

ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. ሕወሓት መራሹ ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ከነበሩ ገጽታዎች በከፊል
June 2, 2024
ግንቦት 20 ዘንድሮ የውዝግብ ርዕስ ሆኖ ነው ያለፈው፡፡ በኢሕአዴግ ዘመን በአዋጅ በተደነገገ ሁኔታ ሕግና ሥርዓት ተበጅቶለት የሚከበር ባይሆንም፣ ግንቦት 20 ድምቀት አጥቶ የማያውቅ በዓል ነበር፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ ያመጣ ቀን ተብሎ በኢሕአዴግ ዘመን እንደ ትልቅ የድል በዓል ሲከበር መቆየቱ የቅርብ ዘመን ትውስታ ነው፡፡

ኢሕአዴግ በትጥቅ ትግል ጠንካራውን አምባገነናዊ ወታደራዊ አገዛዝ ደርግን ጣልኩበት የሚልበትን ግንቦት 20 ብቻ ሳይሆን፣ የግንባሩ ድርጅቶች መመሥረቻ ቀናትንም በትልቁ እየደገሰ ሲያከብር ይታወቃል፡፡
ሕወሓት የተመሠረተበት የካቲት 11 ቀን ከመቀሌ እስከ አዲስ አበባ በልዩ ልዩ ሥነ ሥርዓት ሲከበር ነበር፡፡ በተጨማሪም ብአዴን፣ ኦሕዴድና ደኢሕዴንም የምሥረታ ቀኖቻቸውን በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲያከብሩ ይታወቃሉ፡፡ ኢሕአዴግ ጊዜው ደርሶ ከቦታው ገለል ሲልና የብልፅግና መንግሥት ኢትዮጵያን መምራት ሲጀምር ግን፣ እንኳን የግንባሩ ድርጅቶች ቀን ይቅርና ልዩ ቦታ ይሰጠው የነበረው የግንቦት 20 ቀንም እንደ በዓል መታየቱ ይደበዝዝ ጀመር፡፡
ግንቦት 20 በኢሕአዴግ ዘመን እንደነበረው በዘፈቀደ ሳይሆን ሕግና ሥርዓት ተበጅቶለት በወጉ እንዲከበር የሚጠይቁ ድምፆች ለረዥም ጊዜ ሲሰሙ ቆይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ኢሕአዴግ ይህን ሥርዓት ሳያበጅ ነው ያለፈው፡፡ በኢሕአዴግ እግር የተተካው የብልፅግና መንግሥት በንጉሡ ዘመን የወጣውን ‹‹የሕዝብ በዓላትና የእረፍት ቀናት አዋጅ ቁጥር 15/1967›› እንጂሻሻል የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቷል፡፡ ዘንድሮ ታኅሳስ ለተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ‹‹የሕዝብ በዓላትን እና የበዓላትን አከባበር ለመወሰን የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ቁጥር …….2016›› ግንቦት 20ን በሚመለከት ሕዝባዊ በዓል መሆኑን ሳይደነግግ አልፎታል፡፡
የግንቦት 20 በዓልን በተመለከተ አገሪቱ ስትከተል የመጣችው የአከባበር ሥርዓት የተዘበራረቀ ሆኖ ነው ለረዥም ጊዜ የዘለቀው፡፡ ግንቦት 20 ትልቅ መስዋዕት የተከፈለበት ቀን አድርጎ የሚያስታውሰው እንዳለ ሁሉ በተቃራኒው አገሪቱን የሰዋ ቀን አድርጎ የሚቆጥሩ ብዙ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን የተጎናፀፈችበት፣ ዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊ ሥርዓት የዘረጋችበት፣ ዜጎች ከማንነት ጭቆና ነፃ የወጡበት ቀን ነው ብለው ግንቦት 20ን የሚያከብሩት ወገኖች አሉ፡፡
