
3 ሰኔ 2024, 08:29 EAT
ተሻሽሏል ከ 30 ደቂቃዎች በፊት
በሜክሲኮ ምርጫ ክላውዲያ ሼንባም የሜክሲኮ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዝዳንት በመሆን በከፍተኛ ድምጽ ተመርጠው ታሪክ ሠሩ።
እሑድ በተካሄደው ምርጫ ድምጽ ሰጪዎች የ61 ዓመቷ የቀድሞዋ የአገሪቱ መዲና የሜክሲኮ ሲቲ ከንቲባ አስከ 60 በመቶ የሚደርስ ድምጽ በማግኘት ዋና ተቀናቃኛቸው ሶቺል ጋልቬዝን አሳማኝ በሆነ መልኩ አሸንፈዋል ተብሏል።
የሼንባም ሞሬና ፓርቲ አሸናፊነቱን ከወዲሁ እየገለጸ ይገኛል። ዛሬ ሰኞ ረፋድ ላይ ይፋ በሆነው የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት ሼንባም በአሳማኝ ሁኔታ አሸናፊ ሆነዋል።
በውጥረት ውስጥ በተካሄደው ምርጫ መራጮች የሜክሲኮ ኮንግረስ አባላት እና በስምንት ግዛቶች ያሉትን ገዥዎች እንዲሁም የሜክሲኮ ከተማ አስተዳዳሪን መርጠዋል።
በመላ አገሪቱ ከ20 በላይ የምርጫ ተወዳዳሪ ዕጩዎች መገደላቸውን መንግሥት ቢገልጽም፣ በግል የተደረጉ ጥናቶች ቁጥሩን 37 አድርሰውታል።
እሑድ ዕለት በፑብላ ግዛት በምርጫ ጣቢያዎች ላይ በተፈጸሙ ሁለት ጥቃቶች ሁለት ሰዎች መሞታቸውን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
እአአ ከ2018-23 ሜክሲኮ ሲቲን ያስተዳድሩት ሳይንቲስቷ ሼንባም የተሰናባቹ ፕሬዝዳንት አንድሬስ ማኑኤል ሎፔዝ ኦብራዶር ድጋፍ አላቸው።
ከ 2018 ጀምሮ በሥልጣን ላይ የቆዩት ሎፔዝ ኦብራዶር በሜክሲኮ ሕገ መንግሥት መሠረት ፕሬዝዳንቶች ስድስት ዓመታት የሚዘልቀው ከአንድ የሥልጣን ዘመን በላይ እንዳያገለግሉ ስለሚገድብ በድጋሚ መወዳደር አልቻሉም።
- ‘ጎልደን ቪዛ’ ምንድነው? የትኞቹ አገራትስ ይሰጣሉ? ለምንስ በጣም አነጋጋሪ ሆነ?ከ 5 ሰአት በፊት
- አሜሪካ የተኩስ አቁም ስምምነቱን እስራኤል እንደምትቀበል እጠብቃለሁ አለችከ 4 ሰአት በፊት
- ቢሊየነሩ ሩፐርት መርዶክ ለአምስተኛ ጊዜ ተሞሸሩከ 4 ሰአት በፊት
በቅርብ ጊዜ የተደረጉ የሕዝብ አስተያየቶች ወደ 60 በመቶ የሚጠጋ የሕዝብ ድጋፍ እንዳላቸው የተገለጸላቸው ፕሬዝዳንቱ፣ የሞሬና ፓርቲ አባል ለሆኑቱ ለሼንባም ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።
ፕሬዝደንት ሎፔዝ ኦብራዶር ወደ ኃላፊነት ሲመጡ ቃል የገቧቸውን ጉዳዮች ሳይፈጸሙ ቢቀሩም፣ ድህነትን ለመቀነስ እና አዛውንቶችን ለመርዳት ያደረጉት ጥረት ተወዳጅ አድርጓቸዋል።
የፕሬዝዳንቱ ድጋፍ ማግኘታቸው ለሼንባም የመራጮችን ቁጥር በእጅጉ አሳድጎ ሊሆን ቢችልም ከፍተኛ ተቀባይነት ካላቸው መሪ ግፊት ምን ያህል ነፃ መሆናቸውን በተመለከተ ጥያቄዎች ተነስተዋል።
ሼንባም ራሳቸውን የቻሉ ሴት መሆናቸውን አበክረው ገልጸው፤ በሎፔዝ ኦብራዶር የተጀመሩ በርካታ ስኬቶች ናቸው የተባሉት ሥራዎች ለመቀጠል ቃል ገብተዋል።
ፓርቲያቸው ባለፉት ስድስት ዓመታት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሜክሲካውያንን ከድህነት ማላቀቁን ይናገራል።
ሞሪና በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ለመምጣቱ ዝቅተኛውን የደመወዝ ክፍያ በእጥፍ መጨመርን እና ሌሎችም ፖሊሲያቸውን ዋነኛ ምክንያት አድርገዋል።
ከፖሊሲ ላይ ሌሎች ምክንያቶች እንዳሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ጠቁመዋል። ለምሳሌ በውጭ አገር የሚኖሩ ሜክሲካውያን በአገር ውስጥ ላሉ ጓደኞቻቸው እና ቤተሰቦቻቸው የሚልኩት ገንዘብ መጨመር አንደኛው ነው።

በምርጫው ላይ የሼንባም ዋነኛ ተፎካካሪ ሆነው የቀረቡት ሴናተር እና ባለሃብት የሆኑት ሶቺል ጋልቬዝ ናቸው።
የ61 ዓመቷ ጋልቬዝ የተመረጡት የሞሬና ፓርቲ አገዛዝን ለማቆም ፍላጎት ባላቸው የፓርቲዎች ጥምረት ነው።
እሳቸው እና ፓርቲያቸው ስትሬንግዝ ኤንድ ኸርት ፎር ሜክሲኮ አገሪቱ በምርጫው ወቅት ያጋጠማትን ሁከትና ብጥብጥ ተችተዋል።
በመዝጊያ የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የሜክሲኮ ዜጎች ድምጻቸውን ከሰጧቸው “ወንጀልን የምትጋፈጥ በጣም ደፋር ፕሬዝዳንት” እንደሚያገኙ ተናግረዋል።
የአገሪቱ ምርጫ እሑድ ያበቃ ሲሆን አሸናፊው ከጥቂት ወራት በኋላ ሥራውን ይጀምራል።