
ከ 7 ሰአት በፊት
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በሜክሲኮ በኩል ወደ አሜሪካ የሚገቡ ስደተኞችን ለመቆጣጠር ያለመ አዲስ እና መጠነ ሰፊ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ዛሬ ማክሰኞ ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው።
አዲሱ የፕሬዝዳንቱ ውሳኔ የአሜሪካ ኢሚግሬሽን ባለሥልጣናት በየዕለቱ ከሚመለከቱት በሕገ ወጥ መንገድ የገቡ የጥገኝነት ጠያቂዎች ቁጥር በላይ አመልካቾች ከቀረቡ ጥያቄያቸውን ሳይመለከቱ በቀጥታ ከአገር እንዲባረሩ ማድረግ የሚያስችል ሥልጣን ይሰጣል ተብሏል።
ይህም ድንበር ላይ ያሉ ባለሥልጣናት ወደ አሜሪካ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥርን እንዲገድቡ እንደሚያስችላቸው ሦስት ስማቸው ያልተጠቀሰ ምንጮች በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ባይደን በሥልጣን ላይ በቆዩባቸው ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ከ6.4 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አሜሪካ ለመግባት እንደሞከሩ ተነግሯል። ይህ እስካሁን ከታየው ከፍተኛው ሲሆን፣ ለዳግም ምርጫ ዘመቻ ላይ ያሉትን ባይደን ፈተና ጋርጦባቸዋል።
የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡት እንዳለው ባይደን አሁን በ1952 የወጣውን በአሜሪካ ጥገኝነት የማግኘት ሥርዓትን ለመገደብ የሚያስችለውን ሕግ ለመጠቀም እያሰቡ ነው።
212(ኤፍ) በመባል የሚታወቀው ሕግ ወደ አሜሪካ የሚገቡ የውጭ ዜጎች “ለአገሪቱ ብሔራዊ ጥቅም አስጊ የሚሆኑ ከሆነ” ፕሬዝዳንቱ “እንዳይገቡ ማገድ” የሚያስችለው ነው።
- ‘ጎልደን ቪዛ’ ምንድነው? የትኞቹ አገራትስ ይሰጣሉ? ለምንስ በጣም አነጋጋሪ ሆነ?3 ሰኔ 2024
- ‘በአመጽ ተግባር የተሳተፈ ቡድንን’ የፓርቲነት ጥያቄን ውድቅ የማድረግ ሥልጣን ለምርጫ ቦርድ ያልሰጠው አዋጅ ለፓርላማ ቀረበከ 8 ሰአት በፊት
- 10 ወራት ያስቆጠረው የአማራ ክልል ግጭት እና ሊጠናቀቅ የተቃረበው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅከ 8 ሰአት በፊት
ይህን ሕግ ትራምፕ በሥልጣን ላይ ሳሉ ተግባራዊ አድርገው አብዛኞቹ ሙስሊም ከሆኑ አገራት የሚመጡ ስደተኞች እና ተጓዦች እንዲሁም በሕገ ወጥ መንገድ የአሜሪካንን ድንበር አቋርጠው ሲገቡ የተያዙ ስደተኞች ላይ ዕገዳ ጥለው ነበር። ነገር ግን በፕሬዝዳንቱ ላይ የዘረኝነት ወቀሳ እንዲነሳባቸው አድርጎ ነበር።
አሜሪካንን ከሜክሲኮ ጋር በሚያዋስኑ ግዛቶች ውስጥ የሚገኙት ከተሞች ከንቲባዎች ፕሬዝዳንት ባይደን አዲሱን የስደተኞች መቆጣጠሪያ ውሳኔያቸውን በሚያሳውቁበት ጊዜ ለመገኘት ዋሽንግተን ገብተዋል።
የዲሞክራቲክ ፓርቲ የምክር ቤት አባላት የፕሬዝዳንቱ ዕቅድን በተመለከተ ቀደም ተብሎ ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል።
የፕሬዝዳንቱ ውሳኔ ለስደተኞች መብት ከሚቆረቆሩ ወገኖች ወይም በሪፐብሊካኖች ከሚመሩ ግዛቶች በኩል በፍርድ ቤት ተቃውሞ ሊቀርብበት እንደሚችል ይጠበቃል።
ከዚህ ቀደም የአሜሪካንን የድንበር ደኅንነት ለማጠናከር በዲሞክራቶች ቀርቦ የነበረው ሐሳብ በሪፐብሊካኖች ተቃውሞ ገጥሞት ሳይሳካ መቅረቱ ይታወሳል።
ሪፐብሊካኖች አሜሪካ ሕገወጥ ስደትን ለመከላከል ሕግ ቢኖራትም በዲሞክራቶች በኩል በተገቢው ሁኔታ ተግባራዊ አልተደረገም በማለት ባይደን ይፋ ሊያደርጉ ያቀዱትን የድንበር ቁጥጥር ውሳኔ ለምርጫ የሚደረግ እንቅስቃሴ ሲሉ ተችተውታል።
ባለፉት ወራት ከሜክሲኮ ወደ አሜሪካ የሚገቡ የስደተኞች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱ የተነገረ ሲሆን፣ ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። ነገር ግን ይህ የመቀነስ ሁኔታ ዘላቂ እንዳልሆነ የሚናገሩም አሉ።
በአሜሪካ የተደረጉ የሕዝብ አስተያየት ምዘናዎች በቀጣይ ዓመት በሚደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የበርካታ ድምጽ ሰጪዎች ቀዳሚ አሳሳቢ ነገር የስደተኞች ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል።
ባለፈው ሚያዝያ ወር ማብቂያ ላይ በጋሉፕ በተደረገው የሕዝብ አስተያየት መመዘኛ 27 በመቶ አሜሪካውያን ከምጣኔ ሀብት እና ከዋጋ ግሽበት በላይ የስደተኞች ጉዳይ የአገሪቱ ዋነኛ ችግር ነው ብለው ያምናሉ።
በአሶሺየትድ ፕሬስ እና ኖርክ በተባለው የምርምር ተቋም በመጋቢት ወር በተሰበሰበ የሕዝብ አስተያየት ከአሜሪካውያን ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት እና 40 በመቶዎቹ የዲሞክራቲክ ፓርቲ መራጮች የባይደን የድንበር ደኅንነት አያያዝን ይተቻሉ።