በተቃራኒው ግን ግንቦት 20 የኢትዮጵያ አንድነት በማንነት ፖለቲካ ክፍፍል ውስጥ እንዲወድቅ ያደረገ ቀን ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ግንቦት 20 ፌዴራላዊ ሥርዓት ሳይሆን የቋንቋና የብሔር ፖለቲካ ሽንሸና የተካሄደበት፣ ኢትዮጵያ የባህር በር አጥታ ባዶ እጇን የቀረችበት፣ አገራዊ አንድነቷ የተሸረሸረበትና የተናጋበት ዕለት ነው ብለው ቀኑን የሚረግሙትና የሚጠሉት መኖራቸውን መካድም ፈጽሞ አይቻልም የሚሉም አሉ፡፡
ግንቦት 20 ይህን ያህል ፍፁም የሚቃረን ልዩነት ለምን ፈጠረ ለሚለው ጥያቄ በርካቶች ቀኑ በዘፈቀደ እንጂ በሕግና በሥርዓት ሲከበር አለመቆየቱ ትልቅ ችግር እንደፈጠረ ያወሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ ግንቦት 20 ሕዝባዊ በዓል ስለመሆኑ በሕግና በአዋጅ የተደነገገም ቢሆን እንኳን፣ በዓሉን በተመለከተ ያለው ልዩነት ይረግብ ነበር ወይ የሚለው ጉዳይ ደግሞ አሁንም ያከራክራል፡፡
በርካታ ወገኖች በሕዝባዊ በዓላት ላይ ያለው ውዝግብ መነሻ ሕግ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ አለመሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ከእነዚህ ወገኖች አንዱ የሆኑት አየለ በከሪ (ፕሮፌሰር) ሕዝባዊ በዓላት በመጡ ቁጥር፣ በኢትዮጵያ ፅንፍ የወጣ ልዩነትና ሽኩቻ እየተለመደ ስለመምጣቱ ነው የሚናገሩት፡፡
በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ባህል የራስን የማዋደድ (ሠልፍ ሴንተርድ) ነው የሚሉት አየለ (ፕሮፌሰር)፣ በቀደመው ዘመን ትልቅ ቦታና ግምት የሚሰጣቸው ጉዳዮች በቦታው የሚተካው ተከታይ ሲመጣ እንዲረሱ ማድረጉ የተለመደ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹አዲሱ የቀደመውን ማንኳሰሱና ማንቋሸሹ የተለመደ፣ ነገር ግን መጥፎ የፖለቲካ ባህል ነው፤›› ሲሉ ይገልጹታል፡፡ ግንቦት 20ም የዚሁ ፖለቲካ ሰለባ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
ፕሮፌሰሩ ሲቀጥሉ፣ ‹‹ግንቦት 20 ብቻ እኮ አይደለም ልክ እንደ አላስፈላጊ ነገር የተጣለው፡፡ መታሰቢያ በዓል የሚባለው ነገር ያመናል መሰለኝ አሁን አሁን የካቲት 12ትም ብዙም አይታሰብም፡፡ በእኛ ጊዜ የካቲት 12 ትልቅ ብሔራዊ በዓል ነበር፡፡ ደርግ ሲመጣ በኃይለ ሥላሴ ዘመን ይከበሩ የነበሩትን የዘውድና የልደት በዓሎችን ሰረዘ፡፡ ወያኔ በደርግ ቦታ ሲመጣ ደግሞ የደርግ በዓላትን ውድቅ አደረጋቸው፡፡ አሁን ያለው የብልፅግና መንግሥት ደግሞ የቀድሞውን የኢሕአዴግ ግንቦት 20 