
ከ 5 ሰአት በፊት
ስፔን “ጎልደን ቪዛ” የተባለውን ፕሮግራሟን ልታቋርጥ እያቀደች ነው። ይህ ቪዛ ጠብሰቅ ያለ ገንዘብ ይዘው መጥተው መዋዕለ ንዋያቸውን ለሚያፈሱ አውሮፓውያን ላልሆኑ ሰዎች የሚሰጥ ነው።
ስፔን ብቻ ሳትሆን ሌሎችም አገራት ይህን ፕሮግራም እያቋረጡ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ይህን ፕሮግራም ለምን ማቋረጥ እንደፈለጉ ሲናገሩ “ቤት ማግኘት መብት ሊሆን ይገባል እንጂ ቢዝነስ አይደለም” ይላሉ።
አክለው “የመኖሪያ ቤት ዘርፉ ከባድ ጫና ላይ ነው። በተለይ ደግሞ ጥረው ግረው ለሚገቡ ሰዎች ቤት መግዛት የማይታሰብ ሆኗል” ይላሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
በርካታ ኢንቨስተሮች “ጎልደን ቪዛን” ተጠቅመው አዲስ ሕይወት ይጀምራሉ። አሊያም ከአገራቸው በፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ ጫና አምልጠው ለመውጣት ይጠቀሙበታል።
ነገር ግን የፀረ-ሙስና አቀንቃኞች እና ፖለቲከኞች፤ ወንጀለኞች ይህን ቪዛ ተጠቅመው እየመጡ የቤት ዋጋን በማስወደድ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ፈተና እየሆኑ ነው ይላሉ።
‘ጎልደን ቪዛ’ ወይም ‘ጎልደን ፓስፖርት’ ምንድነው?
ጎልደን ቪዛ የሚባለው ፕሮግራም ለውጭ አገር ሰዎች የሚሰጥ ቪዛ ሲሆን፣ ቪዛው የሚሰጠው መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ለሚችሉ ባለጸጎች ነው።
ይህን ቪዛ ለማግኘት የሚከፈለው ገንዘብ ይለያያል። ለምሳሌ ፓናማ ይህን ቪዛ ለማግኘት በሪል ስቴት ኢንዱስትሪ 100 ሺህ ዶላር ኢንቨስት ማድረግን ትጠይቃለች። ለግዘምበርግ ደግሞ እስከ 21.4 ሚሊዮን ዶላር ተቀማጭ ገንዘብ በአገሪቱ የገንዘብ ተቋማት ማስቀመጠን ትጠይቃለች።
ጎልደን ፓስፖርት ደግሞ ለሀብታም ሰዎች የሚሰጥ ፓስፖርት ሲሆን፣ እኒህ ግለሰቦች ይህን ቪዛ በምትሰጣቸው አገር የመሥራት መብት እንዲሁም የመምረጥ ነፃነት ሊሰጣቸው ይችላል።
- ኬንያ ከአዲሱ አሠራሯ ውጪ ኢትዮጵያውያን ያለክፍያ ወደ አገሯ እንዲገቡ ፈቀደች19 የካቲት 2024
- በርካታ አገራትን ያለ ቪዛ ማሻገር የሚያስችሉ ፓስፖርቶች ያሏቸው አገራት ይፋ ሆኑ11 ጥር 2023
- እንግሊዝ አጭበርባሪ ባለሀብቶችን ቪዛ ልትከለክል ነው6 ታህሳስ 2018

የትኞቹ አገራት ታዋቂ ናቸው?
