
ተሟገት የምርጫ 97 ትውስታ!
ቀን: June 2, 2024
(ክፍል ሁለት)
በበቀለ ሹሜ
የመጨረሻው የዋንጫ ግጥሚያ
የቅንጅትና የኅብረቱ በድምፅ ለመታጋገዝና የትብብር/ጥምር መንግሥት ለመመሥረት መስማማት ለኢሕአዴግ ሌላ ራስ ምታት ነበር፡፡ በተቃዋሚዎቹ የሥልጣን እሽቅድምድም ለመጠቀም የነበረውን ቀዳዳ የሚዘጋ ሆነ፡፡ ይህን መበለጥ ለማካካስ፣ አፈናና እስራቱን እንደ ልብ አይለቀቅበት ነገር ሕዝብ በየአካባቢው በርትቷል፡፡ የአሜሪካ መንግሥት የምርጫውን ዴሞክራሲያዊነት ተቃዋሚዎች በሚያገኙት ወንበር እስከ መለካት አምርሯል፡፡ አሜሪካ ‹X› ምልክት ያደረገችበትና ሕዝብ የተፋው ገዥ ምን ሊደርስበት እንደሚችል ዓይቷል፡፡ በገዛ ድርጅቶቹና በደኅንነት መዋቅሩ ውስጥ የታሰበው ሳይቀር እየሾለከ ለተቃዋሚዎቹ ይደርሳል (በተለይ ለቅንጅት)፡፡ የኢሕአዴግ አባል መሆንና በአቋሞቹ ማመን ተለያይቶ በድርጅቱ ውስጥ መላወስ የእንጀራ ጉዳይ ከሆነ ቆይቷል፡፡ ‹‹በቀጣይ፣ እንደ ኢሕአዴግ፣ እንደ መንግሥት…›› በማለት ስብሰባ እያሳመሩ በልግመትና በአሳሳችነት ሲሸፍጠው የቆየው ቢሮክራሲ፣ የራሱ የገዥው ቡድን ድድብናና የጊዜው መጣበብ አንድ ላይ ገጥመው ችግሩን አክብደውታል፡፡
በአንድ በኩል በ‹‹ኮንዶሚኒየም›› ቤትና በሌሎች የተስፋ ዕርምጃዎች ሕዝብን ለማሳሳቅ ሲጥር በሌላ በኩል በጣም ዘግይቶ የመጣ የግብር ተመን አዲስ አበባ ላይ ሕዝብን ያበግንበታል፡፡ ኢነጋማን (የኢትዮጵያ ነፃ ጋዜጠኞች ማኅበር) ሰርዤ ሌላ ‹‹ኢነጋማ›› ፈጥሬ ተገላገልኩ ሲል በይግባኝ ፍርድ ቤት ለነባሩ ኢነጋማ ፈርዶ አዋረደው፡፡ ይህ ሳያንስ፣ የምርጫ ጽሕፈት ቤቱ ኢሕአዴጋዊ ማኅበራትን (የሴት፣ የወጣት፣ ወዘተ) ለታዛቢነት አቅፎ፣ ‹‹ገለልተኛ አይደላችሁም፣ በመመሥረቻ ጽሑፋችሁ ላይ ምርጫ መታዘብን ያካተተ ዓላማ ካለ አምጡ›› በሚል ሰበብ ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ቢያግድ ፍርድ ቤት እንዲታዘቡ ፈረደላቸው፡፡ እነ ኢሠመጉን ከታዛቢነት ማገድ አልተቻለውም፡፡ ይግባኝ አይል ጊዜ የለም፡፡ የታዛቢነት ፈቃድ መስጠት ግዱ ሆነ፡፡ በማጓተት ጊዜ ቢገድልም ኢሠመጉ ታዛቢ ማሰማራት አልተሳነውም፡፡
የብሔር/ክልላዊ ፖለቲካዊ ቡድድኖሽ የማርጀቱ ብዛት ተቃዋሚዎቹ ትግራይ ውስጥ እንኳ ተወዳዳሪና አዳማጭ ነበራቸው፣ በአዲስ አበባ ጭብጨባን ፈርቶ ያስከለከለው ኢሕአዴግ (የተሻለ ተቀባይነት ባለበት) ትግራይ ውስጥ እንኳ ፍርሐቱ አልለቀቀውም ነበር፡፡ ተቃዋሚዎቹን በጨዋነት ሰሚ አሳጥቶ ሊሸኝ አቅቶት የንብ ዓርማን እያሳዩ በሚጮሁ ደጋፊዎቹ አማካይነት የተቃዋሚዎቹን ስብሰባ ከመረበሽ አላመለጠም ነበር፡፡
