሩ የአገልግሎት ዘመናቸው ያለፈባቸው ከ3,000 ሊትር በላይ ፈሳሽና ከ8,600 በላይ ጠጣር ኬሚካሎች እንዲወገዱ መደረጉ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

ማዕድን ባለባቸው አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶች ለማዕድን ሥራ እንቅፋት እንደሆኑና ይህንን ችግር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ለመፍታት ሚኒስቴሩ ምን እየሠራ እንደሚገኝ፣ የወርቅ ምርት ባለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ አለመሆን ለሕገወጥ ንግድ መበራከት ምክንያት በመሆኑ ሚኒስቴሩ ችግሩን ለመፍታት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ያከናወናቸውን ተግባራት በተመለከተ በምክር ቤት አባሉ አቶ ሳዲቅ አደም ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡ ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡት የማዕድን ሚኒስትሩ፣ ማዕድናት በሚገኙባቸው አካባቢዎች ያለው የፀጥታ ችግር ለማዕድን ማውጣት ሥራው ፈተና መሆኑን ገልጸው፣ በእነዚህ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ተዋጊዎችን ማስለቀቅም ቀላል ሥራ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም የማዕድን ማውጣት ሥራ በሚከናወንባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ ላይ ሚኒስቴሩ ትኩረት አድርጎ እየሠራ እንደሚገኝ፣ ይህንንም ለማጠናከር ፕሮጀክቶቹ ባሉባቸው አካባቢዎች የሚቋቋም የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በ2017 ዓ.ም. ወደ ተግባር እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

የኢንዱስትሪና የማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አማረች ባካሎ (ዶ/ር)፣ የማዕድን ማውጣት ሥራው በትክክለኛው መንገድ ተግባራዊ የሚደረግና ለሕዝብ ጥቅም የሚውል መሆኑን ማረጋገጥ ላይ፣ ሚኒስቴሩ ትኩረት አድርጎ መሥራት እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡

አክለውም ተከማችተው የሚገኙ የከሰል ድንጋይ ምርቶች እያሉ ከውጭ እንዲገቡ የሚደረገው አሠራር ሊለወጥ ይገባል ብለዋል፡፡