ጎልደን ቪዛን በተለመለከተ መፅሐፍ ያሳተሙት የለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ክሪስቲን ሱራክ 60 የሚሆኑ አገራት ጎልደን ቪዛ ይሰጣሉ ይላሉ።
ፕሮፌሰሯ አክለው 20 አገራት ኢንቨስት ላደረጉ ሰዎች ዜግነት እንደሚሰጡ፤ ግማሽ ያህሉ ደግሞ በየዓመቱ 100 ሰዎች እንደሚቀበሉ ይናገራሉ።
“ቱርክ የዜግነት ሽያጭ ቀንደኛ አገር ናት” የሚሉት ክሪስቲን፤ በየዓመቱ ከሚሸጡ ዜግነቶች መካከል ግማሽ ያህሉ የቱርክ እንደሆኑ ለቢቢሲ ይናገራሉ።
እሳቸው እንደሚሉት ኢንቨስት ላደረጉ ሰዎች የመኖሪያ ፈቃድ ከሚሰጡ አገራት መካከል ማሌዢያ እና ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ የሚጠቀሱ ናቸው።
ሴይንት ኪትስ፣ ዶሚኒካ፣ ቫኑዋቱ፣ ግሬናዳ፣ አንቲጉዋ እና ማልታ ጎልደን ፓስርፖርት በመስጠት የሚታወቁ አገራት ናቸው።
ጎልደን ቪዛ ለሚፈልጉ ሰዎች ተመራጩ ሥፍራ አውሮፓ ነው። ለዚህ ዋነኛው ምክንያት የአውሮፓ ኅብረት አባል ከሆነች አገር ቪዛ ማግኘት ማለተ የሸንገን አካባቢ በሚባሉ አገራት ውስጥ በነፃነት መንቀሳቀስ ስለሚፈቅድ ነው።
በአውሮፓውያኑ 2020 ከአውሮፓ ኅብረት አገራት 14 የሚሆኑት ጎልደን ቪዛ ይሰጡ ነበር። ግሪክ፣ ላትቪያ፣ ፖርቹጋል እና ስፔን 70 በመቶ ያህሉን ድርሻ ይወስዳሉ። ነገር ግን አሁን አብዛኞቹ አገራት ይህን ፕሮግራም ገታ በማድረግ ላይ ናቸው።
በ2022 በዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ንብረት ለሚገዙ ሀብታም የውጭ አገር ዜጎች ይሰጥ የነበረውን የመኖሪያ ፈቃድ ማቆሙን ገልጧል።
በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ አየርላንድ በተመሳሳይ ይህን ፕሮግራሟን ማቋረጧን አሳውቃለች። ፖርቹጋል ሙሉ በሙሉ ባታቆምም፣ ከዚህ ቀደም ንብረት ለገዛ የነበው አሁን ካፒታል ማስተላለፍ ለሚችል እና በጥናት እና በምርምር ላይ ኢንቨስት ለሚያደርግ በሚል ተቀይሯል።

ለምን ተመራጭ ሆኑ?
ጎልደን ቪዛ እና ፓስፖርት ገንዘብ ላላቸው ሰዎች ተመራጭ ናቸው። እኒህ ሰዎች የተሻለ ቢዝነስ ለመሥራት አሊያም አዲስ ሕይወት ለመጀመር ነው ቪዛውን የሚፈለጉት።
“ባለንበት ብዙ ነገሮች እርግጠኛ ባልሆኑበት ዓለም ሁለተኛ መኖሪያ ፈቃድ፣ አሊያም ፓስፖርት ማግኘት ከምንጊዜውም በላይ ጨምሯል” ይላሉ ላ ቪዳ ጎልደን ቪዛስ የተባለ ኩባንያ የማርኬቲንግ ኃላፊ የሆኑት ሊዚ ኤድዋርድስ።
“የኢንቨስተሮች ምክንያት የተለያየ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ብዙውን ጊዜ ምክንያት ደኅንነት፣ የተሻለ ቪዛ ማግኘት እና ዓለም አቀፍ ዕድልን ማስፋት ነው።”
ጎልደን ቪዛ እንዴት ይገኛል?