ወደ ጎን ብሎታል፡፡ በዚህ መንገድ ከቀጠልን አገራዊ ትውስታ ቀጣይነት እንዳይኖረው ከማድረግ ባለፈ አገራዊ መግባባት ለመፍጠርም እንቸገራለን፡፡ አንዱ ሌላውን የማጥፋት ባህል ፈጥረናል፡፡ ከዚያ በከፋ ደግሞ በኔጌቲቭ የማብዛት አካሄድ እንከተላለን፡፡ የዘንድሮ ግንቦት 20 ይከበራል አይከበርም የሚለውን እንኳን ለማወቅ ተቸግረን ነበር፡፡ እኔ ባለሁበት አካባቢ ብዙ ሰዎች ሥራ አልሄዱም፣ ከትምህርታቸው የቀሩ ልጆችም ብዙ ናቸው፡፡ መጨረሻ ላይ በዋዜማው ወደ ማታ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ትምህርትም ሥራም እንዳለ መግለጫ መስጠቱና የተወሰኑ ሥራዎች ክፍት እንደሚሆኑ መግለጹ ካልሆነ በስተቀር፣ በዓሉ ይከበር አይከበር ያወቅንበት መንገድ እንኳን አልነበርም፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡
በብልፅግና መንግሥት ዘመን የሚሰጠው ትኩረትና ድምቀት የቀነሰው ግንቦት 20 ዘንድሮ በአሜሪካ ኤምባሲና በአሜሪካ ፖለቲከኞች ትኩረት ሲያገኝ ታይቷል፡፡ የአሜሪካ ኤምባሲ ዓርብ ባወጣው መግለጫ ነበር ሰኞ የሚሞሪያል ዴይ በዓል፣ እንዲሁም ማክሰኞ በግንቦት 20 በዓል የተነሳ ኤምባሲው ለሁለት ቀናት እንደሚዘጋና አገልግሎት እንደማይሰጥ አስቀድሞ ማስታወቁ አስገርሞ ነበር፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን ለበዓሉ ትልቅ ትኩረት በመስጠት የደስታ መግለጫ ማስተላለፋቸው ብዙዎችን ያነጋገረ ነበር፡፡ እንደ ቲቦር ናዥ ያሉ የቀድሞ ዲፕሎማቶችም የደስታ መልዕክት ሲያስተላልፉ ታይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ የአሜሪካ ኤምባሲ ከወትሮው በተለየ መንገድ ከሚሞሪያል ዴይ ጋር አገናኝቶ ሥራ እንደሚዘጋ መግለጫ ማውጣቱ ያልተለመደና አነጋጋሪ ሆኖ ነበር፡፡
የሕግ ባለሙያው አቶ አንዷለም በዕውቀቱ የግንቦት 20 አከባበር የሚያወዛግበው፣ ‹‹በዓሉ በዘልማድ እንጂ በሕግ ብሔራዊ በዓል ተብሎ ባለመታወጁ›› እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በኢትዮጵያ በዓላትን ለመደንገግ የወጡ ሕጎች መኖራቸውን የሚጠቁሙት አቶ አንዷለም የመጀመሪያው በ1948 የወጣ አዋጅ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹ይህ ሕግ በዘመኑ የሃይማኖትና የመንግሥት የመነጣጠል መርህ የተከበረ ስላልነበር እሑድ ቀንን ጭምር የበዓል ቀን አድርጎ የደነገገ ነበር፡፡ ቀጥሎ የወጣው አዋጅ ቁጥር 16/1967 ይህን የሻረ ሲሆን፣ አሁንም ድረስ የሚከበሩ ሃይማኖታዊና ሕዝባዊ በዓላትን፣ እንዲሁም ታስበው የሚውሉ ቀናት የደነገገው ይኼው ሕግ ነው፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ቀጥሎ የወጣው ደግሞ የኢሕአዴግ ዘመኑ አዋጅ ቁጥር 25/1988 አዋጅ መሆኑን የሚናገሩት የሕግ ባለሙያው፣ ይህ አዋጅ ግን አንድ የሕግ አንቀጽን ብቻ ያሻሻለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹የ1988 አዋጅ የደርግ መንግሥት ወደ መጋቢት 28 ወስዶት የነበረውን የአርበኞች የድል በዓልን ቀድሞ ወደ የሚከበርበት ሚያዝያ 27 የመለሰ ነበር፤›› በማለትም ጠቁመዋል፡፡
