EOTC TV

የግንቦት 2016 ዓ/ም የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የማጠቃለያ መግለጫ ተሰጥቷል።

June 6, 2024 

የግንቦት 2016 ዓ/ም የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የማጠቃለያ መግለጫ ተሰጥቷል።

በዚሁ መግለጫ ቅዱስ ሲኖዶስ ፥ ” በመላው ሀገራችን በተፈጠሩ ግጭቶች፣ አለመግባባቶችና የሰላም ዕጦት በርካታ የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት እንደቀጠለ በመሆኑ በእጅጉ እናዝናለን ” ብሏል።

ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከግጭትና ከጥፋት ድርጊት ተቆጥበው የተፈጠረውን አለመግባባትና ግጭት በውይይትና በምክክር እንዲፈቱ እና ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ በአጽንኦት ጥሪ አቅርቧል።

በሌላ በኩል ቅዱስ ሲኖዶስ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አካሄድ ጋር በተያያዘ ቅሬታ እንዳለው ገልጿል።

” ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት አዋጅ መረዳት እንደሚቻለው ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ ሁኔታ ሀገራዊ ችግሮችን በምክክርና በውይይት ለመፍታት የተቋቋመ መሆኑን ተረድተናል ” ብሏል።

ይሁን እንጅ ” ሀገረ መንግሥትን ከመመሥረት ጀምሮ በአስታራቂነትና በሰላም ግንባታ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ለሆነችው እናት ቤተ ክርስቲያን እስከአሁን ድረስ በይፋ የቀረበ የተሳትፎ ጥሪ ሳይኖር ኮሚሽኑ የተሳታፊ ልየታንና አጀንዳ መረጣ አጠናቆ ወደ ምክክር ትግበራ እየገባ መሆኑ ቅር አሰኝቶናል ” ብሏል።

በመሆኑም የቤተ ክርስቲያኒቱ ተሳትፎና አጀንዳ የማቅረብ መብቷ እንዲረጋገጥ ከኮሚሽኑ ጋር በመነጋገር ጉዳዩን ተከታትሎ ለፍጻሜ የሚያበቃ ኮሚቴ ቅዱስ ሲኖዶስ መሰየሙን አሳውቋል።