ሕጉ ጎልደን ቪዛውን አንደሚሰጠው አገር ሊለያይ ይችላል። ለምሳሌ ቱርክ 400 ሺህ ዶላር እና ከዚያ በላይ አውጥተው ሪል ስቴት ለሚገዙ ሰዎች ጎልደን ፓስፖርት ትሰጣለች።
እንደ ለግዘምበርግ ያሉ አገራት ደግሞ የተለያዩ አማራጮች አሏቸው። አንደኛው አማራጭ ለግዘምበርግ ያለ ኩባንያ ላይ ቢያንስ 536 ሺህ ዶላር ኢንቨስት ማድረግ ሲሆን፣ ሌላኛው አማራጭ ደግሞ 21.4 ሚሊዮን ዶላር ተቀማጭ ማድረግ ነው።
ብዙ አገራት በተራድዖ፣ በጥናት እና በምርምር ላይ ኢንቨስት ማድረግን ለጎልደን ቪዛ ማሟያነት ይቀበላሉ።
ጎልደን ቪዛ የሚሰጡ አገራት ይህን የሚያደርጉበት ዋነኛው ምክንያት ካፒታል ወደ አገራቸው እንዲመጣ ማድረግ እና ምጣኔ ሀብታቸውን ማሳደግ ነው።
ዶ/ር ክሪስቲን ያሳተሙት አንድ የጥናት ፅሑፍ እንደሚጠቁመው ከ2013 እስከ 2019 ባለው ጊዜ 14.4 በመቶ የሚሆነው የፖርቹጋል ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት የመጣው ከጎልደን ቪዛ ነው። በተመሳሳይ ጊዜ ላትቪያ 12.2 በመቶ ግሪክ ደግሞ 7 በመቶ አስመዝግበዋል።

ለምን አነጋጋሪ ሆኑ?
ይህ ቪዛ እንዲቆም የሚጠይቁ ሰዎች ሁለት ጉዳዮች ያነሳሉ፤ ሙስና እና ቪዛውን በሚሰጠው አገር ዜጋ ላይ የመኖሪያ ቤት ዋጋ መናር በመከሰቱ ነው።
ትራንስፓረንሲ ኢንትርናሽናል የተባለው ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ሙስና ላይ የሚሠራ ደርጅት በተለይ በአውሮፓ የፕሮግራሙ ዓላማ “ኢንቨስትመንት ወይም ስደት አይደለም” ሲል አስጠንቅቆ ነበር።
በ2022 የአውሮፓ ኅብረት ኮሚቴ የኅብረቱ አገራት ጎልደን ፓስፖርት መስጠት እንዲያቆሙ የሚያደርግ አዋጅ አፅድቋል።
ክሪስቲን እንደሚሉተ ይህን ፕሮግራም ተጠቅሞ ገንዘብ በሕገ-ወጥ መልኩ ማስተላለፍ ቢቻልም “ሌሎች ቀለል ያሉ አማራጮች” አሉ።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት የወጣ አንድ ዘገባ እንደሚጠቁመው፣ የቀድሞ የሊቢያ ኮሎኔል እና ቱርክ ውስጥ እሥር የተፈረደበት ቱርካዊ ባለሀብት የዶሚኒካን ፓስፖርት መግዛት ችለዋል።
በተመሳሳይ ባለፈው ዓመት የዩናይትድ ኪንግደም የአገር ውስጥ ጉዳይ መሥሪያ ቤት (ሆም ኦፊስ) ባወጣው ዘገባ “ጥቂት የውጭ አገር ኢንቨስተሮች” ከሙስና እና ከወንጀለኛ ቡድኖች ጋር ግንኙነት ሳይኖራቸው አይቀርም” ብሏል።
ሁለተኛው ምክንያት የቤት ዋጋ መናር ነው። አብዛኞቹ አገራት ጎልደን ቪዛ ለማግኘት ሪል ስቴት መግዛትን ይጠይቃሉ። ይህ ደግሞ የመኖሪያ ቤት ዋጋን ከፍ ያደርገዋል።
የዶ/ር ክሪስቲን ጥናት ግን ጎልደን ቪዛ የመኖሪያ ቤት ዋጋ ያለው ተፅዕኖ አነስተኛ ነው ይላል። ለምሳሌ ስፔን በአንድ ዓመት 2 ሺህ ጎልደን ቪዛ ጠያቂያዎች ትቀበላለች። 48 ሚሊዮን ሕዝብ ላላት አገር 2 ሺህ ትንሽ ቁጥር ነው።
ቢሆንም ብዙውን ጊዜ ሪል ስቴት የሚገዙት በጣም ተፈላጊ በሚባሉ ቦታዎች ሲሆን፣ በእነዚህ አካባቢዎች ያለው የቤት ዋጋ መናሩ አይቀርም።
በደቡባዊ የቱርክ ክፍል የምትገኘው አንታልያ አንዷ ናት። አንታልያ በሩሲያውያን እና በዩክሬናውያን ጎብኝዎች ዘንድ ታዋቂ ናት። ከጦርነቱ በኋላ የከተማዋ የመኖሪያ ዋጋ እየጨመረ እንደመጣ የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ።