ድንበር ላይ የተያዙ ስደተኞች

ከ 4 ሰአት በፊት

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከሜክሲኮ የአሜሪካን ድንበር በማቋረጥ በአሜሪካ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ቁጥር ለመገደብ የሚያስችል ትዕዛዝ አስተላለፉ።

በሕገ-ወጥ መንገድ የአሜሪካን ድንበር እያቋረጡ ጥገኝነት የሚጠይቁ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች ጉዳይ የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደርን ሲያስተች ቆይቷል።

በአዲሱ ፕሬዝዳንታዊ መመሪያ መሠረት ባለስልጣናት ድንበር አቋርጠው የገቡ ሰዎች የጥገኝነት ጥያቄያቸው ሳይታይ ከአሜሪካ በኃይል እንዲያስወጡ ይፈቅድላቸዋል።

ዋይት ሃውስ በመግለጫ እንዳለው ጉዳያቸው የሚመዘገቡ ሰዎች ዕለታዊ ኮታ ከተሟላ የተቀሩት ከአሜሪካ እንዲወጡ ይደረጋሉ።

የበርካታ የድንበር ከተሞች ከንቲባዎች በተገኙበት ስነ-ስርዓት ላይ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አዲሱን መመሪያ በተመለከት ባደረጉት ንግግር “ይህ እርምጃ በድንበራችን አካባቢ ነገሮችን መልስን እንድንቆጣጠር ያስችለናል” ብለዋል።

ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለማካሄደ የወራት ዕድሜ በቀራት አሜሪካ የጆ ባይደን አስተዳደር ወቀሳ ከሚደርሱበት ጉዳዮች መካከል ቀዳሚው ከሜክሲኮ ወደ አሜሪካ የሚሻገሩ ስደተኞች ጉዳይ ነው።

በርካታ የመብት ተሟጋቾች መመሪያውን እየተቃወሙት ይገኛሉ። የናሽናል ኢሚግሬሽን ፎረም ፕሬዝዳንት የሆኑት ጄኒ መሪይ “ፖለቲካዊ ጉዳዮች የኢሚግሬሽን ጉዳዮችን እያወሳሰቡት መሆኑ ያሳዝናል” ብለዋል።

በባይደን አስተዳደር ወቅት ብቻ ከ6.4 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ድንበር አቋርጠው በሕገ-ወጥ መንገድ አሜሪካ ገብተዋል።

ባይደን ለአሜሪካ ብሔራዊ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የውጪ ዜጋ ወደ አገር እንዳይገባ “እንዲታገድ” የሚል ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንዲሁ ይህን ሕግ ተጠቅመው ከሙስሊም አገራት የሚመጡ ተጓዦችን ማገዳቸው ይታወሳል።

በአዲሱ መመሪያ መሠረት በየዕለቱ 2ሺህ 500 ሰዎች ድንበር ካቋረጡ በኋላ የሚሻገሩ ተጨማሪ ስደተኞች በኃይል ከአሜሪካ እንዲወጡ ይደረጋሉ።

ባለፉት ዓመታት በአማካይ በየዓመቱ ግማሽ ሚሊዮን ሰዎች በሕገ-ወጥ መንግድ የአሜሪካን ድንበር ሲያቋርጡ ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህ አሃዝ ከፍተኛ ጭማሪን አሳይቷል።

በሕዳር ወር 2016 ዓ.ም. ብቻ በሜክሲኮ በኩል ድንበር ያቋረጡ ሰዎች ቁጥር 250ሺህ ገደማ ነበር። ከዚያ ቀደም በነበረው ወር ደግሞ 192ሺህ ሰዎች ድንበር ማቋረጣቸውን የአሜሪካ የድንበር ጥበቃ ባለስልጣን አሃዝ ያሳያል።

በአሪዞና እና ቴክሳስ ግዛቶች በኩል ወደ አሜሪካ ድንበር ከሚያቋርጡ ዜጎች መካከል የሜክሲኮ፣ ቬንዙዌላ፣ ጓቲማላ፣ ሆንዱራስ እና ኮሎምቢያ ቀዳሚዎቹ ናቸው።