በምግብ እጥረት እየተሳቃዩ ያሉ ሱዳናውያን

ከ 5 ሰአት በፊት

ከአንድ ዓመት ባለፈው የእርስ በእርስ ጦርነት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሱዳናውያንን ለረሃብ አደጋ ማጋለጡን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ።

በሱዳን መንግሥት ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል የሚደረገው ጦርነት ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ሱዳናውያንን ከመኖሪያቸው ያፈናቀለ ሲሆን፣ ከአጠቃላይ የአገሪቱ ሕዝዝ ቀላል የማይባለው “ለከፍተኛ የረሃብ አደጋ” ተጋልጧል ተብሏል።

በጋዛ እና ዩክሬን እየተካሄዱ ባሉ ጦርነቶች ትኩረት የተነፈገው የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት በብዙዎች ዘንድ “የተዘነጋው ጦርነት” የሚል መጠሪያ አግኝቷል።

ይሁን እንጂ የሰብዓዊ ድርጅቶች ጦርነቱ በአስርት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ የረሃብ አደጋ የደቀነ ሊሆን ይችላል ሱሉ እያስጠነቀቁ ነው።

9 ሚሊዮን የሚሆኑ ሱዳናውያን ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል።
የምስሉ መግለጫ,9 ሚሊዮን የሚሆኑ ሱዳናውያን ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል።

ከሱዳን መዲና ካርቱም በቅርብ ርቀት የምትገኘው ኦምዱርማን ከተማ ነዋሪ የሆነው አሕመድ፤ በአገሪቱ ያለውን የምግብ እጥረት እና የምግብ ዋጋ መናርን በተመለከተ ስላለው ሁኔታ ቀርጾ ለቢቢሲ ልኳል።

እንደ አሕመድ ከሆነ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተቆጣጥሮ በሚገኝባቸው ካርቱም እና በኦምዱርማን የምስር ዋጋ በአራት እጥፍ ጨምሯል።

“ሁሉም ምግቦች ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከሚቆጣጠራቸው ቦታዎች በከፍተኛ ዋጋ ተገዝተው በድብቅ የሚገቡ ናቸው” ይላል።

“በመንደሩ ከቤት የማይወጡ ሰዎች አብዛኞቹ በቀን አንድ ጊዜ ብቻ የሚመገቡ ናቸው።

“ይህን እየቀርጽኩ ባለሁበት ቦታ ቁርሳቸውን ምስር ለመብላት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከጠዋት ጀምረው ተሰልፈዋል። ብዙ ሰዎች የሚያገኙት ምግብ ላይ ውሃ በብዛት እየጨመሩ ለእራት ጭምር ያደርጉታል።

“የአገሪቱ ጦርም ሆነ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተቆጣጥረው በሚገኙባቸው እና በነጻ ምግብ በሚቀርብባቸው ቦታዎች ምግብ ፍለጋ የሚሄዱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። ሰልፎች በየቀኑ በጣም ረዥም እየሆኑ ነው። ምግብ በነጻ የሚቀርብባቸው ቦታዎች እየጨመሩ ሲሆን የምግብ ጥራቱም እየቀነሰ ነው።”

Members of the Sudan Liberation Movement
የምስሉ መግለጫ,አርኤስኤፍ የሚባለው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ከአጋር የሚሊሻ ቡድኖች ጋር በመሆን ከአንድ ዓመት በላይ ከሱዳን ጦር ጋር ሲዋጋ ቆይቷል።

የሱዳን ጦርነት እንዴት ጀመረ?