አቶ አንዷለም ሲቀጥሉ ግንቦት 20 በአገር አቀፍ ደረጃ ብሔራዊ በዓል ሆኖ እንዲከበር አዋጅ ካለመውጣቱ በተጨማሪም፣ በጉዳዩ ላይ መግባባትም እንደሌለ ገልጸዋል፡፡
‹‹ግንቦት 20 ያስገኘው በጎ ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ በዚያ ለውጥ መጣልኝ ብሎ የሚያስብ ማኅበረሰብ ሊኖር ይችላል፡፡ ሆኖም ቀኑ የእርስ በእርስ ግጭት ያበቃበት ቀን እንጂ የድል በዓል ተብሎ በጭፈራ መከበር የለበትም፡፡ የደርግ ሠራዊት ተብሎ ሜዳ ላይ የተበተነ ወገን አለ፡፡ እስካሁንም ዕምባቸው ያልደረቀና ልጆቻቸውን ያልቀበሩ እናቶች አሉ፡፡ ግንቦት 20ን ልክ እንደ ዓድዋ በጭፈራ የምታከብረው አይደለም፡፡ እኔ ለምሳሌ አንዱ ቤተሰቤ ሞቶብኛል፣ ሌላኛው ቤተሰቤ ደግሞ ታስሮብኛል፡፡ ስለዚህ ግንቦት 20ን የማከብርበት ምክንያት የለኝም፤›› በማለት ነው ያስረዱት፡፡
‹‹ኢትዮ ሎው›› በተባለ የሕግ ባለሙያዎች ሐሳብ በሚያጋሩበት ማኅበራዊ ዓምድ ላይ ስለብሔራዊ በዓላት ምጥን መጣጥፍ ያጋሩት አቶ አብረሃም ዮሐንስ፣ ከ195 የዓለም አገሮች መካከል ኢራን 30 የሕዝብ በዓላት በመያዝ አንደኛ ደረጃን እንደያዘች ገልጸዋል፡፡ አዘርንባጃ፣ ቡልጋሪያና ማሌዥያ 19 በዓላትን ይዘው በሁለተኝነት መቀመጣቸውን ጠቅሰዋል፡፡ አሜሪካ አሥር በዓላት እንዳሏትና ኖርዌይ ደግሞ ሁለት በዓላት ብቻ ይዛ ከዓለም በደረጃ መጨረሻ ላይ እንደምትገኝ ጠቁመዋል፡፡ የኢትዮጵያን በተመለከተ 13 በዓላት እንዳላት የጠቀሱ ሲሆን፣ በሕግ የሚታወቁ የሕዝብ በዓላት ቢኖሩም በሕጉና በአተገባበሩ መካከል ልዩነት መኖሩን ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡
ደርግ ወደ ሥልጣን የመጣበትን መስከረም 2 ቀን ‹‹የሕዝብ ንቅናቄ (ሪቮሉሹን) ቀን መታሰቢያ›› ብሎ በሕግ ደንግጎ ያከብረው ነበር፡፡ ኢሕአዴግ በበኩሉ ግንቦት 20 ቀንን ‹‹ደርግ የወደቀበት (የተደመሰሰበት) ቀን›› በሚል ስም በሕግ ሳይደነግግ ያከብረው ነበር፡፡ በኢሕአዴግ ዘመን ከግንቦት 20 በተጨማሪም ኅዳር 29 ቀን ‹‹የብሔር ብሔረሰቦች ቀን›› እየተባለ በሕግ ሳይደነገግ ይከበር እንደነበር ጸሐፊው ገልጸዋል፡፡ ይህ የሕዝባዊ በዓላት አሰያየምና አከባበር በአዋጅ ያልተደገፈ መሆኑንም እኚሁ ጸሐፊ አውስተዋል፡፡
