እአአ 2007 ላይ በሶማሊያ የነበሩ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ከሞቃዲሾ ሲወጡ
የምስሉ መግለጫ,እአአ 2007 ላይ በሶማሊያ የነበሩ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ከሞቃዲሾ ሲወጡ

ከ 1 ሰአት በፊት

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከሶማሊያው ፕሬዝዳንት ጋር በነበራቸው የስልክ ንግግር በቀጠናው ያለው ውጥረት መርገብ እንዳለበት አሳስበዋል።

ብሊንክ ቅዳሜ ግንቦት 24/2016 ዓ.ም. ከሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ጋር በነበራቸው ውይይት ቀጠናዊ ውጥረትን መቀነስ አስፈላጊነት ለፕሬዝዳንቱ መናገራቸው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል።

የብሊንከን እና የፕሬዝዳንት ሐሰን የስልክ ውይይት የተደረገው፤ የሶማሊያ መንግሥት በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር በሶማሊያ በሰላም ማስከበር ሥራ ላይ ተሰማርቶ የሚገኘውን የኢትዮጵያን ሠራዊት ለማስወጣት የመወሰኑ ዜና ከተሰማ በኋላ ነው።

ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ተነጥላ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ማግኘት የሚያስችላትን ስምምነት መፈረሟ ይታወሳል።

ይህ የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ መንግሥታት ሰምምነት ሶማሊያን እጅጉን ከማስቆጣቱ ባሻገር በሞቃዲሾ እና አዲስ አበባ መካከል ከፍተኛ የዲፕሎማሲያዊ ውጥረት አስከትቷል።

የሶማሊያ ፕሬዝዳንት የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ የሆኑት ሑሴን አሊ በሶሻል ሚዲያ የውይይት መድረክ ላይ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር በሶማሊያ በሰላም ማስከበር ላይ ተሰማርተው የሚገኙ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት በአውሮፓውያኑ 2024 ማብቂያ ላይ ከሶማሊያ ጠቅልለው ይወጣሉ ብለዋል።

በሶማሊያ ሰላም ለማስከበር ተሰማርቶ የሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት ትራንዚሽን ሚሽን ኢን ሶማሊያ (አትሚስ) (የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ) በ2024 መጨረሻ ቆይታው ይጠናቀቃል።

ይሁን እንጂ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪው ዓርብ ምሽት በነበረ የኤክስ ውይይት ላይ ሶማሊያ የአትሚስ ኃይል ተሳታፊ የሆኑት የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ከተልዕኮው ወጪ ሆነው ከኬንያ፣ ከጂቡቲ፣ ከኡጋንዳ እና ከቡሩንዲ በተወጣጡ ወታደሮች ተልዕኮው በአንድ ዓመት እንዲቀጥል ፍላጎት አላት ብለዋል።

“የኢትዮጵያ ሠራዊት የሰላም አስከባሪ ኃይል ውስጥ እንደማይካተት እና በአገሪቱ እንደማይቆይ ግልጽ ውሳኔ አሳልፈናል” ያሉት ሑሴን አሊ፤ ሶማሊያ የኢትዮጵያ ሠራዊት በአገሪቱ እንዳይቆይ ውሳኔ ያስተላለፈችው በሁለቱ አገራት መካከል በተፈጠረው ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሠራዊት ለአካባቢው አደገኛ ነው ተብሎ የነበረውን የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ቡድንን ዛቻ ተከትሎ ወደ ሶማሊያ ዘልቆ በመግባት የቡድኑን መዋቅር በማፈራረስ ለሶማሊያ መንግሥት መጠናከር ድጋፍ አድርጓል።

ከዚያም በኋላ በአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተልዕኮዎች ስር በመሆን አል ሻባብ በሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ላይ የደቀነውን አደጋ ለመግታት ከፍተኛ ሚና ሲጫወት መቆየቱ ይነገርለታል።

ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚነገርለት አልሻባብ ከሶማሊያ አልፎ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች ጎረቤት አገራትን በጠላትንት የሚመለከት ሲሆን፣ በአንዳንዶቹ ላይ በግዛቶቻቸው ውስጥ የሽብር ጥቃት እስከ መፈጸም ደርሷል።

የኢትዮጵያ እና የሌሎች የአፍሪካ አገራት ሠራዊቶች በሶማሊያ ውስጥ ተሰማርተው የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥትን ባይጠብቁ እና ባያጠናክሩ ኖሮ አል ሻባብ አገሪቱን ለመቆጣጠር የሚያግደው ነገር እንደማይኖር ይታመናል።

