የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ

ከ 2 ሰአት በፊት

በጀርመን አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ የብሔራዊ ቡድኑን ተጫዎች ዘር በተመለከተ የሠራውን ጥናት የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ጁልያን ናገልስማን “ዘረኛ” ነው ሲሉ አውግዘውታል።

ኤአርዲ በተባላ የቴሌቪዥን ጣቢያ የተጀራው የዳሰሳ ጥናት ተሳታፊዎቹን በአገሪቱ ብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ ነጭ ተጫዋቾች በርከት ብለው እንዲታዩ ይፈልጉ እንደሆነ የሚጠይቅ ነው። በዚህ ጥናት ከተሳታፉት 21 በመቶ የሚሆኑት “ተጨማሪ ነጭ ተጫዋቾችን ማየት እንፈልጋለን” ብለዋል።

“ጥናቱ ዘረኛ ነው። መንቃት እንዳለብን ይሰማኛል” ብለዋል ዋና አሠልጣኙ ናገልስማን።

የጀርመን ብሔራዊ ቡድን የአማካኝ ተጫዋቹ ጆሽዋ ኪሚቺ መጠይቁን “ዘረኛ ነው” ሲል ገልጾት የነበረ ሲሆን፣ እሱ ይህንን ካለ ከአንድ ቀን በኋላ የ36 ዓመቱ ዋና አሠልጣኝ በሀሳቡ እንደሚስማሙ ገልጸዋል።

“ጆሽ በማያሻማ እና በጣም በጥሩ ሁኔታ ነው ምላሽ የሰጠው” ሲሉ የተናገሩት አሠልጣኙ “እኔም ያለምንም ልዩነት በተመሳሳይ መንገድ ነው የምረዳው። ጥያቄው አላስፈላጊ ነው” ብሏል።

ጨምሮም በጦርነት፣ በኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች፣ በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ብዙ ሰዎች ወደ አውሮፓ የግድ መምጣት ነበረባቸው ሲል ገልጿል።

በዚህም ምክንያት ይህን መሰሉን ተግባር ማድረግ ስህተት እና ያልተገባ እንደሆነ ጠቅሷል።

መጠይቁን ያቀረበው ኤአርዲ ወይም የጀርመን ‘ፐብሊክ’ ብሮድካስት የተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ የዳሰሳ ጥናቱ የተዘጋጀው እግር ኳስ እና ብዝኃነት ለተሰኘ ዘጋቢ ፊልም ግብዓት እንደሆነ ገልጿል። ጨምሮም በተደጋጋሚ ከሚጠየቀው የእግር ኳስ ቡድኑ የቀለም ብዝኃነትን የሚለካ መረጃ ለማዘጋጀት እንደሆነ አሳውቋል።

ይህን ጥያቄ የያዘው መጠይቅ በዘፈቀደ (randomly) ለተገኙ 1304 ተሳታፊዎች ተሠራጭቷል።

መጠየቁን ያዘጋጀው የቴሌቪዥን ጣቢያው የስፖርት ክፍል ኃላፊ ካርል ቫልክስ ውጤቱ የታየውን ቢመስልም በጀርመን አሁን ያለውን የሕብረተሰብ ፍላጎት ማሳያ ነው ብለዋል።

ጨምረውም ስፖርት በሕበረተሰቡ ውስጥ ትልቅ ሚና ይጫውታል ካሉ በኋላ፣ የኅብረት ምሳሌ ነው ብለው ስለመናገራቸው ተዘግቧል።

ኃላፊው የአሁኑ ቡድን አምበሉን ኢልኬ ጉንዶዋን እና የክንፍ መስመር ተጨዋቹን ሌሮይ ሳኔን ጨምሮ የተለያየ የቤተሰብ የኋላ ታሪክ ያላቸው በርካታ ተጨዋቾቸን የያዘ ነው ብለዋል።

ጀርመን ሰኔ 7/2016 ዓ.ም. የሚጀመረውን የዘንደሮ የአውሮፓ ዋንጫ የምታስተናግድ ሲሆን፣ የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ቡድናቸው ለሁሉም ዜጋ ይጨዋታል ብለዋል።

በዳሰሳ ጥናቱ ምክንያት ውዝግብ ከመነሳቱ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ የስፖርት ትጥቅ አምራቹ አዲዳስ ይፋ ያደረገው መለያ ውዝግብ አስነስቶ ጫና ከደረሰበት በኋላ እንዳይሸጥ ተደርጓል።

መለያው 44 ቁጥር በሚሰፍርበት ጊዜ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ግፍ በመፈጸም የሚታወቀውን ኤስኤስ የተባለውን የናዚ ኃይል አርማ ጋር በመመሳሰሉ ምክንያት ነበር ውዝግብ የተነሳው።

ኤስኤስ ናዚ በሰብአዊነት ላይ ለፈጸማቸው አብዛኞቹ ወንጀሎች ተጠያቂ እንደሆነ ሲገለጽ ቆይቷል።