ይህን የሚያጠናክር ሐሳብ የሚሰጡት የሕግ ባለሙያው አቶ አንዷለም በበኩላቸው፣ በጊዜ ዑደት በዓልነታቸው ወይም መከበራቸው የቀረ በዓላት መኖራቸውን ያስረዳሉ፡፡ ‹‹መስከረም አንድ ዘመን መለወጫ ብቻ ሳይሆን ኤርትራ ወደ እናት አገሯ የተቀላቀለችበት ቀን ተብሎም ይታሰብ ነበር፡፡ አሁን ኤርትራ ነፃ አገር ሆና የራሷን የነፃነት ቀን ታከብራለች፡፡ እኛ ይህን በዓል በሕግ ብንሽረውም በተግባር ግን ዘመን መለወጫን ብቻ እንጂ አናከብረውም፡፡ መስከረም ሁለት የሕዝባዊ ንቅናቄ (ሪቮሉሹን ቀን) ተብሎ ሲከበር ቢቆይም ኢሕአዴግ ሲመጣ ግን ቆሟል፡፡ በዓሉ በሕግ እንዳይከበር ግን አልተሻረም፡፡ አንድ ሰው መስከረም ሁለት በዓል ስለሆነ ሥራ አልገባም ብሎ ፍርድ ቤት ቢከራከር ሕጉ ይደግፈዋል፡፡ መስከረም ሁለት በዓል እንጂ የሥራ ቀን አይደለም፡፡ ሃይማኖታዊ በዓላትን በተመለከተ በሥራ ላይ ያለው ሕግ የፍልሰታ ፆም ፍቺ በዓልን ቀንሶ አምስት የክርስቲያን፣ እንዲሁም ሦስት የሙስሊም በዓላትን የሚደነግግ ነው፤›› ሲሉ የሕጉን የበዓላት አሠራር አስረድተዋል፡፡
አቶ አንዷለም ሲቀጥሉም ከሰሞኑ ሰዎች ግንቦት 20 ሥራ ተዘግቶ ይውላል አይውልም ብለው ግራ በተጋቡ ሰዓት፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ያወጣው መግለጫ ስህተት ነው ይላሉ፡፡ አዲሱ የበዓላት አከባበር አዋጅ ቢዘጋጅም ገና ፀድቆ በሥራ ላይ ስላልዋለ ሥራ አይዘጋም ማለቱ አላስፈላጊ እንደነበር ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹ግንቦት 20 ሕዝባዊ በዓል ነው የሚል አዋጅ የለም፡፡ ስለዚህ የሌለ ሕግን ለመሻር አዋጅ አታወጣም፡፡ መተው ነው የሚያስፈልገው፡፡ ለወትሮም ግንቦት 20 በሕግ ሳይሆን በማናለብኝነት ነው ሲከበር የነበረው፡፡ ስለዚህ ይህን የሚሽር ሕግ አያስፈልግም፤›› ብለዋል፡፡
የዘንድሮው ግንቦት 20 አከባበር ተንተርሶ በሕዝባዊ በዓላት አከባበር ዙሪያ የሚነሳው ክርክርና ውዝግብ ብዙ ዓይነት ገጽታ ያለው ነው የሚመስለው፡፡ የፖለቲከኞችና የፖለቲካ ሥርዓት መፈራረቅ በኢትዮጵያ ለሕዝባዊ በዓላት የሚሰጠውን ቦታና ትኩረት የሚወስን ቁልፍ ጉዳይ መሆኑ ግን ከሁሉም ወገን በሰፊው ሲነሳ ሰንብቷል፡፡ ግንቦት 20 የኢኮኖሚ ልማት ያበበበት፣ የብሔር ነፃነነት የተከበረበት፣ እንደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ያሉ ፕሮጀክቶች መጀመርን ያስከተለ ተፅዕኖ የነበረው ነው ሲሉ ቀኑን ሊየጎሉት የሞከሩ ወገኖች ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ በተቃራኒው ግንቦት 20 በኢትዮጵያ የሉዓላዊነት፣ የአንድነትና የአገራዊ ህልውና መሠረት አደጋ ላይ የወደቀበት ዕለት ስለመሆኑ የሞገቱ ወገኖችም መኖራቸው ይገለጻል፡፡
