የጨቅላ ልጅ እግር

ከ 23 ደቂቃዎች በፊት

በተለያዩ ዓመታት ለንደን ከተማ ውስጥ መንገድ ላይ ተጥለው የተገኙ ጨቅላ ህጻናት የተመሳሳይ ወላጆች ያሏቸው በመሆናቸው እህት እና ወንድም እንደሆኑ በምርመራ ሲረጋገጥ፣ እናት እና አባታቸው በፖሊስ እየተፈለጉ ነው።

ይህ ይፋ የሆነው ከቅርብ ወራት በፊት በዩናይትድ ኪንግደም ለንደን ከተማ ውስጥ ተጥላ የተገኘች አንዲት ጨቅላ ከዚህ ቀደም ተጥለው የተገኙ ሁለት ልጆች እህት መሆኗ በተረጋገጠበት ጊዜ ነው።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሰሜናዊ ለንደን ተጥለው የተገኙት ሦስት ጨቅላዎች ከተመሳሳይ አባት እና እናት የተወለዱ መሆናቸውን የዲኤንኤ ምርመራ አረጋግጧል።

ምሥራቅ ለንድን ለሚገኘው ፍርድ ቤት የቀረበው የዘረ መል ምርመራ ውጤት ከአምስት ወራት በፊት ተጥላ የተገኘችው ጨቅላ፤ በመተሳሳይ ሁኔታ እአአ 2017 እና 2019 ላይ ተጥለው ከተገኙት ወንድ እና ሴት ልጆች ጋር ተመሳሳይ ወላጆችን እንደምትጋራ አሳይቷል።

የለንደን ፖሊስ በተለያዩ ጊዜያት ሦስት ጨቅላ ልጆቻቸውን ጥለው የጠፉትን ወላጆች ማንነት ለመለየት ያደረገው ጥረት እስካሁን አልተሳካም።

ቢቢሲ እና ፒኤ ሚዲያ ባለፉት 7 ዓመታት ተጥለው የተገኙት ልጆች ከተመሳሳይ እናት እና አባት የተወለዱ መሆናቸውን እንዲሁም ዘራቸው ጥቁር መሆኑን እንዲዘግቡ በፍርድ ቤት ተፈቅዶላቸዋል።

በቤተሰብ ጉዳዮች ላይ ፍርድ ቤትን የሚያማክረው የልጆች እና የቤተሰብ ጉዳዮች አገልግሎት፣ ሦስቱ ልጆች የሥጋ ዝምድና እንዳላቸው እንዳይዘገብ ጠይቆ ነበር።

ፖሊስ ደግሞ ልጆች ተጥለው የመገኘታቸው ዜና መሠራጨት ወላጆች ልጆችን ወልዶ መጣልን እንደማራጭ ሊያበራታታ ይችላል የሚል ስጋት ነበረው።

ይሁን እንጂ ቢቢሲ እና ፒኤ ሚዲያ የልጆቹ ተጥሎ የመገኘትን ጉዳይ ሕዝቡ የማወቅ ፍላጎት ይኖረዋል እንዲሁም ወላጆቹን ለመለየት ዘገባ መሥራቱ ለፖሊስ ሥራ ጠቃሚ ነው ብለው ተከራክረዋል።

ዳኛ ካሮል አትኪንሰን ሕዝቡ በጉዳዩ ላይ ፍላጎት እንደሚኖረው እና በዘመናዊ የብሪታኒያ ታሪክ ተጥለው የሚገኙ ልጆች ቁጥር በጣም ያነሰ በመሆኑ እንዲዘገብ ፈቅደዋል።

እአአ 2017 እና 2019 ላይ ተጥለው የተገኙት ወንድ እና ሴት ልጆች በማደጎ የተሰጡ ሲሆን፣ ኤልሳ የሚል ስያሜ የተሰጣት እና ከጥቂት ወራት በፊት ተጥላ የተገኘቸው ጨቅላ ግን በማሳደጊያ ቤት ውስጥ እንክብካቤ እየተደረገላት ትገኛለች።

ኤልሳ ከአምስት ወራት በፊት ነበር ከዜሮ ዲግሪ ሴንትግሬድ በሆነ ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ ውስጥ በፎጣ ተጠቅልላ ነበር የተገኘቸው።

ኤልሳ ተጥላ ስትገኘ እትብቷ እንኳ አለመቆረጡ እና ከተወለደች የሰዓታት ዕድሜ ብቻ እንደነበራት ሐኪሞች ገልጸዋል።

ጨቅላዋ ስትገኝ ሰውነቷ እጅጉን ቀዝቃዛ የነበረ ቢሆንም በተደረገላት የጤና ክትትል አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ አገግማ በጥሩ የጤና ሁኔታ ላይ ትገኛለች።

በተመሳሳይ ታላቅ ወንድም እና እህቷ በተለያዩ ዓመታት በምሥራቅ ለንደን አካባቢ በብርድ ልብስ ተጠቅልለው ነበር የተገኙት።

ሦስቱ ልጆች ወንድም እና እህት መሆናቸውን እንዲያውቁት እንደሚደረግ እና በእድገታቸው እንደአስፈላጊነቱ ግንኙነት እንዲኖራቸው እንደሚደረግ ተገልጿል።

ፖሊስ ተጥለው የተገኙትን የሦስቱን ልጆች ወላጆች ለመለየት ሕብረተሰቡ ጥቆማ በስጠት እንዲተባበረው ጠይቋል።