ፅዮን ታደሰ

June 5, 2024

የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር)

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለግብርና ዘርፍ አበድሮ ሊመለስለት ያልቻለ 4.97 ቢሊዮን ብር የተበላሸ ብድር እንደሚሰርዝ አስታወቀ።

ባንኩ ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት፣ መመለስ ካልተቻለው አጠቃላይ ብድር ወይም የተበላሸ ብድር መጠን ከፍተኛው ድርሻ የሚይዘውን የግብርና ዘርፍ ድርሻ ሊሰርዝ መሆኑ ተመላክቷል።

በመጋቢት ወር 2016 ዓ.ም. በተሰበሰበ መረጃ መሠረት ባንኩ በአጠቃላይ ማስመለስ ያልቻለው የተበላሸ ብድር መጠን 7.8 በመቶ መሆኑን፣ 73.2 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ የሚይዘው የግብርና ዘርፍ እንደሆነ በሪፖርቱ ተገልጿል። ከተመዘገበው አጠቃላይ የተበላሸ ብድር ውስጥ 5.16 በመቶ የሚሆነው በኪሳራ መያዙንና 3.9 ቢሊዮን ብር የሚሆነው በኪሳራ የተመዘገበ ብድር በግብርና ዘርፉ የተያዘ ነው ተብሏል።

ጤናማ ባልሆኑ ብድሮች ምክንያት በግብርናው ዘርፍ የተያዘው ያልተመለሰ ብድር የተፈጠረውም በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች፣ እንዲሁም ጎንደር አካባቢ ከሱዳን ድንበር ጋር በሚያዋስኑ አካባቢዎች መሆኑን ሪፖርቱ ያትታል። በዋናነት በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በዝናብ ላይ ጥገኛ የሆኑ የግብርና ፕሮጀክቶች ያልመለሱት የብድር መጠን ከፍ ያለ መሆኑንና ችግሩን ለመፍታትም ተገቢው የመሰረዝ ዕርምጃ አለመወሰዱ ተገልጿል።

በሁለቱ ክልሎች የተመዘገበው የተበላሸ ብድር ከፍ እንዲል ያደረገው፣ የብድር አጠቃቀሙ ላይ የነበሩ ችግሮች መሆናቸውን ያብራሩት የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር)፣ ‹‹የተሰጠው ገንዘብ የታለመለትን ዓላማ ስቶ የከተማ ሕንፃዎች እንዲሠሩበት መደረጉን በጥናት አረጋግጠናል፤›› ብለዋል። በዝናብ ለሚለማ መሬት ተብሎ ተሰጥቶ ካልተመለሰው የተበላሸ ብድር ምጣኔ ውጪ አሁን ያለው የተበላሸ ብድር 3.7 በመቶ ብቻ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ባለፉት ዘጠኝ ወራት 116 ፕሮጀክቶች ወደ ተበላሸ ብድር ክምች መግባታቸው በሪፖርቱ የተመላከተ ሲሆን፣ ጠቅላላ የብድር መጠናቸው 771.38 ሚሊዮን ብር የሆኑ 111 ብድሮች በዲስትሪክቶች ወደ ተበላሸ ብድር መግባታቸው ተመላክቷል። ከእነዚህም ውስጥ በፕሮጀክት ፋይናንሲንግ 666.40 ሚሊዮን ብር የብድር ክምችት ያላቸው፣ እንዲሁም በሊዝ ፋይናንሲንግ 104.98 ሚሊዮን ብር የብድር ክምችት ያላቸው ፕሮጀክቶች መሆናቸው በሪፖርቱ ተገልጿል።

ባንኩ ካካሄደው የለውጥ ሥራ በፊት በመንግሥት ጣልቃ ገብነት በትዕዛዝ አላግባብ ይሰጡ የነበሩ ብድሮች እንደነበሩ የገለጹት የባንኩ ፕሬዚዳንት፣ ባለፉት አምስት ዓመታት በተካሄዱ ሥራዎች 57 በመቶ የነበረውን ያልተመለሰ የብድር መጠን በአሁኑ ውቅት 7.8 በመቶ ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ባንኩ ከአጠቃላይ ሀብቱ አንፃር የትርፍ ግኝቱን 2.5 በመቶ ለማድረስ ዕቅድ ተይዞ ሲሠራ እንደነበርና በዘጠኝ ወራት 4.9 በመቶ ማድረስ መቻሉ በሪፖርቱ ተመላክቷል። በተጨማሪ በ2012 ዓ.ም. ባንኩ ያፀደቀው ብድር መጠን አሥር ቢሊዮን ብር እንደነበር ያስታወሱት ዮሐንስ (ዶ/ር)፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ግን 44.6 ቢሊዮን ብር ብድር ማፅደቁን አስታውቀዋል። ከዚህ ውስጥ ለአምራች ዘርፉ 30.5 ቢሊዮን ብር፣ ለግብርና ዘርፉ ደግሞ 6.3 ቢሊዮን ብር መሰጠቱን አስረድተዋል።

የባንኩ ዕዳ ተመላሽ ሳይደረግ በባንኩ ዋስትና የተመዘገበ መሬት ወደ ክልሎች መሬት ባንክ እንዲገባ እየተደረገ መሆኑን፣ የመሬት/ሼድ አቅርቦት ውስንነት፣ የመያዣ መብት መዝጋቢ አካላት በሕግ የተጣለባቸውን ኃላፊነት አለመወጣት፣ እንዲሁም በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል አለመኖር ባንኩ እያጋጠሙት ካሉ ችግሮች መካከል በሪፖርቱ የተጠቀሱ ናቸው።

የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ መሐመድ አብዶ (ፕሮፌሰር)፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ባንኩ ያከናወናቸውን ጠንካራ ሥራዎች ማስቀጠል እንዳለበት ገልጸው፣ ማኅበረሰብ ተኮር የሆኑ ተግባራትን ማከናወን እንደሚኖርበት ጠቁመዋል። አክለውም ከሌሎች የልማት ድርጅቶች ጋር በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።