
ከ 4 ሰአት በፊት
አሜሪካ የጋዛውን ጦርነት ለማስቆም ያቀረበችውን የተኩስ አቁም ስምምነት ሐማስ የሚቀበል ከሆነ እስራኤልም በተመሳሳይ እቅዱን ተግባራዊ እንደምታደርግ እጠብቃለሁ አለች።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ባለፈው ሳምንት ባቀረቡት ጦርነት የማስቆም አማራጭ መሠረት የተኩስ አቁም ስምምነቱ በሦስት ደረጃዎች ተፈጻሚ ይሆናል። በእቅዱ መሠረት በስድስት ሳምንታት ውስጥ የእስራኤል ጦር በርካታ ፍልስጤማውያን ከሚኖሩባቸው አካባቢዎች ይወጣል።
ስምምነቱ በሐማስ እገታ ስር ያሉ ሰዎችን ነጻ እንደሚያወጣ እንዲሁም በእስራኤል ቁጥጥር ስር የሚገኙ ፍልስጤሞችንም ያስለቅቃል።
እቅዱ ቋሚ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ እና ከፍተኛ የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ጋዛ በማድረስ ጋዛን ወደ መልሶ ገንባታ የሚያስገባ ነው።
ይህ እቅድ ይፋ መሆኑን ተከትሎ ሐማስ በባይደን የቀረበውን አማራጭ በበጎ እንደሚመለከተው ገልጿል። አንድ ከፍተኛ የሐማስ መሪ ለቢቢሲ ሲናገሩ እስራኤል ስምምነቱ ተፈጻሚ የምታደርግ ከሆነ ሐማስም እቅዱን ተግባራዊ ያደርጋል ብለዋል።
የዋይት ሃውስ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢይ ሐማስ በእቅዱ ከተስማማ እስራኤል ለአሜሪካ እቅድ ተግባራዊነት ትስማማለች ብለን እንጠብቃለን ብለዋል።
የዋይት ሃውስ ባለስልጣኑ ይህን ይበሉ እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢኒያሚን ኔታኒያሁን ጨምሮ ከፍተኛ የእስራኤል ባለስልጣናት የአሜሪካን አማራጭ እንደማይቀበሉት ሲገልጹ ተሰምተዋል።
- ‘ጎልደን ቪዛ’ ምንድነው? የትኞቹ አገራትስ ይሰጣሉ? ለምንስ በጣም አነጋጋሪ ሆነ?ከ 5 ሰአት በፊት
- በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ የመጣው የሞት ቅጣት፣ ወንጀልን ለመግታት አስተዋጽኦ አለው?ከ 5 ሰአት በፊት
- ቢሊየነሩ ሩፐርት መርዶክ ለአምስተኛ ጊዜ ተሞሸሩከ 4 ሰአት በፊት
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ የሐማስ ወታደራዊ እና አስተዳደራዊ አቋም ሙሉ በሙሉ ሳይወገድ እና በእገታ ስር ያሉ ሰዎች በሙሉ ነጻ ሳይወጡ የተኩስ አቁም ለማድረግ አልስማማም ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ሁለት ቀኝ ዘመም የእስራኤል ሚኒስትሮች አገራቸው የተኩስ አቁም ለማድረግ ከተስማማች ጥምር መንግሥቱን አፍርሰን ስልጣን እንለቃለን ሲሉ ዝተዋል።
የፋይናንስ ሚኒስትር ቤዛሌል ስሞትሪች እና የብሔራዊ ደኅንነት ሚኒስትር አታማር ቤን-ጋቪር ሐማስ ሙሉ በሙሉ ሳይወገድ እስራኤል ወታደራዊ እርምጃዋን የሚያስቆም የተኩስ አቁም ስምምነት መድረስ የለባትም ብለዋል።
ጆን ኪርቢይ ግን ለኤቢሲ ኒውስ ሲናገሩ እስራኤል ለዚህ ስምምነት አዎንታዊ መልስ እንደምትሰጥ ሙሉ እምነት አለን ብለዋል።
ከሐማስ ይፋዊ ምላሽ እየጠበቅን ነው ያሉት ኪርቢይ ሁለቱም አካላት ወደ ተኩስ አቁም ስምምነቱ የመጀመሪያ ክፍል ትግበራ በፍጥነት ይገባሉ ብለን እንጠብቃለን ብለዋል።
ትናንት እሁድ ግንቦት 25/2016 ዓ.ም. የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እስራኤል ስምምነቱን እንድትቀበል ጫና ለመፍጠር ከመከላከያ ሚስትሩ ዮቫን ጋላንት እና ከጦርነት ካቢኔ አባሉ ቤኒ ጋንትዝ ጋር በስልክ መነጋገራቸው ተገልጿል።
ኪሪቢይ ግን የአሜሪካ ደኅንነት ሐማስ በአሁኑ ወቅት መስከረም 26/2016 ዓ.ም. የፈጸመውን ጥቃት አይነት መልሶ የመፈጸም አቅም ጨርሶ የለውም ብሎ ያምናል ብለዋል።
“አሁንም ቢሆን ሐማስ በእስራኤል ሕዝብ ላይ አደጋ መደቀን አይችልም እያልን አይደለም። ግን ከዚህ ቀደም ያደረጉትን መልሰው ለመፈጸም ወታደራዊ አቅም የላቸውም” ብለዋል።
እስራኤል-ሐማስ ጦርነት አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ሕጻናት የሆኑ ከ36ሺህ ያላነሱ ሰዎች በጋዛ ተገድለዋል።