ተመስገን ተጋፋው

June 5, 2024

ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድር የወሰዱ የትግራይ ክልል አንዳንድ ባለሀብቶች፣ በንብረታቸው ላይ ሐራጅ እየወጣባቸው መሆኑንና ሥጋት ውስጥ መውደቃቸውን፣ የትግራይ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

በትግራይ ክልል በጦርነቱ ንብረታቸው የወደመባቸው ባለሀብቶች እስካሁን መንግሥት ያለባቸውን ዕዳ እንዲሰርዝ ወይም አስፈላጊውን የሥራ ማስኬጃ ብድር እንዲመቻችላቸው ውሳኔ ባለማስተላለፉ፣ ባለሀብቶቹ የመኖሪያ ቤቶቻቸው በሐራጅ እንዳይሸጡ ሥጋት ውስጥ መውደቃቸውን የትግራይ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዳንኤል መኮንን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የትግራይ ክልል ባለሀብቶች ያለባቸውን ብድር ለመመለስ ተጨማሪ የጊዜ ገደብ እንዲሰጣቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚመራ ማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ ጋር ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

በክልሉ ጦርነት ከመከሰቱ በፊት በርካታ ባለሀብቶች ንብረታቸውን አስይዘው ብድር ማግኘታቸው የሚታወቅ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ ባለሀብቶቹ የወሰዱት ብድር እንዲመልሱ መንግሥት ምንም ዓይነት ሥርዓት ባለመዘርጋቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ በእጃቸው ያለ ንብረት እንዳይሸጥ ሥጋት እንዳደረባቸው አስረድተዋል፡፡

በጦርነቱ ወቅት ንብረቶቻቸው የወደሙባቸውን ሁለት ባለሀብቶችን ንብረት ለመሸጥ ልማት ባንክ በቅርቡ ሐራጅ ማውጣቱንና ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ ቤቶቻቸውን አስይዘው የተበደሩና በጦርነቱ ወቅት ሙሉ ለሙሉ ንብረታቸው የወደመባቸውም ባለሀብቶች የዚህ ዕጣ ፈንታ ተካፋይ እንደሚሆኑ አክለው ገልጸዋል፡፡

በትግራይ ክልል ንብረታቸው የወደመባቸው ባለሀብቶች በተመለከተ መንግሥት አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጥ በተደጋጋሚ መጠየቁን፣ ነገር ግን እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ምላሽ አለመሰጠቱንና ከአንድ ወር በላይ ማስቆጠሩን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ልማት ባንክ ብቻ ለሁለት ወይም ለሦስት ባለሀብቶች ብድር እየሰጡ መሆኑን መረጃ እንዳላቸው የተናገሩት ኮሚሽነሩ፣ ጉዳዩ በዚሁ ከቀጠለ የትግራይ የኢኮኖሚ ዕድገት በፍጥነት ይመለሳል ብሎ ማሰብ የማይቻል ነው ብለዋል፡፡

መጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሚመራው ማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ ወለድ ሙሉ ለሙሉ እንዳይታሰብ፣ እንዲሁም ባለሀብቶች ያለባቸውን ብድር ለመክፈል ሌላ ብድር እንዲመቻችላቸው ጥያቄ መቅረቡንና በሳምንቱም ምላሽ ይሰጥበት ተብሎ እንደነበር የትግራይ ክልል የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ፕሬዚዳንት አቶ አሸናፊ ኃይሉ ለሪፖርተር ተናግረው ነበር፡፡

በወቅቱም ባለሀብቶች ከተበደሩት ብድር ውጪ ወለድ ክፈሉ መባሉ አግባብ እንዳልሆነ የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ወለድን ጨምሮ የብድር ክፍያ የጊዜ ገደብና ሌሎች ጉዳዮች እንዲቀሩ ለብሔራዊ ባንክና ለገንዘብ ሚኒስቴር ደብዳቤ ማስገባታቸውን አክለዋል፡፡

በትግራይ ክልል ንብረታቸው የወደመባቸው ባለሀብቶች የብድር ሁኔታና ሐራጅ በተመለከተ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ምላሽ እንዲሰጥበት የተደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