የታሪክ ምሁሩ አየለ (ፕሮፌሰር) ግንቦት 20 በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ የመጣበትና ቀኑን ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ወገኖች መኖራቸው መረሳት እንደሌለበት ይናገራሉ፡፡ ‹‹ለምሳሌ ከሰሞኑ ጄኔራል ባጫ ደበሌ የዛሬ ዓመት የኤርትራ የነፃነት ቀንን በኬንያ ኤርትራዊያን ሲያከብሩ ተገኝተው የጨፈሩበት ቪዲዮን በማኅበራዊ ሚዲያ ተለቆ አይቻለሁ፡፡ በአንድ ወቅት ጄኔራሉ ከኤርትራ ጋር በተደረገ ጦርነት የተዋጉ ቢሆንም፣ በነፃነነት በዓላቸው አሁን ሲጨፍሩ ማየቱ ደግሞ የጊዜውን ተለዋዋጭነት ያመላክታል፡፡ አንዳንዴ ብንቃወመውና ብንጠላውም እንኳን አንድን ጉዳይ በሌሎች ጫማ ውስጥ ሆኖ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ግንቦት 20 የማያስፈልግ በዓል ነው ከተባለ እንኳን ይህንኑ ጉዳይ ለሕዝብ ማስረዳት በወጉና በሥርዓቱ ጉዳዩን ዕልባት መስጠት ያስፈልጋል፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የሕግ ባለሙያው መንግሥታት በተለዋወጡ ቁጥር ወደ ሥልጣን የመጡባቸውን ወይም ደስ ያላቸውን ቀን በዓል ለማድረግ መሞከራቸው ትልቅ ችግር መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ግንቦት 20ም አከባበሩ ይህን ዓይነት መልክ እንደነበረው ይናገራሉ፡፡ ‹‹የእርስ በርስ ጦርነት የተደረገበት እንጂ፣ የውጭ ወራሪ ወይም ጠላት የተሸነፈበት አይደለም፡፡ በእኔ እምነት አገሪቱ ከእርስ በርስ ዕልቂት የወጣችበትና ስህተቱ የቆመበት ቀን ተብሎ በሐዘን መከበር የነበረበት እንጂ እንደ ዓድዋ በጭፈራ መከበር አልነበረበትም፡፡ ግንቦት 20 የድል በዓሌ ነው ብሎ አንዱ በአሸናፊነት ስሜት ማክበሩ በሌላው ወገን ላይ ግን የተሸናፊነትና የተበዳይነት ስሜት የሚፈጥር ነው፡፡ መንግሥታት በዘፈቀደና በማናለብኝነት ሕዝባዊ በዓላትን ለማክበር መፍጨርጨራቸው በዓሉን ሕዝባዊ አያደርገውም፡፡ ጊዜያቸው አብቅቶ ከሥልጣን ሲወርዱ ዞሮ ዞሮ በዓል የተባለው ቀን ተረስቶ አዘቦት ይሆናል፤›› በማለት ነበር ሐሳባቸውን ያጠቃለሉት፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፖለቲከኞች በተፈራረቁ ቁጥር የአከባበር ሁኔታቸው የሚፈራረቀውን በዓላት ቀርቶ ለዘመናት በሕግ ተደንግገው የሚከበሩ እንደ ዓድዋ ድል ያሉ በዓላትንም በማክበር ረገድ የፖለቲካው ውዝግብ እየተለመደ መምጣቱ ይነገራል፡፡
አየለ (ፕሮፌሰር)ም ሆኑ አቶ አንዷለም ስለዚሁ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፣ በሕዝባዊ በዓላት የፖለቲካ ፍላጎትን የማስፈጸም ነገር የችግር ምንጭ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የሕዝባዊ በዓላትን ባለቤትነት ለራሱ ለሕዝቡ በመተው ከዚህ ችግር ለመውጣት መፍትሔ እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡ መንግሥታት ወይም ፖለቲከኞች ሕዝባዊ በዓላትን ወደ ራሳቸው ፖለቲካ ተፅዕኖ መክተት እንደሌለባቸውም ነው ያሳሰቡት፡፡ የዓድዋ ድል በዓልን ጨምሮ ሕዝባዊ በዓላትን እንደ ስማቸው ለሕዝቡ እንዲተውም ጠይቀዋል፡፡