በአገሪቱ መንግሥት በሚመራው በሱዳን መከላያ ኃይል እና በአማጺ ጄኔራል በሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል ግጭት የጀመረው ከአንድ ዓመት በፊት ሚያዝያ 2015 ዓ.ም. ነበር።

ባለፉት 12 ወራት ሔሜቱ ተብለው በሚታወቁት ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ የሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ከአብዛኛውን የካርቱም እና በምዕራብ ሱዳን የምትገኘውን ዳርፉርን ጨምሮ ከበርካታ የሱዳን አካባቢዎች የአገሪቱን ጦር አስወጥቶ ተቆጣጥሮ ይዟል።

ባለፈው ኅዳር ወር ደግሞ የሱዳን ዋነኛ እህል አብቃይ የሆነችውን የኤል ጌዚራ ግዛትን በመውረር በእጁ አስገብቷል።

ከካርቱም ለመሸሽ የተገደደው የሱዳን መንግሥት መቀመጫውን ወደ ወደበ ከተማዋ ፖርት ሱዳን አዘዋውሯል።

የረሃብ ስጋቱ እጅግ ከፍተኛ የሆነው 9 ሚሊዮን ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው በመፈናቀላቸው መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት ያሳያል።

ገበሬው ያመረተውን ምግብ የሚሊሻ አባላት ይዘርፉበታል። ሌላው አደገኛው አካሄድ ደግሞ ተዋጊዎች የባላንጣዎቻቸውን አካባቢዎች አቋርጦ የሚመጣ ሰብዓዊ እርዳታ አናስገባም ማለታቸው ነው።

የምግብ እጥረቱ ምን ያክል ከባድ እየሆነ ነው?

ከአጠቃላይ 49 ሚሊዮን ሱዳናውያን 18 ሚሊዮን የሚሆነው ሕዝብ ለከፍተኛ የምግብ እጥረት መጋለጡን የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባባሪያ ጽ/ቤት (ኦቻ) ይገልጻል።

የሱዳን ካርታ

“የአስር ሺዎች ሕይወት ሊቀጠፍ”

በሱዳን የኦቻ ኃላፊ የሆኑት ጀስቲን ብራዲ 4.9 ሚሊዮን ሰዎች አንደ ደረጃ ብቻ ለቀረው የረሃብ አደጋ መጋለጣቸውን ይናገራሉ።

“በቀጣይ ወራት ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ካነሰ ደግሞ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን በረሃብ አደጋ ሕይወታቸው ሊያልፍ ይችላል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“የዓለም መሪዎች አስቸኳይ የሆነ ትክክለኛ እርምጃ ሳይወስዱ መቅረታቸው፣ ቀድሞውኑ ከፍተኛ ተፈናቃይ ያለበት በመሆኑ በዓለማችን ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ ምክንያት ሆኗል” ያሉት ደግሞ የዓለም አቀፍ ጉዳዮችን ተንታኝ የሆኑት አኔት ሆፍማን ናቸው።

በአንዳንድ የካርቱም አካባቢዎች ነዋሪዎች ከዛፎች ላይ ቅጠል እየቀጠፉ መመገብ ጀምረዋል።

በሱዳን የጥራጥሬ ምርት በ40 በመቶ መቀነሱን የተመድ የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) አሃዝ ያሳያል።

የቀጣይ ሰብል ከሚሰበሰብበት ጊዜ ከመድረሱ በፊት ባሉት ሞቃታማ ወራት የረሃብ አደጋው እንደሚጨምር ይገመታል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደሚለው ግን ገበሬዎች የእርሻ መሬታቸውን ጥለው በመሄዳቸው ወይም ለዘር ያስቀመጡትን እህል በመመገባቸው መሬት ጾሙን እያደረ ስለሆነ ተዘርቶ የሚበቅል ነገር ባለመኖሩ በቀጣይ ሱዳን በመኅር ወቅት የምታጭደው እህል አይኖራትም ይላል።

የሱዳን ገበያ
የምስሉ መግለጫ,በሱዳን ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ የእህል ዋጋ በከፍተኛ መጠን ጨምሯል።

በአሁኑ ወቅት የምግብ እጥረት ብቻ አይደለም የተከሰተው። ያለውን ቢሆን ዋጋው በእጅጉ በመናሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሱዳናውያን እህል ለመግዛት አቅሙ የላቸውም።

የዓለም አቀፉ ገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ሪፖርት እንደሚጠቁመው ደግሞ ከአጠቃላይ ሕዝቡ ገሚሱ ሥራ አጥ ሆኗል።