የአዲስ አበባ ጭንቀቱ አያድርስ፡፡ ወጣት፣ ሴት፣ ነጋዴ፣ ወዘተ እየሰበሰቡ የመስበኩ ሥራ (በመሪው ጭምር) አላልቅ አለ፡፡ ያች የጋራ መኖሪያ ቤት ሕንፃ ሕዝብ ላይ የፈጠረችውን ደስታ እስከ ምርጫው ለማራዘም ከክፍለ ከተማ ክፍለ ከተማ እየዘለሉ ያላለቀለት ቤት ቁልፍ በመስጠት ሽር ጉድ መከራ ታየ፡፡ ተቃዋሚዎች ‹‹ሁከት መደገሳቸውን ትተው፣ የምርጫውን ውጤት በፀጋ መቀበል አለባቸው›› በሚል ጩኸት በውስጠ ታዋቂ የኢሕአዴግን አሸናፊነት በሰው ልቦና ውስጥ ለመትከል ተጣረ፡፡ የሩዋንዳ ዓይነት የመጨፋጨፍ አደጋን ከፍ አድርጎ ከመጮህ ባሻገር፣ ሕዝብን በሠልፍ እያንጋጉ በዕልቂት ፍርኃት አወነባብዶ ከኢሕአዴግ ጀርባ እንዲደበቅ ለማድረግ ታላቅ ሠልፍ ታቀደ፡፡ መረጃ በጧቱ የሚደርሰው ቅንጅት አልተበለጠም፡፡ ሚስጥር ከማጋለጥ አልፎ ኢሕአዴግን ቀደመና በአዲስ አበባ (ለእሑድ ሚያዝያ 30) ሕዝብን ስብሰባ ጠራ፡፡ ኢሕአዴግ ተከተለና ቅዳሜን መረጠ፡፡
የኢሕአዴግ ተቀጢላ የሴትና የወጣት ማኅበራት ‹‹ታሪክ ለመሥራት›› ተሰማሩ፡፡ የ‹‹ኮንዶሚኒየም›› ቤት፣ ሥራ፣ ብድር የማግኘት ተስፋ ሁሉ ወደ ሠልፍ መጎተቻ ገመድ ሆነው አገለገሉ፡፡ ‹‹ኢሕአዴግን ለመደገፍ ሳይሆን ምርጫው በሰላም እንዲያልቅና ሁሉም ለሰላም እንዲተባበር ነው የሠልፉ ዓላማ›› እየተባለ በየቤትና በየሱቁ ተዞረ፣ ስም እየጻፉ ማስፈረምም ተካሄደ፡፡ የንብ ምሥልን የያዘ ካኔታራ እየታደለ (አበልም ተከፍሏል ይባላል) በአውቶቡስ ሰው ከየአካባቢው ተግዞ፣ ቅዳሜ ዕለት መስቀል አደባባይ ንብ በንብ ሆነ፡፡ መለስ ዜናዊ ጉሮሮው እስኪሰነጠቅ እየጮኸ ሕዝብን በስሜት ሊያናውጥ ጣረ፡፡ ሕዝብ ‹‹ለብጥብጥና ለትርምስ የተዘጋጁ›› ተቃዋሚዎችን ነቅቶ እንዲጠብቅ ተለፈፈ፡፡ ‹‹ሰላምና ልማትን የተጠሙ ከኢሕአዴግ ጋር ናቸው!›› እየተባለ ተጮኸ፡፡ ንብ ያለበት ካኔቴራ የለበሰው ‹‹ደጋፊ›› በምርጫው ዕለት ድምፁን ለኢሕአዴግ መስጠት እንዳይረሳ ከንቲባ አርከበ ዕቁባይ አስታወሰ፡፡ ሬዲዮ ፋና ታሪከኛውን ሠልፍ ሲያራግብ አረፈደ፡፡ የሠልፈኛው ብዛት 1.2 ሚሊዮን አካባቢ ተገመተ፡፡ ኢሕአዴግ ከፍተኛ ድጋፍ እንዳለው ተረጋገጠ ተባለ፡፡ ኢሕአዴግ የልቡ ደረሰ፡፡ አዲስ አበባ ላይ የተገኘው ‹‹ስኬት›› በሌሎች አካባቢዎች ላይ ጫና እንደሚያሳድርለት ይገባዋል፡፡ የዕለቱ ዕለት ማታ በቴሌቪዥን ሠልፉን ከማገማሸር ባለፈ የጋምቤላ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ የሶማሌ፣ የአፋርና የሐረሪ ገዥዎች ቀደም ባለ ጊዜ የሰጡት መግለጫ (እንደ ትኩስ) በማጠናከሪያነት ተለቀቀ፡፡ ድርጅቶቻቸው ተለጣፊ መባላቸው በሕዝቦች ላይ የተሰነዘረ ስድብ ተደርጎ ቀረበ፡፡ እንስሳ ተባልን የሚለውም ነገር ተነስቶ ከቀድሞ የንቀት አባባሎች ጋር ተቆጣጠረ፡፡ የተቃዋሚዎች አካሄድ አብሮ መኖርን ሊያስቀር እንደሚችል ተጠቆመ፡፡ ዋናው መልዕክት (ማስፈራሪያ) ግን ባለው አወቃቀርና በአንቀጽ 39 ላይ ከመጣችሁ ጦርነት ነው የሚል ነበር፡፡
ከዚህ ዓይነቱ ፕሮፓጋንዳ በስተጀርባ የዚያን ዕለቷ አዲስ አበባ ሌላ ዓይነት ግብግብ ይዛ ነበር፡፡ ኢሕአዴጎች የተቃዋሚዎቹን የእሑድ ሠልፍ የሰው ደሃ ለማድረግ ብጥብጥ ይነሳል የሚል ሽብርና የሠልፉ ቀን ተራዝሟል የሚል ውሽት በመበተን ተጠምደዋል፡፡ ተቃዋሚዎችና ደጋፊዎቻቸው በተለያየ የግንኙነት መንገድ ሲያከሽፉ አመሹ፣ አደሩ፡፡
