ዙማ

ከ 5 ሰአት በፊት

በአውሮፓውያኑ 2018 በደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ የሥልጣን ሽኩቻ ነበር። ይህንን ተከትሎ ሲርል ራማፎሳ የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኤኤንሲ) እና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት በመሆን ጃኮብ ዙማን ተክተዋል።

ስድስት ዓመት ወደ ኋላ እንመለስ። የ82 ዓመቱ ጃኮብ ዙማ ከፕሬዝዳንትነታቸው ሲለቁ የፖለቲካ ሕይወታቸው ያበቃ መስሎ ነበር።

ነገር ግን ያልታሰበው ሆነና አንሰራርተው አሁን ብቅ አሉ። ይህም ‘የዙማ ሱናሚ’ የሚል ስያሜ ተሰጠው።

ዙማ እና ውዝግብ ግን የሚለያዩ አልሆነም። በበርካቶች ዘንድ ያላቸው ተወዳጅነት (ፖፑሊስት) እና ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ ናቸው ከሚባሉት ትውልደ ሕንዳውያኑ ቱጃሮች የጉፕታ ቤተሰቦች ጋር ያላቸው ከሙስና ጋር የተያያዘ ግንኙነት ከውዝግብ እንዳይለዩ ካደረጓቸው መካከል ናቸው።

ባለፈው ሳምንት በደቡብ አፍሪካ በተካሄደ አጠቃላይ ምርጫ በቅርቡ ያቋቋሙት ኡምኾንቶ ዊሲዝዌ (ኤምኬ) ፓርቲ ከ14 በመቶ በላይ ድምጽ ለማግኘት መቻሉ በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ያላቸው ሚና አለማብቃቱን አመልክቷል።

ፓርቲያቸው ከ16.2 ሚሊዮን በላይ ድምጽ ሰጪዎች መካከል 2.3 ሚሊዮን ድምፅ አግኝቷል። ከገዢው ከአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኤኤንሲ) እና ከዴሞክራቲክ አሊያንስ (ዲኤ) በመቀጠል በሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ብዙዎች የዙማን መውደቅ እና መነሳት ከዶናልድ ትራምፕ ጋር አነጻጽረውታል። ትራምፕ በዚህ ሳምንት ጥፋተኛ የተባሉ የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነዋል።

ከሦስት ዓመታት በፊት ዙማ በፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው በሙስና ወንጀል ላይ በተደረገ ምርመራ ላይ ፍርድ ቤት ቀርበው ማስረጃ ባለማቅረባቸው ጥፋተኛ ተብለው እስር ቤት ተወርውረው ነበር።

ደቡብ አፍሪካ ወደ ዲሞክራሲ ከተሸጋገረችበት ጊዜ አንስቶ ከ300 በላይ ሰዎችን ለህልፈት የዳረገው ከፍተኛውን ረብሻ የተነሳውም እሳቸው እአአ ሐምሌ 2021 ሲታሰሩ ነበር።

የጃኮብ ዙማ ኡምኾንቶ ዊሲዝዌ (ኤምኬ) ፓርቲ ደጋፊዎች
የምስሉ መግለጫ,የጃኮብ ዙማ ኡምኾንቶ ዊሲዝዌ (ኤምኬ) ፓርቲ ደጋፊዎች

ተጽእኖ ፈጣሪነታቸው ያልደበዘዘው ዙማ

ከምርጫው ጥቂት ሳምንታት በፊት ዙማ በወንጀል ጥፋተኛ ሆነው ስለተፈረደባቸወ ለፓርላማ አባልነት እንዳይወዳደሩ በፍርድ ቤት ተከለከሉ። ይህ ደግሞ ሌላ የመውደቃቸው ምልክት ሆኖ ታየ።

መሰናክሉ ግን ፓርቲያቸው በምርጫ የላቀ ውጤት እንዳያመጣ አላገደውም። የዙማ የመታገድ ውሳኔ መራጮች ለፓርቲያቸው ድምጽ እንዳይሰጡ አላደረጋቸውም።

የፓርቲያቸውን የምርጫ ውጤት ተከትሎ ዙማ በድጋሚ መነሳት ጀመሩ።

ዙማ የምርጫ ውጤት ማብሰሪያው ዋዜማ ላይ “ማንም ሰው ውጤት ማወጅ የለበትም። አታስቆጡን። ችግር አትውለዱ” ሲሉ ከኤምኬ እና ሌሎች ሃያ አምስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን (አይኢሲ) ላይ ከድምጽ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ ዛቻ መሰል ክስ ሰነዘሩ።

