የክሪፕቶ ንግሥቷ ሩጃ ኢግናቶቫ
የምስሉ መግለጫ,የክሪፕቶ ንግሥቷ ሩጃ ኢግናቶቫ

ከ 8 ሰአት በፊት

በአውሮፓውያን መስከረም 2019 የቢቢሲ ፖድካስት ስለቡልጋሪያዊቷ ሩጃ ኢግናቶቫ አንድ አስገራሚ ታሪክ ይፋ አድርጓል።

ይህ የሆነው ሐሰተኛ ክሪፕቶከረንሲ በመጀመር 4.5 ቢሊዮን ዶላር ባለሀብቶችን በማጭበርበሯ በኤፍቢአይ ተፈላጊዎች ዝርዝር ውስጥ ገብታ ደብዛዋ ከመጥፋቱ በፊት ነው።

አሁን ዕጣ ፈንታዋን ለማወቅ ቢቢሲ ዱካዋን ተከትሏል። የቢቢሲ አይ ኢንቨስቲጌሽን እና ፓኖራማ ከቡልጋሪያዊ የማፈያ አለቃ ጋር ያላትን የቅርብ ግንኙነት እና በአሰቃቂ ሁኔታ መገደሏን ተመልክተዋል።

ለመሆኑ ኢግናቶቫ በተዘረፈው ቢሊዮን ዶላር ዓለሟን ቀጨችበት ወይንስ እሷን ለመጠበቅ በተቀጠሩ ሰዎች ህይወቷ አለፈ?

የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ምሩቋ ሩጃ ኢግናቶቫ ቡልጋሪያ ተወልዳ ጀርመን ነው ያደገችው። በ2014 ዋንኮይን ክሪፕቶከረንሲን ከመጀመሯ በፊት በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ የተሳካ ቆይታ ነበራት።

ኢግናቶቫ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ዋን ኮይን ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ አሳምናለች። እንደቢትኮይን ያሉ ክሪፕቶከረንሲዎች ካስገኙት በላይ ዋን ኮይን ትርፋማ ነው የሚል ቃል ገብታ ነው ከመላው ዓለም ብዙዎችን የሳበችው።

ለብዙዎች ዶ/ር ሩጃ በመባል የምትታወቀው ኢግናቶቫ እንደ ቢትኮይን ያሉ ሕጋዊ ዲጂታል ገንዘቦችን ሳይሆን ሐሰተኛ የኢንቨስትመንት ሃሳብ ነው ይዛ ብቅ ያለችው።

እአአ ጥቅምት 2017 የጀርመን እና የአሜሪካ መርማሪዎች ሊይዟት መቃረባቸውን ያወቀችው ኢግናቶቫ ጎህ ሳይቀድ ከቡልጋሪያ መዲና ሶፊያ ወደ አቴንስ በረረች። ዳግመኛ ግን አልታየችም።

የቢቢሲ ወርልድ ሰርቪስ አይ ኢንቨስቲጌሽን እና ፓኖራማ የት እንደገባች እና በሕይወት ስለመኖሯ ለማወቅ ሲሞክሩ ቆይተዋል።

የዚህ ምርመራ ዋናው መረጃ የተገኘው ከቀርብ ሰዎቿ ነው።

ከኤፍቢአይ ጋር በመሆን ዋን ኮይን ለአሜሪካ ገቢዎች ቢሮ ምርመራውን የጀመረው ሪቻርድ ሬይንሃርድ መርማሪዎች ከዚህ በፊት በይፋ ስማቸው ስለማያውቁት ቁልፍ ሰው ባህሪ ለቢቢሲ ተናግሯል።

የጠፋችው ክሪፕቶንግስት ምን ገጠማት?

የዋንኮይን ክሪፕቶከረንሲ ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ሩጃ ኢግናቶቫ የኤፍቢአይ በጣም ተፈላጊ ሴት ለመሆን በቅታለች። በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ዘርፋ አሁን ደብዛዋ ጠፍቷል። ምን እንዳጋጠማት የሚገልጹ አዳዲስ መረጃዎች ወጥተዋል። ጠፋች ወይስ ተገደለች?