እሑድ ከረፋዱ ጀምሮ የአዲስ አበባና የአካባቢዋ ሕዝብ እንደ ጉድ ይፈላ ጀመር፡፡ በኢሕአዴግ ፈጣጣ ብልጠትና የሐሰት ወሬ አለመበለጡንና እልሁን አሳየ፡፡ በቅዳሜው የኢሕአዴግ ሠልፍ ‹‹ንብ››ን አንለጥፍም ያሉ የአዲስ አበባ ታክሲዎች የቅንጅት ምልክትን ለጥፈው ጥሩምባ እያንጣጡ ሕዝብ አጓጓዥ ሆኑ (በነፃ ጭምር)፡፡ ከቤት መኪኖችም የቅንጅትን የጣት ምልክት የሚያሳይ በርክቶ ታየ፡፡ ሠልፈኛው ሕዝብ መስቀል አደባባይ ሞልቶበት፣ ይልቅም መድረስ የማይቻል ሆኖበት በአደባባዩ መጋቢ መንገዶች ላይ ርቆ እየተርመሰመሰ የቅዳሜውን የኢሕአዴግ ሠልፍ አኮሰሰው፡፡ ድርጅታዊ ቅኝት ያላገኙ ነፃ ስሜቶች ተለቀቁ፡፡ ‹‹ትናንት ለ‹ቲ ሸርት› ዛሬ ለነፃነት››…፣ አርከበ ሌባ! መለስ ሌባ! አላሙዲን ሌባ! ዋይ ዋይ ለኢሕአዴግ! ንቦ አትናደፊ!…›› ተባለ፡፡ የስብሰባው ሥነ ሥርዓት መካሄጃ ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋረጠ፡፡ በስልክ አቤት አይባል የሞባይል ግንኙነት እንቢ አለ፡፡ ሕዝብ ጠብቆ ጠብቆ በድምፅ ካርዱ ሊበቀል እየዛተ ሲበተን ኤሌክትሪክ ተመለሰ፡፡ ሕዝብ እንደገና ተሰባሰበ፡፡ ዲስኩርና ሥነ ሥርዓቱ የተወሰነ ያህል ከተራመደ በኋላ ለኢሕአዴግ ዝናብ ደረሰለት፣ ተቋረጠ፡፡
ማታ የመብራት ኃይል ኮርፖሬሽን ኤሌክትሪክ የተቋረጠው በቴክኒክ ችግር ነው ቢል ማን ሊቀበለው፡፡ የኢሕአዴግ ‹‹እንከን የለሽ›› ምርጫ የት ድረስ እንደሆነ፣ ኢሕአዴግ በይፋና በሥውር እንዴት እንዴት እንደሚሠራ እንደገና አገር አወቀ፡፡ ኢሕአዴግ በራሱ ላይ እልህ አባበሰ፡፡ የእሑዱ ሠልፍ የሬዲዮ ፋናን ‹‹ገለልተኛነት››ም ገፎ ጣለ፡፡ በኢሕአዴግ ሠልፍ ጊዜ ዘጋቢዎችን በየአቅጣጫው አሰማርቶ ወዲያው ወዲያው ሃሎ እያለ ሲፈተፍት እንዳልነበር ሁሉ፣ ለእሑዱ ግን በዜና ከማውራት ያለፈ ነገር አልነበረውም ትችት ሲወርድበት፣ በሠልፉ ሰዓት የአማርኛ ሥርጭት አልነበረኝም ቢልም ተቀባይ አላገኘም፡፡ የመንግሥት መገናኛ ዘዴዎችና ሬዲዮ ፋና የኢሕአዴግን ሠልፍ አንድ ሚሊዮን አካባቢ ለመገመት እንደ ተግባቡ ሁሉ የእሑዱን ግዙፍ የተቀዋሚዎች የሕዝብ ትዕይንት ከኢሕአዴግ እኩል አድርገው መሳለቂያ ሆኑ፡፡ በቴሌቪዥን የቀረበው ቅጂ ራሱ አሳጣቸው፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ ያ ብሶተኛ ሁሉ ተትርፍርፎ መንገድ ለመንገድ በፈሰሰው ታላቅ ትዕይንት አንጀቱ ቅቤ ጠጣ፡፡ ተቃዋሚዎችም በፊርማ ጫና፣ በካኒቴራ፣ በአበልና በነፃ ማጓጓዣ ተደጋግፎ የተከናወነውን የኢሕአዴግ ሠልፍ በኩራት አሽሟጠጡ፡፡ የኢሕአዴግ ድል ውኃ እንዳገኘው የብዕር ጽሑፍ ታጠበ፡፡
ኢሕአዴግ የሚያደርገው ቢያጣ፣ በእሑዱ ትዕይንተ ሕዝብ ላይ አንዱ የቅንጅት መሪ ‹‹ኢሕአዴግ ወደ መጣበት ይመለሳል›› እያለ ያሰማውን መፈክርና ቦዘኔ ለሚለው መጠሪያ የሚመቹ ወጣቶችን (ሲጋራ እያጨሱ መለስን፣ አርከበን፣ አላሙዲን ሌባ ሲሉ የነበሩትን) ለይቶና መላልሶ እያሳየ ተቃዋሚዎች የወንጀልና የዝርፊያ ኃይል እያንቀሳቀሱ መሆናቸውንና ‹‹የኢንተርሃሞይ›› ዘረኛ ቅስቀሳ አራማጅነታቸውን አተተ፡፡ ውስጥ ውስጡንም ይኸውላችሁ ትግሬን ሁሉ እየነቀሉ ሊያባርሩ ነው የሚል ወሬ ተረጨ፡፡ የታክሲዎችን የፖለቲካ ድርጅት ዓርማ መለጠፍ በሕገወጥነት ነቀፈ፡፡ የታክሲ ባለቤቶች ንብረታቸውን ከሕገወጥ ተግባር እንዲጠብቁ አስጠነቀቀ፡፡ ቅንጅቶችንም ሕዝባዊ ስብሳባ አስፈቅደው ወደ ሠልፍ የመቀየር ሕገወጥነት እንደፈጸሙ አድርጎ ሊያቀርብ ሞከረ፡፡ አንዳንድ ቡድኖች ሕገወጥ ተግባር ሊፈጽሙ ስለመዘጋጀታቸው ደርሰንበታል ተብሎ ማስጠንቀቂያና የሌለ መደናገጥ ተለቀቀና ምርጫው በሰላም እንዲያልቅ ሻማና ጧፍ እናብራ የሚል ጥሪ ተጠራ፡፡ ግንቦት 4 ቀን በአዲስ አበባ የምርጫ ክልሎች የሻማና የጧፍ ቴአትር ተሠራ፡፡ ተቃዋሚዎችን ‹‹አመፅ››ን ባለመጠቀም ውል (በውጭ ታዛቢዎች ፊት) ለማሰር ከመሞከር ጋር ‹‹ስለሰላም›› የሚደረገው ሠልፍ በሌሎች አካባቢዎችም ሲንጋጋ ቆየ፡፡ ተቃዋሚዎችም በበኩላቸው የማን ይብስ የሠልፍ ውድድሩን ተያያዙት፡፡ አፈሳ መጀመሩንና የቅንጅትን ማኅተም በማስመሰል አሠርቶ የመንግሥት ሹሞችን ቅንጅት ሊገድል ስለመዘጋጀቱ መረጃ ተገኘ በማለትና ፈንጅ አፈንድቶ ቅንጅትን ለመወንጀል መታቀዱን ቅንጅቶች አሳወቁ፡፡ በምርጫው ዕለት ከሌሊቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ የሠልፍ ተራ ቀድሞ በመያዝና ሒደት በማጓተት የተቃዋሚዎችን ድምፅ ለመቀነስና በቆጠራ ጊዜም መብራት በማጥፋት የድምፅ ወረቀት የመቀየር ማጭበርበር ሊፈጸም ስለመታሰቡ በመግለጽ መራጩ ሕዝብ እንዳይበለጥ አስጠነቀቁ፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ በኢሕአዴግ ተቆራርጣ ሳታልቅ ቅንጅትን ምረጡ›› ሲሉም ጥሪ አቀረቡ (በሬዲዮ)፡፡ ዘመቻ አልደምቅለት ያለው ኅብረቱም ችጋርን ለማስወገድ ስላለው ዕቅድ፣ ስለዕርቅና ስለጥምር ሽግግር መንግሥት አስፈላጊነት አስታወሰ (ባድመን የምንለቅ ከሆነ ለምን ደማችን ፈሰሰ? ነበር ወይ ሐበሻን ለመቀነስ? የሚል ማፈሪያ ዘፈን ብቅ ጥልቅ እያደረገ)፡፡
የፍፃሜው ግጥሚያ ኅብረት፣ ኢሕአዴግና ቅንጅት በየፊናቸው በሰጡት የቃለ መጠይቅ ዝግጅት ተከናወነ [ለመጠይቆቹ የቀረቡት በተለያዩ ቀናት ነበር፡፡ ከመለስ ቃለ መጠይቅ በቀር የኅብረትና የቅንጅት ቃለ መጠይቆች በሚተላለፉበት ጊዜ ኢቲቪ ከግርጌ ጥያቄዎቹን ያወጡት ራሳቸው ድርጅቶቹ መሆናቸውን ይገልጥ ነበር፡፡ መለስ የሚጠየቀውን የማያውቅና የእስከ ዛሬዎቹ ቃለ መጠይቆችም የዚህ ዓይነት ባህርይ ያላቸው መሆኑ የማይታወቅ ይመስል]፡፡ ዋናው ግጥሚያ በኢሕአዴግና በቅንጅት መሀል ነበር፡፡ የኢሕአዴግ ተጋጣሚነትም ቢሆን ከመንፈራፈር የማይሻል ነበር፡፡ የመለስ የጨዋታ ብልጠት እንኳ ቢሳል ቢሳል ሥለት አላወጣ ብሎ አስቸገረ፡፡