የሱዳን የባንክ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ስለፈረሰ ጥሬ ገንዘብ ከባንክ ቅርንጫ ማውጣት አይቻልም። ወደ ሱዳን ገንዘብ መላክ እና መቀበል እጅግ አዳጋች ሆኗል።

በሱዳናውያን የአመጋገብ ባሕል ውስጥ መደበኛ የሚባሉት እንደ ሩዝ እና ምስር ዋጋቸው ከ400 እስከ 600 በመቶ ንሯል።

ግጭቱ የሰብዓዊ እርዳታ ማድረስን እጅግ አክብዶታል። ‘ሂዩማኒቴሪያን አውትካምስ’ የተባለው አማካሪ ድርጅት እንደሚለው፣ የሰብዓዊ እርዳታ ከሚያስፈልጋቸው አምስት ሱዳናውያን አንዱ ብቻ ነው እርዳታ እያገኘ የሚገኘው።

እርዳታ ድርጅቶች ምን ማድረግ ይችላሉ?

ሰብዓዊ ድርጅቶች ለምሳሌ እንደ ዳርፉር ባሉ ግዛቶች መሠረታዊ ቁሶችን ለማድረስ ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ፣ ከሌሎች የሚሊሻ ቡድኖች እና ከተደራጅቱ የወንጀል ቡድኖች ፍቃድ ለማግኘት ሳምንታት እንደሚወስድባቸው ይገልጻሉ።

የሱዳን ጦር የእርዳታ አቅርቦትን እየዘረፈ ያለው እና መንገድ እየዘጋ ያለው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ነው ይላል። ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በበኩሉ ይህ ሐሰት ነው በማለት ያስተባብላል።

የሱዳን መንግሥት ሰብዓዊ እርዳታ ለተጎጂዎች እንዲደርስ ጥረት እያደረኩ ነው ይላል።

ይሁን እንጂ የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች መንግሥት ያስተዋወቃቸው አዳዲስ መመሪያዎች የእርዳታ ሥርጭት ላይ እክል እየሆኑ ነው ይላሉ።

የምግብ እጥረት ያጋጠማቸው ሕጻናት።
የምስሉ መግለጫ,በመጠለያ ጣቢያ የሚገኙ በርካታ ሕጻናት የምግብ እጥረት ያጋጠማቸው ናቸው።

የዓለም የምግብ ደኅንንትን የሚከታተለው ስብስብ በካርቱም እና ዙሪያዋ የሚገኙ የማኅብረሰብ ክፍሎች ከፍተኛ የሆነ “የረሃብ አደጋ” አደጋ ተደቅኖባቸው ይላል።

ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ተዋጊዎች ባላንጣዎቻቸው የሚቆጣጠሯቸውን አካባቢዎች አቋርጠው የሚመጡ እርዳታዎችን አናሳልፍም በማለታቸው ነው።

ከጥቂት ወራት በፊት ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተቆጣጥሮ በያዛቸው አካባቢዎች ሰብዓዊ ድርጅቶች እርዳታ እንዲያቀርቡ ተማጽኖ አቅርቦ ነበር።

ይሁን እንጂ የሱዳን ጦር መሪ ጄኔራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሐን “እነዚህ ወንጀለኛ አማጺያን ተሸንፈው ጦርነቱ እስኪያበቃ ድረስ ይህ አይሆንም” ብለው ነበር።

“አፈር እየበሉ ያሉ ሕጻናት”

ከፍተኛ የምግብ እጥረት ካጋጠማቸው የሱዳን አካባቢዎች መካከል ሰሜን ዳርፉር ተጠቃሽ ነው። በዚህ አካባቢ ግማሽ ሚሊዮን ስደተኞችን የሚያስጠልል ዘምዘም የተባለ መጠለያ ጣቢያ ይገኛል።

ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን በመጠለያ ጣቢያ ከሚገኙ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ከሆኑ ሕጻናት ሲሶው ለከፍተኛ የምግብ እጥረት የተጋለጡ ናቸው ይላል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል በዘምዘም ያሉ የተራቡ ሕጻናት አፈር እየተመገቡ እንደሆነ ዘግቧል።