ኤምኬ የዙማ የመኖሪያ ግዛት በሆነችው ክዋዙሉ ናታል ውስጥ ከፍተኛው ድምጽ አግኝቷል። በአገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ሦስተኛ ሆኖ አጠናቋል። በዚህ ያልረካ የሚመስለው ፓርቲው ምርጫው ነጻ አልነበረም፣ ተአማኒነትም ይጎድለዋል ብሏል።

ኮሚሽኑ ግን እነዚህን ክሶች ውድቅ አድርጓል።

ዙማ የምርጫው ውጤት ይፋ ከመሆኑ በፊት ቅዳሜ ምሽት ባልተጠበቀ እና አስገራሚ በሆነ ሁኔታ በጆሃንስበርግ የምርጫ ማዕከል መድረሳቸው የአካባቢው ድባብ በአንዴ ተቀየረው። በደቡበ አፈሪካ ተወዳጀ የሆነወ አማፒያኖ ወይም የአፍሮፖፕ ሙዚቀኛ ወደ መድረክ የገባ ይመስል ህንጻው በአንድ አግሩ ቆመ።

ከቀድሞ አጋሮቻቸው ጋር ብቻ ሳይሆን አሁን ከሚቃወሟች የኤኤንሲ ፓርቲ አባል ጭምር ነበር አቀባበሉ የደመቀላቸው።

“ጃኮብ ዙማ በደቡብ አፍሪካ ፖለቲካ ውስጥ ትልቅ ስም ያለው ኃይል ነው… አሳንሰን አናየውም” ሲሉ የኤኤንሲ ዋና ፀሐፊ ፊኪሌ ምባሉላ በፓርቲያቸው ደካማ የምርጫ አፈጻጸም ዙሪያ አስተያየት ሲሰጡ ተናግረዋል።

የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኤኤንሲ) ደጋፊዎች
የምስሉ መግለጫ,የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኤኤንሲ) ደጋፊዎች

ያልተበጠሰው የዙማ እና የኤኤንሲ ትስስር

ዙማ ምንም እንኳን ደቡብ አፍሪካን ከአፓርታይድ ሥርዓት ለማላቀቅ ከታገለው ከኤኤንሲ ፓርቲ የታገዱ ቢሆንም ፈጽሞ ከአባልነት ግን አልተባረሩም።

በታኅሣሥ ወር አዲሱን ኤምኬ ፓርቲያቸውን ይፋ ባደረጉበት ወቅት ዙማ ምንጊዜም የኤኤንሲ አባል እንደሚሆኑ አስታውቀዋል። በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ የኤኤንሲ ደጋፊዎች ከፓርቲው እንዲርቁ ጠይቀዋል።

የዙማ ታዋቂነት ለኤኤንሲ እንቅልፍ አልባ ምሽቶችን እንደሚፈጥር ምንም ጥርጥር የለውም።

በኤኤንሲ እና በዙማ መካከል ያለው ግንኙነት የሚጀምረው ፓርቲው ሕገ-ወጥ ድርጅት በነበረበት ወቅት ነው። ምንም ዓይነት መደበኛ ትምህርት ያልተከታተሉት ዙማ፣ በፀረ-አፓርታይድ እንቅስቃሴ ወቅት በሮቢን ደሴት ከኔልሰን ማንዴላ ጋር ለአስር ዓመታት ታስረዋል።

በአውሮፓወያኑ 1990 በኤኤንሲ ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ በአፓርታይድ መንግሠት ተነሳ። ዙማም ከስደት ተመልሰው በፖለቲካው ውስጥ ከፍ ማለት ጀመሩ። ከዚያም በ1999 የአገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ተሾሙ።

እአአ በ2005 የሥልጣን ዘመናቸው በድንገት አበቃ። ፕሬዝዳንት ታቦ ምቤኪ ከጦር መሳሪያ ሽያጭ ጋር በተያያዘ በሙስና ወንጀል ተሳትፈዋል መባሉን ተከትሎ ነው ከሥልጣን ያነሷቸው።