- ኢሕአዴግ 14 ዓመታት ሞክሮ አቃተው ይልቀቅ የሚለውን የተቃዋሚዎችን ውትወታ፣ የእንግሊዝ የሌበር ፓርቲ ለሦስተኛ ጊዜ ሊገዛ እየተወዳደረ መሆኑንና በጃፓን አንድ ፓርቲ ለ50 ዓመታት በሥልጣን መቆየቱን እማኝ ቆጥሮ ሊያከሽፍና በሥልጣን መቆየቱን አግባብ ሊያደርግ ሲጥር ታየ፡፡
- አርሶ አደሩ መሬት እንዲሸጥ ስለማይሻ ቢያንስ አርሶ አደሩ የሚመርጠው እኛን እንደሆነ እናውቃለን፣ የመሸነፍ ሥጋት የለብንም በማለት ማሸነፉን ሊያስተማምን ሞከረ፡፡
- ተፈራ ዋልዋ ‹‹መምህራን በትምህርቱ ላይ ለውጥ እስካላመጡ ጭማሪና ዕድገት አያገኙም›› ማለቱ የሚረሳና በቀላሉ የሚደለል ያለ ይመስል፣ ጭማሪና ዕድገቱ የተጓጎለው ‹‹ውጤት ተኮር›› ምዘናው በሁሉም ቦታ ተግባራዊ እስኪሆን ነው በሚል ውሸት ‹‹አይደርስ መስሏት …›› ለሚል ትዝብት ተዳረገ፡፡
- ‹‹የአክሱም ሐውልት ለወላይታ ምኑ ነው›› የምትል መዘዘኛ ንግግሩን፣ እኔ እንደዚያ ያልኩት የሁሉም ታሪክ ይታወቅ፣ ለምን አክሱም፣ ጎንደር፣ ላሊበላ፣ ብቻ ይባላል የጨለንቆውም ሌላውም ይታወቅ በሚል የመልዕክት አግባብ ነው ብሎ ሊያርም፣ እግረ መንገዱንም የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ተቆርቋሪ ሆኖ መራጭ ሊያበዛ ሞከረ፡፡
- ሌሎች ባልደረቦቹ እንዳደረጉት፣ ተቃዋሚዎች ደርግ ጨፍጫፊ አልነበረም የሚሉ አስመለ፡፡ ለአመፅና ለብጥብጥ የቆሙ የጥፋት ፓርቲዎች ናቸው፣ አማራጭ ፓርቲ የለም ሲል ደመደመ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምርጫ እያጣ ኢሕአዴግን የሚመርጥ ከሆነ ሥጋት ነው በሚሉ አነጋገር ኢሕአዴግን ከወዲሁ ሾመ፡፡
- የፌዴራል በጀት አመዳደብን በተመለከተ ተቃዋሚዎች ትግራይን ለመንካት እነ ጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉሙዝን በመጠጊያነት እንደተጠቀሙ ሁሉ መለስም እነ ጋምቤላን መሸወጃ አድርጎ ተጠቀመ፡፡ ጋምቤላ ሶማሌ፣ ሐረሪና አፋር ቤኒሻንጉል ጉሙዝ በቅርብ ዓመታት ያገኙትን የበጀት ድጎማ በነፍስ ወከፍና በሙሉ ሒሳብ እያሳየ ለአማራና ለኦሮሚያ ተሰጥቶ ከነበረው ጋር እያገናዘበ እነዚህ ክልሎች ኋላቀርነታቸው የባሰ ስለሆነ ይታገዙ ሊባል ሲገባ ብልጫ አገኙ እየተባለ መብጠልጠላቸውን አሳጣ፡፡ ተቃዋሚዎች ለመላ ኢትዮጵያ ልማት የቆሙ መሆን አለመሆናቸው ላይ የጥያቄ ምልክት አስቀመጠ፡፡ ብዙ ሰው ጆሮውን አቁሞ ይጠብቀው የነበረውን የትግራይን የበጀት ድርሻ ሳይናገር ዘለለው፡፡ ስለእነ ጋምቤላ የተባለውን የመታከኪያ ሐሜት ፉርሽ ቢያደርግም ዋናውን ሐሜት ሳያከሽፍ ቀረ፡፡ ኢሕአዴግ-ሕወሓት የሚነዘነዙበትን የኩባንያዎች ጉዳይ ጭራሽ ሳያነሳ አለፈው፡፡