ለዚህም ነው ባለፉት ሁለት አስርታት ዓመታት ለሚሆን ጊዜ በሶማሊያ ተሰማርቶ የቆየው የኢትዮጵያ ሠራዊት በአገሪቱ በስፋት የሚንቀሳቀሰውን የአል-ሸባብ ቡድንን ሲዋጋ ቆይቷል።

በቅርቡ የኢትዮጵያ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ለብሔራዊ የቴሌቪዥን ሲናገሩ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የሶማሊያ ግዛት በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሚጠበቅ መሆኑን ተናግረው ነበር።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ “የሶማሊያ መንግሥት ሞቃዲሾ እንዲቀመጥ ያደረገው የኢትዮጵያ መካለከያ ሠራዊት ነው” በማለት “የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ነገ ቢወጣ የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ሞቃዲሾ የሚቀመጥ አይመስለኝም” ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር ወደ ሶማሊያ ከላከቻቸው ወታደሮች በተጨማሪ በሁለቱ አገራት ስምምነት በርካታ የአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በሶማሊያ ተሰማርተው ይገኛሉ።

ይህን የኢትዮጵያ ሠራዊት ከሶማሊያ የማስወጣት ዕቅድን የሶማሊያ ግዛት የሆነችው ሳውዝዌስት ተቃውማለች።

ካርታ

አንዳንዶች ለአል-ቃይዳ አጋርነቱን የገለጸውን አል-ሸባብን ለበርካታ ዓመታት ሲዋጋ የነበረ ኃይል ከአገር ቢወጣ ጸንፈኛው ቡድን የሶማሊያ መንግሥትን ሊያጠቃ ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ጋር በነበራቸው ውይይት ውጥረት በማርገብ የሶማሊያ መንግሥት ትኩረቱን በፀረ ሽብር ተግባራት እና የአትሚስ ተልዕኮ በሚተካበት ዕቅድ ላይ መሆን አለበት ብለዋል።

ኢትዮጵያ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ከሶማሊላንድ ጋር ባለፈው ታኅሣሥ ወር የመግባቢያ ሰነድ ከተፈራረመች በኋላ ሶማሊያ ስምምነቱ ሉዓላዊነቷን የሚጋፋ መሆኑን በመግለጽ ተቃውማ በሁለቱ አገራት መካከል ውዝግብ ተፈጥሮ ቆይቷል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ በተፈራረሙት ስምምነት ላይ ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ አገልግሎት የሚውል 20 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የባሕር ጠረፍ በኪራይ እንደምትሰጥ እና በምላሹም ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ የአገርነት እውቅና ትሰጣለች ተብሎ ነበር።

ነገር ግን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና በሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ቢሂ መካከል ታኅሣሥ 22/2016 ዓ.ም. የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ በአንድ ወር ውስጥ ተግባራዊ ይሆናል ቢባልም፣ የትግበራ ሁኔታውን በተመለከተ አስካሁን ከሁለቱም ወገኖች የተወሰደ ተግባራዊ እርምጃ የለም።

ይህ የኢትዮጵያ እና የሶማሊላንድ ስምምነት የሶማሊያን መንግሥት ከማስቆጣት ባሻገር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን እስከማቋረጥ በሚደርስ ሁኔታ የኢትዮጵያ አምባሳደርን ከሞቃዲሾ አስወጥቷል።

አሁን ደግሞ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር በሶማሊያ ለዓመታት ተሰመርቶ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሠራዊት ከወራት በኋላ ከአገሪቱ እንዲወጣ እንደሚፈልግ አሳውቋል።

በዚህ የሶማሊያ መንግሥት ውሳኔ ላይ የተልዕኮው መሪ የአፍሪካ ኅብረትም ሆነ በተልዕኮው ወታደሮቻቸውን እያሳታፉ ያሉ አገራት አስካሁን ያሉት ነገር የለም።

ነገር ግን በአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ ውስጥ በርካታ ወታደሮችን ያሠማራው የኢትዮጵያ ሠራዊት ሌላ አማራጭ ሳይገኝለት ከሶማሊያ የሚወጣ ከሆነ በአገሪቱ ጉልህ የፀጥታ ክፍተትን ሊፈጥር እንደሚችል ስጋት ፈጥሯል።

ይህ ደግሞ አሁን በአመቺ ሁኔታዎች ሁሉ የሶማሊያ መንግሥት በማጥቃት እና በማዳከም ላይ ለሚገኘው አልሻባብ ቡድን ተጨማሪ ዕድልን ሊፈጥርለት ይችላል እየተባለ ነው።