የኢግናቶቫን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነት የተሰጠው አንድ ሰው አለ። ክሪስቶፎሮስ ኒኮስ አማናቲዲስ ይባላል። በስፋት የሚታወቀው ታኪ በሚለው ስሙ ነው።

ሬይንሃርድ በ2023 መገባደጃ ላይ ጡረታ ከወጣ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጠው ቃለ ምልልስ “በአደንዛዥ ዕፅ ማዘዋወር ስሙ የገነነ አንድ ሰው የግል ጥበቃዋን ይመራው ነበር ተብሎ ተነግሮን ነበር” ብሏል።

“ታኪ የሚለውን ስም ከአንድ ጊዜ በላይ ሰምተናል። አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ የሰማነው ነበር።”

ይህ ቀደም ሲል ቢቢሲ ከነበረው መረጃ ጋር ይጣመማል። የአሜሪካ መንግሥት ጠበቆች እአአ በ2019 እንደገለጹት ከሆነ የኢግናቶቫ የደኅንነት ኃላፊ በቡልጋሪያ ውስጥ የተደራጀ ወንጀል ቡድን መሪ መሆኑን አንጂ ስሙን አልጠቀሱም።

“ቡልጋሪያ ውስጥ በጣም ታዋቂው የዕፅ አዘዋዋሪ የሆነ ግለሰብ ከዋን ኮይን ጋር የተገናኘ መሆኑን ብቻ ሳይሆን የሩጃ ጠባቂ ሆኖ እንደሚሠራ የሚያሳይ ማስረጃ አለን” ሲሉ አንድ ጠበቃ ተናግረዋል።

ይህ ተመሳሳይ “የደኅንነት ኃላፊ” ነበር በኢግናቶቫ መጥፋት ውስጥ “የተሳተፈው” ሲሉ ሌላ ጠበቃ ገልጸዋል።

የቀድሞው መርማሪ ሪቻርድ
የምስሉ መግለጫ,የቀድሞው መርማሪ ሪቻርድ

እንደ ራይንሃርት ገለጻ ከሆነ ኢግናቶቫ አብዛኛው ሰው ከሚያስበው በላይ በጣም የተራቀቀች ወንጀለኛ ነበረች።

“ይህ ልክ ከአንድ በላይ ሕገወጥ ደርጊቶች ላይ እንደሚሳተፍ ወንጀለኛ ማለት ነው።”

ይህ ጽንሰ-ሐሳብ ቢቢሲ በተመለከተው የዩሮፖል ሰነዶች የተደገፈ ይመስላል። ኢግናቶቫ በ2017 ከመጥፋቷ በፊት የቡልጋሪያ ፖሊስ በእሷ እና በታኪ መካከል ግንኙነት እንደተፈጠረ ያሳያል።

ፖሊስ በሰነዶቹ እንደገለጸው ከሆነ ታኪ ከአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ያገነውን ገንዘብ ሕጋዊ ለማስመሰል ዋን ኮይንን በመጠቀም ጠርጥሮታል።

ታኪ በአገሩ ቡልጋርያ ኤል ቻፖ ወይም ፓብሎ ኤስኮባር ዓይነት ሰው ነው። የቡልጋሪያ የተደራጀ ወንጀል ድርጅት እና የዕፅ አዘዋዋሪዎች ኃላፊ እንደሆነ በሰፊው ይጠረጠራል።

እሱ እና አጋሮቹ በመሣሪያ በታገዘ ዝርፊያ፣ በአደንዛዥ ዕጽ በማዘዋወር እና በግድያ ተጠርጥረው ምርመራ ቢካሄድባቸውም አንዴም ተከሶ አያውቅም።