ቅንጅቶች በበኩላቸው በሰጡት ቃለ መጠይቅ ደግሞ የኢሕአዴግ ኩባንያዎች የሀብት ምንጭ ምርኮ፣ ውርስና ተራድኦ መሆኑን እያስታወሱ በ‹‹ኤፈርት›› ድርጅቶች የትግራይ ሕዝብ ከተጠቀመ እሰየው፣ ግን ኩባንያዎቹ የማን ናቸው? በግልጽ ይታወቅ፣ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ እንኳን አያውቅም፡፡ በትግራይ ሕዝብ ስም ከሆነ የሚነገደው ሕዝቡ ዕዳውን ይወቅ፣ የኦዲት ሪፖርት ይቅረብለት፡፡ መሰቦ ሲሚንቶ ትግራይ ውስጥ 70 ብር ሲሽጥ ባህር ዳር ላይ ግን (ከሙገር ጋር ለመወዳደር) 65 ብር ይሸጣል እያሉ የትግራይ ሕዝብ ብሶት ተናጋሪ እስከመሆን ድረስ የፖለቲካ ብልጠቱን ከሕወሓት ተቀበሉ፡፡
የሚቻለውን ያህል ድጋፍ መሰብሰብ፣ ‹‹አደገኛ ቦዘኔ›› የሚባለውም ወገን እንዲመርጥ መጠየቅ ኃጢያት አለመሆኑን ከመናገር በላይ ኢሕአዴግ ‹‹አደገኛ›› የሚለው ሠራዊት በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ሄዶ የተዋጋ ባለውለታ መሆኑን አስታወሱ፡፡ አደገኛ ቦዘኔ እየተባለ የሚታሰረው ወጣትም በ14 ዓመት የኢሕአዴግ አገዛዝ የተፈለፈለ ስለመሆኑም ዓመታት እየደመሩ አሠሉለት፡፡
የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ከተቃዋሚዎች ጋር አቃርኖ የምርጫ መጠቀሚያ ለማድረግ ኢሕአዴግ ያካሄደውን ዘመቻም አልማሩለትም፡፡ በአደባባይ እንዳደረጉት ሁሉ በቃለ መጠይቁም በአንዋር መስጊድ የሠራውን፣ የሙስሊሙ ኅብረተሰብ ያዘነበትን የኢራቅን ወረራ ደግፎ የቆመበትን ጊዜና ሌላ ሌላውንም ገመናውን እያነሱ የገዛ መቅለያው አደረጉት፡፡ የሩዋንዳ ዓይነት አደጋ ለመጎተት ከእነሱ ይልቅ የተሻለ ቅርበት እንዳለው ነገሩት፡፡ ለደርግም ከእነሱ ይልቅ እሱ መቅረቡን በቀላል አማርኛ አስቀመጡለት፡፡ ደርግ ገድሎ የፍየል ወጠጤን ያዘፍናል፣ ኢሕአዴግ ደግሞ ይገድልና አብሮ ያፋልጋል በሚል ንፅፅር፡፡
ቢመረጡ በሕገ መንግሥት መሠረት የሚሠሩ መሆኑን፣ ከሕገ መንግሥቱ እንዲለወጡ የሚሿቸው አንቀጾች መኖራቸውን፣ እነሱም ቢሆኑ የሚለወጡት በሕዝብ ውሳኔ መሆኑን፣ የደኅንነት አካላት ሠራዊትና የመንግሥት ሠራተኛ የመበተን ባህርይም እንደሌላቸው በመግለጽ የአፀፋ ፕሮፓጋንዳ አካሄዱ፡፡ የጥላቻና የቂም በቀል ዘመን ማክተሙንም ሰበኩ፡፡
ሁነኛ የብሶት ጥያቄዎችንም ደቀኑ፣
- በደርግም ሆነ በኢሕአዴግ ለተወረሱ ንብረቶች (ሰዎችን በማያፈናቅል ሁኔታ) ምላሽ ለመስጠት፣
- መንግሥት ባሻው የሚያስነሳበትን ሁኔታ ለማስቀረትና የመሬት ይዞታ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣
- በአፍ መፍቻ ቋንቋ ለመማር መብት፣
- አሃዳዊ የትምህርት አሰጣጥን ለማስቀረትና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን ከ9 እስከ 12 ለማድረግ፣
- የግብር ጫናን ለማቃለልና
– የፖለቲካ ፓርቲ ነጋዴነትን ለማስቀረት የቆሙ መሆናቸውን ገለጹ፡፡
ኢሕአዴግ በጎል ሊያስተካክላቸው አልቻለም፡፡ ድህነቱና ቀውሱ ሳይሰፋ የኢትዮጵያን ህልውና የማትረፍ ዕድልንም ከኢሕአዴግ መውረድና ከእነሱ ወደ ሥልጣን መውጣት ጋር አዛምደው ተሰናበቱ፡፡
ግንቦት 7 – የሕዝብ ቀን!
