

ማኅበራዊ ወላጆች ከጤና ተቋም ውጪ የሚወለዱ ሕፃናትን ለሲቪል ምዝገባ እንዲያሳውቁ የሚያስገድድ ረቂቅ ሕግ…
ቀን: June 2, 2024
- ተፈናቃዮች የሚመዘገቡበት ሥርዓት ተደንግጓል
ከጤና ተቋም ውጪ የሚወለዱ ሕፃናትን ወላጆች ለሲቪል ምዝገባ ጽሕፈት ቤት እንዲያስታውቁ የሚያስገድድ ሕግ ለፓርላማ ቀረበ፡፡ በዝቅተኛው እርከን ላይ ያለው የመዋቅር ወይም የጤና ባለሙያ አግባብ ያላቸውን መረጃዎች የያዘ ቅጽ ሞልቶ፣ ውልደቱ የተከሰተበት ቦታ ለሚገኝ የሲቪል ምዝገባ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ወላጆች እንዲያሳውቁ ሕጉ ያስገድዳል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐሙስ ግንቦት 22 ቀን 2016 ዓ.ም. ባካሄደው 29ኛ መደበኛ ስብሰባው በሥራ ላይ ካለው የሲቪልና የቤተሰብ ምዝገባና ብሔራዊ መታወቂያ አዋጅ ቁጥር 760/2004 አዋጅ ራሱን ችሎ በተዘጋጀው የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት አድርጓል፡፡
ረቂቅ አዋጁ በርካታ ማሻሻያዎች ተደርገውበታል፡፡ ለአብነትም በሥራ ላይ ባለው አዋጅ የሲቪል ምዝገባ ቦታ በመደበኛ መኖሪያ ቦታ የሚለውን አሁን ሁነቱ በተከሰበት ቦታ እንዲሆን የቀረበ ሲሆን፣ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሲቪል ምዝገባን እንዲያደርጉ ይፈቅዳል፡፡
በረቂቁ አዋጅ አስመዝጋቢው አካል ለዘገየበት በቂ ምክንያት በማስረጃ አስደግፎ ካላቀረበ በስተቀር፣ ልደትን በ90 ቀናት ሞትን በ50 ቀናት ውስጥ ማስመዝገብ እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ሳያስመዘግቡ መቆየት የተከለከለ እንደሆነ በረቂቁ ተብራርቷል፡፡
በረቂቁ አዋጁ እንደተብራራው ከዚህ ቀደም በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ‹‹ተጥሎ የተገኘ ሕፃን›› የሚለው አገላለጽ በማሻሻያው፣ ‹‹ወላጆቹ የማይታወቁ ሕፃን›› በሚል ተሻሽሎ ቀርቧል፡፡
በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ልደትን የማስመዝገብ ግዴታ ለወላጆች የጣለ ሲሆን፣ በተሻሻለው ረቂቅ ወላጆቹ የሌሉ ከሆነ ደግሞ አሳዳሪ ወይም ሞግዚት ልደቱን ያስመዘግባሉ፡፡
የልደትና የሞት ምዝገባ ከዚህ ቀደም እንደነበረው በመደበኛ መኖሪያ ቦታ ሳይሆን፣ ልደቱ በተከሰተበት ቦታ የሚገኝ የሲቪል ምዝገባ ጽሕፈት ቤት እንዲካሄድ በረቂቁ ተደንግጓል፡፡
ሞትን የማስመዝገብ ግዴታ በተመለከተ ከሟች ጋር አብሮ ይኖር የነበረ ሰው ማስመዘገብ እንዳለበት ግዴታ ይጥላል፡፡
በረቂቁ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሚያስተዳድረውን ቤተሰብ በአገልግሎቱ በተዘጋጀው የቴክኖሎጂ መተግበሪያ ሥርዓት ላይ ማስመዝገብ እንዳለበት ግዴታ እንደሚጣልበት ተደንግጓል፡፡
ስደተኞችን በተመለከተ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ስደተኞችን ለመመዝገብ እንደ ሲቪል ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን፣ የክብር መዝገብ ሹም ሆኖ የሚሠራ ሠራተኛም መመደብ እንዳለበት በረቂቁ ተቀምጧል፡፡
በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ልደትን ለማስመዝገብ ሁለቱ ወላጆች እንዲቀርቡ አስገዳጅ የነበረው ተሻሽሎ ሞግዚት ወይም አሳዳሪ ሊያስመዘግቡ እንደሚችሉ ረቂቁ ይፈቅዳል፡፡ ለዚህ አሠራር እንዲያመች በአገሪቱ ካለው የመንግሥት አወቃቀር ሥርዓት በመጠቀም፣ በፌዴራልና በክልል የሲቪል ምዝገባ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት እንዲደራጅ በአዋጁ ተደንግጓል፡፡
የቤተሰብ ምዝገባ መዝጋቢ አካል እስካሁን በተለያዩ ምክንያቶች ያልተመዘገቡ ዜጎች በወሳኝ ኩነት የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት ወይም ሥልት በመንደፍ፣ በውዝፍ መመዝገብ እንዳለባቸው ተደንግጓል፡፡