ኢንተርፖል ታኪ ላይ የእስር ማዘዣ አውጥቶ ነበር
የምስሉ መግለጫ,ኢንተርፖል ታኪ ላይ የእስር ማዘዣ አውጥቶ ነበር

“ስለ ታኪ ስንናገር በቡልጋሪያ ውስጥ የማፍያ ዋነኛ ኃላፊ ነው። በጣም ኃይለኛ ግለሰብ ነው” ሲሉ በ2022 ታኪ በሙስና የተዘፈቁ ባለሥልጣናትን በመጠቀም የወንጀል መረብን ይመራ የነበረ መሆኑን የመረመሩት የቀድሞ የቡልጋሪያ ምክትል ሚኒስትር ኢቫን ሂስታኖቭ ተናግረዋል።

“ታኪ መንፈስ ነው። በጭራሽ አታየውም። ስለ እሱ ብቻ ነው የምትሰማው። በሌሎች ሰዎች በኩል ነው የሚያናግርህ። ካልሰማህ ከምድር ላይ መጥፋት ብቻ ነው መጨረሻህ።”

“(ኢግናቶቫን) ከየትኛውም የወንጀል ምርመራዎች ሊጠብቃት የሚችለው ብቸኛው ሰው ታኪ ነበር” ብለዋል።

ቢቢሲ በሙስና የተዘፈቁ የተባሉ ባለሥልጣናትን አስመልክቶ ለቡልጋሪያ መንግሥት ጥያቄ አቅርቧል። ምላሽ አልተሰጠውም። በርዕሰ መዲናዋ ሶፊያ የሚገኘው የዐቃቤ ሕግ ቢሮ በበኩሉ “ወንጀሎችን እና ምናልባትም ወንጀል የፈጸሙ ሰዎችን አንደብቅንም” ብሏል።

ታኪ አሁን ዱባይ ይኖራል ተብሎ ይታመናል። ዱባይ ኢግናቶቫ የቅንጦት መኖሪያ ቤት የገዛችበት እና ከዋን ኮይን የምታገኘውን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር የምታስቀምጥባቸው የባንክ ሂሳቦቿም ያሉበት ነው።

ታኪ እና ኢግናቶቫ እንዴት እንደተገናኙ አይታወቅም። ዋን ኮይን ሲጠነሰስ ጀምሮ አብረው ስለመሆናቸው የሚታወቅ ነገር የለም። ከብዙ የቅርብ ምንጮች የተገኙ መረጃዎች ግን ሁለቱ የቅርብ ግንኙነት እንደነበራቸው እና ለሴት ልጅዋም የክርስትና አባት እንደሆነ ይናገራሉ።

ለኢግናቶቫ ቅርብ የሆነች አንዲት የቡልጋሪያ ምንጭ ለቢቢሲ እንደገለጸችው ታኪን እንዲጠብቃት በወር እስከ 100 ሺህ ዩሮ ትከፍለው ነበር።

በኢግናቶቫ እና በታኪ መካከል ሌላም የገንዘብ ግንኙነት ያለ ይመስላል።

የዩሮፖል ሰነዶች እንደሚየሳዩት ከሆነ በቡልጋሪያ የጥቁር ባሕር ዳርቻ ላይ ያለውን መሬት ለመሸጥ ውስብስብ ስምምነትን መደረሱን ይጠቅሳሉ። ይህም ከኢግናቶቫ ኩባንያዎች አንዱን ከታኪ ሚስት ጋር ያገናኛል።

ምሥጢዊ የፖሊስ ሰነዶች ለቢቢሲ የተላለፉት በቀድሞ ሰላይ እና የኢግናቶቫ አማካሪ በነበረው ፍራንክ ሽናይደር ነው።

የድሮው አለቃው “ከአጭበርባሪዎች” እና “ከወንበዴዎች” ጋር እየሠራች መሆኑን ተናግሯል።

ከቃለ መጠይቁ በኋላ የጠፋው ፍራንክ ሽናይደር
የምስሉ መግለጫ,ከቃለ መጠይቁ በኋላ የጠፋው ፍራንክ ሽናይደር

ቢቢሲ ሽናይደርን ፈረንሳይ በሚገኘው በመኖሪያ ቤቱ ቃለ መጠይቅ ባደረገበት ወቅት በቤቱ የቁም እስረኛ ከመሆኑም በላይ ከዋን ኮይን ማጭበርበር ጋር በተያያዘ ለአሜሪካ ተላልፎ መስጠቱን በመጠባበቅ ላይ ነበር። ስሞችን ለመግለጽ ግን ዝግጁ አልነበረም።