‹‹እንከን የለሽና ሰላማዊ ምርጫ››ን የሚዘምር የአስመሳይነትን ልብስና ጓንት አመለኛው ኢሕአዴግ ደራርቦ ለበሰ፡፡ ተቃዋሚዎችንና ሕዝብ ላለመመንተፍ ዓይናቸውን አነቁ፡፡ በምርጫ ቦርድ የመጨረሻ ሰዓት ገለጻ ሳይወሰኑ በአመራረጥ ላለመሳሳት የበኩላቸውን ዝግጅት አደረጉ፡፡ ከሌሊቱ አሥርና አሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ ሕዝብ ሠልፍ ያዥ ሆነ፡፡ በጎታታ መስተንግዶና በጊዜያዊ መስተጓጎል ሳይመረርና ለሁከት ማማሃኛ ሳይሆን እንዲያውም መላ እያማከረ፣ ከደንብ ውጪ የሆኑና አጠራጣሪ ድርጊቶችን (አድልኦዊ ገለጻን፣ ጣልቃ ገብነትን፣ ምልክት የተደረገባቸው የምርጫ ወረቀቶችን፣ የሚለቅ የጣት ቀለምን፣ ወዘተ) እዚያው በዚያው እየጠቆመና በስልክና በመልዕክተኛ እያጋለጠ ቁርሴና ምሳዬ ሳይል ታገለ፡፡ አልጋ የያዙ ታማሚዎች ተደግፈው፣ ትኩስ ሐዘንተኞች ዕንባቸውን ውጠው፣ ያልጠኑ አራሶች ወገባቸውን አስረው ድምፅ ሰጡ፡፡
የምርጫው ማክተሚያ (12፡00 ሰዓት) እየቀረበ ሲመጣ ሕዝብ ድምፁን ሳይሰጥ ላለመሄድ በተለያየ መንገድ ተፅዕኖ አደረገ፡፡ አሥራ ሁለት ላይ በምርጫ ጣቢያ የተገኘ መራጭ ሁሉ ሳይመርጥ አይሄድም በሚለው መመርያ የመጠቀም ዕድሉን ላለማጣት ብርድን፣ ድካምንና እንቅልፍን አሸንፎ እስከ እኩለ ሌሊት፣ እስከ ዘጠኝና አሥራ አንድ ሰዓት ድረስ ድምፅ ሰጠ፡፡ ምርጫ ካበቃም በኋላ በድምፅ ቆጠራ ላይ ማጭበርበር እንዳይፈጸም አስደናቂ ፍጥጫና ትንቅንቅ ሲካሄድ ታየ፡፡ በዚህ ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ በኑሮ ሁኔታው የቱን ያህል እንደተንገሸገሸ (ፍትሕና ዴሞክራሲን ምን ያህል እንደተጠማ) ለኢትዮጵያ ፖለቲከኞችና ለዓለም አሳወቀ፡፡
ጭንቅ ውስጥ ያለው ኢሕአዴግ በየአቅጣጫው በበተናቸው የመንግሥት ጋዜጠኞች አማካይነት ቀኑን ሙሉ በሬዲዮና በቴሌቪዥን የምርጫውን ስኬታማነት እያናፈሰና ጥቆማዎችን፣ አስተያየቶችንና ማስተካከያዎችን እያስተናበረ ሥር ሥሩን ግን ከጉድ ለመትረፍ ሲዋደቅ ዋለ፡፡ ከምርጫው በኋላ የቀረቡበት አቤቱታዎች እንደሚጠቁሙት የተንቀሳቃሽ ታዛቢዎችን እግር የጠበቁ፣ ገጠር ገብነትን፣ የመገናኛ ችግርንና ርቀትን ተገን ያደረጉ፣ በአፈና ብርታት፣ ማስረጃ አሳጥቶ በመካድ ወይም በልምድ ማጣት ሽፋን ሊደበቁ የተሞከሩ በመልክና በዓይን አውጣነት ደረጃ የተለያዩ የሸፍጥ ሥራዎች መከሰታቸው አልቀረም ነበር (ተባባሪ ያልሆኑ የምርጫ አስፈጻሚዎችን በጫና ማንበርከክ ካልሆነም በማስፈራራት፣ በድብደባና በእስራት ማራቅ፣ የድምፅ አሳጠጡን ሚስጥራዊነት ማጉድፍ፣ የምርጫ ወረቀትን በእጅ መረከብ፣ በተቃዋሚነት የተፈረጁ መራጮችን በተለያየ መንገድ ከምርጫ ማደናቀፍና የምርጫ ሰዓት ሳያበቃ ሒደቱን ማስቆም ሊጠቀሱ ይችላሉ)፡፡