የቀድሞ የፋይናንስ አማካሪያቸው ሻቢር ሼክ በእሳቸው ስም ከአንድ የፈረንሳይ የጦር መሳሪያ ኩባንያ ጉቦ በመጠየቅ ጥፋተኛ ተብለዋል። በዚያው ዓመት ዙማም የሙስና ክስ ቀርቦባቸዋል። ክሱ ውድቅ ተደረገ ሲሆን፣ ዙማም ክሱ ፖለቲካዊ ነው ሲሉ አጣጥለውታል።

እአአ በ2005 ደግሞ ዙማ የፓርቲያቸውን ባልደረባ ልጅ ደፍረዋል በሚል ክስ ቀርቦባቸው ነበር። በወቅቱ 31 ዓመቷ የነበረው ሴት እና እናቷ በዙማ ደጋፊዎች ከደረሰባቸው ዛቻ በኋላ ማንነታቸውን ለመደበቅ ተገደዋል።

ዙማ በአስገድዶ መድፈር ወንጀል በተመሠረተባቸው ክስ ወቅት በሺህዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው ከፍርድ ቤት ደጃፍ ይሰበሰቡ ነበር። ከኤችአይቪ ካለባት ከሳሽ ጋር ጥንቃቄ የጎደለው የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈጸማቸውን ቢያምኑም ግንኙነቱ በስምምነት የተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። በቀጣዩ ዓመት ግን ከሁሉም ክሶች በነጻ ተብለዋል።

ዙማ በደቡብ አፍሪካ ማኅበረሰብ ውስጥ ካሉ ድሆች እና የተገለሉ ብሔረሰቦች ጋር ያላቸው ግንኙነት ከብዙ ፖለቲከኞች ይለያቸዋል። በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ተከሰው ነጻ መውጣታቸውን ተከትሎ በኤኤንሲ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ የሥልጣን ሽኩቻ ተከተለ።

እአአ በ2005 በዙማ ላይ የቀረበው የሙስና እና የማጭበርበር ክስ በቀድሞው ፕሬዝዳንት ታቦ ምቤኪ ወይም በደጋፊዎቻቸው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት እንዳለበት የሚያሳይ ማስረጃ ተገኝቷል ሲል ፍርድ ቤት ወሰነ።

ከጥቂት ቀናት በኋላ ምቤኪ ከፕሬዚዳንትነታቸው እንዲነሱ በኤኤንሲ ተጠየቁ። በፓርቲው ውስጥ ተወዳጅነት የነበራቸው ዙማ በ2007 በተካሄደው የፓርቲው ምርጫ የኤኤንሲ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ።

በ2009 ደግሞ ዙማ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ። በ2018 ከራሳቸው ፓርቲ በደረሰባቸው ከፍተኛ ጫና ምክንያት ሥልጣን ለመልቀቅ እስኪገደዱ ድረስም በፕሬዝዳንትነት ቆይቷል።

ዙማ ከሥልጣን እንዲወርዱ ያደረጋቸው የሥልጣን ሽኩቻ ቢኖረም፤ አብላጫ ወንበር ባለማግኘቱ በራሱ መንግሥት ለመመሥረት የማይችው ኤኤንሲ ከዙማ ኤምኬ ፓርቲ ጋር ጥምረት መፍጠርን ከአማራጮቹ ውጪ አላዳረገውም።

“ከእኛ ጋር መንግሥት ለመመሥረት ከተዘጋጁ ሁሉ ጋር እየተነጋገርን ነው” ሲሉ የኤኤንሲ ዋና ፀሐፊ ፊኪሌ ምባሉላ ተናግረዋል።

ኤምኬም ከኤኤንሲ ጋር መንግሥት ለመመሥረት ዝግጁ ነኝ ብሏል። አንድ ጉዳይ ግን እንደ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠዋል – የፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳን ከሥልጣን መልቀቅ።

ኤኤንሲ ይህ ፍላጎት ጥያቄ ውስጥ አይገባም ብሏል። አንድ እርግጠኛ የሚሆነው ነገር ግን ዙማ በአገሪቱ ከተካሄዱት ነጻ ምርጫዎች ሁሉ ለመገመት አስቸጋሪ በነበረው ምርጫ ኤኤንሲን ያደበዘዙ አማተር የቼዝ ተጫዋች ሆነው መታወሳቸው ነው።

አርማ