“ስም አልጠቅስም፤ ምክንያቱም ቤተሰብ ስላለኝ… ይህ የተደራጀ ከባድ የወንጀል ቡድን ነው።”

መጨረሻ ላይ ግን የኢግናቶቫ ጠባቂ ወደ አጥቂነት ተቀይሮ ሊሆን ይችላል።

እአአ በ2022 የቡልጋሪያ የምርመራ ጋዜጠኛ ዲሚታር ስቶያኖቭ እና ባልደረቦቹ በተገደለ የቡልጋሪያ ፖሊስ መኮንን ቤት የተገኘ የፖሊስ ሪፖርት ተሰጣቸው።

በሰነዱ ውስጥ አንድ የፖሊስ መረጃ ሰጪ የታኪ አማች በ2018 መገባደጃ ላይ ኢግናቶቫ በታኪ ትዕዛዝ መገደሏን እና ሰውነቷ ተቆራርጦ ከጀልባ ላይ ወደ አዮኒያን ባሕር እንዲጣል ስለመደረጉ መስማቱን በዝርዝር ገልጿል። ስቶያኖቭም ይህንን “በጣም በጣም ሊሆን የሚችል ነው” ብሎታል።

የፖሊስ ሰነድ ትክክለኛነት በቡልጋሪያ ባለሥልጣናት የተረጋገጠ ሲሆን፣ በርካታ የታኪ የወንጀል ተባባሪዎች በእሱ መገደሏን እውነት እንደሆነ ያምናሉ ሲሉ ስቶያኖቭ ተናግሯል።

ቢቢሲ ግን ይህንን በራሱ ማረጋገጥ አልቻለም።

ተባባሪዎቹ እንደምክንያት የሚያቀርቡት ከዋን ኮይን ማጭበርበር ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጥፋት ለሚፈልገው ታኪ ኢግናቶቫ ዋነኛ ስጋቱ መሆኗን ነው።

ከእነዚህ መካከል ደግሞ በነፍስ ግድያ ወንጀል በኢንተርፖል የሚፈለገው ክራሲሚር ካሜኖቭ ወይም ኩሮ የተባለ ተባባሪው ይገኝበታል።

ስቶያኖቭ እንዳለው ከሆነ ኩሮ ታኪ በኢግናቶቫ ፊት ስለ ወንጀል ንግዱ ሲወያይ እንደሰማው ኩሮ ተናግሯል። ታኪ ያን ማድረግ እንዳለበት በኩሮ ሙግት ሲገጥመውም “አትጨነቅ፣ እሷ የሞተች ያህል ነች” ሲል መልሷል።

ኩሮ አክሎም ታኪ ኢግናቶቫን እንድትገደል ትዕዛዝ ሰጥቷል የሚለውን ውንጀላ ጨምሮ ስለ ታኪ ከሲአይኤ ጋር እንደተነጋገረ ተናግሯል። ይህ ውይይ በ2022 መገባደጃ ላይ መካሄዱን ለኩሮ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ግንቦት 2023 ላይ ኩሮ ከሚስቱ እና ከሌሎች ሁለት አብረውት ከሚሠሩት ሰዎች ጋር በኬፕ ታውን በሚገኘው ቤቱ ተገደለ። የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ አሁንም ገዳዮቹን እያፈላለገ ነው።

የቡልጋሪያ የቀድሞ ምክትል ሚኒስትር ሂስታኖቭ ግን የኩሮ ግድያ ከታኪ ጋር የተያያዘ ነው በማለት “ስለ ታኪ ብዙ ስለሚያውቁ አንዳንድ ሰዎች መወገድ ነበረባቸው” ያምናሉ።