ኢሕአዴግ በዚህ ብቻ አልተወሰነም፡፡ ድምፅ አጭበርበሮ አሸንፌያለሁ ማለት በሥልጣን ላይ ለመቆየት ዋስትና እንደማይሆነው ታውቆታልና የምርጫው ዕለት ማታውኑ (ተቃዋሚዎች የምርጫውን ውጤት አንቀበልም ብለው ሁከት እንዳይፈጥሩ አስቀድሞ በመጠንቀቅ ሰበብ) ለአንድ ወር የሠልፍና የቤት ውጪ ስብሰባ ማካሄድ መታገዱን፣ የአዲስ አበባ አካባቢ የፀጥታ ኃይሎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ በሆነ አንድ ወጥ ዕዝ ሥር መግባታቸውን ራሱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አወጀ፡፡ መለስና ቡድኑ በድርጅታዊ ቀውሱ ጊዜ ድርጅትን ‹‹ለማዳን›› ሕገ ደንብ እንደጣሰና መንግሥታዊ ሥልጣኑን እንደተጠቀመ ሁሉ፣ ሸፍጥን እንቢ ባለ የሕዝብ ድምፅ ከሥልጣን ላለመወርወር አስቸኳይ ጊዜን የሚያሳውጅ ሁኔታ በሌለበት (ሕገ መንግሥቱን ጥሶ) ‹‹አስቸኳይ›› ሳይል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጣለ፡፡
የድምፅ አሰጣጡ ከቦታ ቦታ እንደነበረው ርዝማኔ ከእሑድ ማታ ጀምሮ እስከ ሰኞ አጥቢያ እየታየ በመጣው ቆጠራ የተገኘው ውጤት ወደ አሸናፊነት እንደማያደርስ ሲያመለክት፣ የድምፅ ቆጠራው ወደ ለየለት የነፍስ አድን ውንብድና ተሸጋገረ፡፡ በቆጠራ ውስጥ የሹማምንትና የታጣቂዎች ጣልቃ መግባትና ቆጠራዎች እንዲቋረጡ ማድረግ ደረሰ፣ የሕዝብ ድምፅ ግልበጣ ሒደት ተከተለ፡፡ የድምፅ ወረቀት መቀየር፣ የተዘጋ ኮረጆ ቀድዶ ወይም ሳይዘጋ ሰድዶ ማስተካከልና ቁጥር መለወጥ አስቀድሞ ያመለጠና በተቃዋሚ እጅ የገባ መተማመኛ ሰነድ ነጥቆ መረጃ ማጥፋት፣ ካልሆነም ኮረጆ ጠልፎ ደብዛ በማጥፋት ወይም በሌላ መንገድ የምርጫ ውጤቱን ተቀባይነት የማሳጣት ተግባራት ውስጥ ተገባ፡፡
ሰኞ (ግንቦት 8) ኢሕአዴግ በአዲስ አበባና በአንዳንድ ከተሞች ሽንፈት ቢደርስብኝም፣ በአጠቃላይ በመንግሥትነት ለመቀጠል የሚያስችል ድል ተቀጃጅቻለሁ የሚል ‹‹የደስታ›› መግለጫ አወጣ፡፡ ተቃዋሚዎቹ በታመነላቸው ድል ሳይደለሉ መግለጫውን ተቃወሙት፡፡ የምርጫ ቦርድ የምርጫ ውጤትን የመግለጽ ሥልጣኑ የእሱ ሆኖ እያለ፣ ገና ቆጠራ ባልተጠናቀቀበትና በተጓጎለበት ሁኔታ (ቢያንስ ከምርጫ ክልሎች ውጤትን አሰባስቦ ባልያዘበት ደረጃ ላይ) በተለይ ከገዥ ፓርቲ የሚሰጥ የአሸናፊነት መግለጫ በውጤቱ ላይ ጫና ሊያሳርፍ እንደሚችል አስቦ መቃወም ሲገባውም፣ ‹‹መብት ነው›› ማሸነፍና አለማሸነፉን ከመተማመኛዎችና ከሚለጠፈው ውጤት ማወቅ ይቻላል የሚል ማብራሪያ ሰጪ ሆኖ አረፈ፡፡ ይህን ማብራሪያ የሰጠ ተቋም በኋላ የተጓጎለ ውጤት እንዲላክለት ሲማፀን፣ አልፎም ወር ሙሉ ‹‹ውጤት›› ሲለቅም ታየ፡፡ (ይቀጥላል)
[የሰሚ ያለህ የኢትዮጵያ ሕዝቦች እሪታ ከበቀለ ሹሜ 1999 መጽሐፍ የተወሰደ]
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