“መግለጫ የሚመስል በአደባባይ የተፈጸመ ግድያ ነበር። ከማን ጋር እንደምገዳደሩ አውቃችሁ ተጠንቀቁ ይመስላል” ብለዋል።

ስለ ኢግናቶቫ ግድያ ጉዳይ ከዘገበ ጊዜ ጀምሮ ጋዜጠኛው ዲሚታር ስቶያኖቭ እና ባልደረቦቹ የግድያ ዛቻ ገጥሟቸው እንደነበር ተናግሯል። በዚህም በሥራው ምክንያት ለአራተኛ ጊዜ ከቡልጋሪያ ለጊዜው እንዲሰደድ አስገድዶታል።

ስቶያኖቭ ለተከሰተው ግድያ ምክንያቱን አውቃለሁ ብሎ አይናገር እንጂ፣ መዛግብት እና የዐይን እማኞች እንደሚናገሩት ከሆነ ኢግናቶቫ ከጠፋች ጀምሮ በርካታ የቡልጋሪያ ንብረቶቿን ከታኪ ጋር የተገናኙ ሰዎች እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።

የሩጃ ኢግናቶቫ ንብረት
የምስሉ መግለጫ,የሩጃ ኢግናቶቫ ንብረት

ታኪ ከኢግናቶቫን ግድያ ጋር በተያያዘ ክስ ተይዞ አያውቅም። አስከሬኗም አልተገኘም። መርማሪዎች ደግሞ እሱን ለመክሰስ በቂ ማስረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል።

የቀድሞው የአይአርኤስ መርማሪ ሪቻርድ ራይንሃርድት በበኩላቸው ኢግናቶቫ ሞታለች ብለው ያስባሉ። ሕይወቷ ማለፉን ከታኪ ጋር የሚያያይዘው ምንም ዓይነት ማስረጃ ባያገኝም የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪዎች ከሚሠሩበት መንገድ ጋር የሚመሳሰል እንደሆነ ተናግሯል።

“በሌቦች ዘንድ ክብር የለም… ምን ያህል ጨካኞች እንደሆኑ ስለሚታወቅ [ታኪ] ለእሱ አስጊ እንደሆነች ካሰበ…ከመያዝ ይልቅ ሊገድላት ይችላል።”

ቢቢሲ ስለምርመራው ለታኪ ጠበቆች ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ አልሰጡም።

ኢግናቶቫ እአአ በ2022 በኤፍቢአይ በብርቱ ከሚፈለጉ አስር ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ተካታለች። እስካሁንም ስሟ ከዝርዝሩ ውስጥ አልወጣም።

ኢግናቶቫ ተገድላለች ከተባለ በኋላ ቢቢሲ የት እንዳለች የሚገልጹ ጥቆማዎችን ተቀብሏል። በ2022 ግሪክ ውስጥ እሷን ለመያዝ ያልተሳካ የፖሊስ ዘመቻ መካሄዱም አንደኛው ነው።

ምናልባትም ስለ ሞቷ የሚናፈሱት ወሬዎች የሁሉንም ሰው ዐይን ከእሷ ላይ ለማንሳት የተደረገ አስደናቂ ዘዴ ሊሆን ይችላል።

ይህ ከሆነ ደግሞ ዓመታት ባለፉ ቁጥር በሽሽት ለመቆየት አስቸጋሪ እየሆነባት ነው ማለት ነው።

“አንዳንድ ጊዜ ኤልቪስ ፕሬስሊ በሕይወት አለ እንደሚባለውን ይመስላል… ይህ ግን አይሆንም” ብለዋል ሂስታኖቭ።

እንደ ራይንሃርት ገለጻ ደግሞ ኤፍቢአይ “በጣም ተፈላጊ አስር ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ለቀልድ ብሎ ብቻ አያስቀምጥም። አንድ ሰው መሞቱን “ማረጋገጫ” ካገኘ ብቻ ስሙን ያነሰዋል። እና ከሁኔታዎች አንፃር፣ ከሩጃ ኢግናቶቫ ጋር በተያያዘ ሞታ ላይሆንይችላል።”

ያ ማለት ደግሞ የጠፋችው የክሪፕቶ ንግሥት ለጊዜውም ቢሆን በታዳኞች ስም ዝርዝር ውስጥ ሆና ትቀጥላለች።