
የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች የሚያደርጉት ፍተሻ በአብዛኛው ከስራ ሰዓት ውጭ መሆኑ ስጋት እና እንግልት ፈጥሯል ሲል ኢሰመጉ አሳሰበ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ዛሬ ባወጣው መግለጫ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች የሚያደርጉት ፍተሻ ህብረተሰቡን ስጋት ውስጥ የሚከት እና ለእንግልት የዳረገ ነው አለ።
መግለጫው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ምክንያት በማድረግ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተለይ በኦሮሚያ ክልል ፤በአማራ ክልል፤ በአዲስ አበባ ከተማ በመንግስት የፀጥታ አካላት ቤት ለቤት ፍተሻ እና ብርበራ ይደረጋል ተብሏል።
ፍተሻው በሚካሄድበት ጊዜ አንዳንድ ቦታዎች ፈታሾች ማንነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያም ሆነ ከየት እንደመጡ የሚገልጽ ማስረጃ እንዲሁም ከፍርድ ቤት የተሰጠ የብርበራ ፈቃድ እንደማያሳዩ እንዲሁም የብርበራው ሰዓት በአብዛኛው ከስራ ሰዓት ውጭ አንዳንዴም በሌሊት እንደሆነና በዚህም የተነሳ ማህበረሰቡ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደገባ እና ለከፍተኛ እንግልት እንደተጋለጠ ኢሰመጉ አረጋግጫለሁ ሲል አስታዉቋል።
ኢሰመጉ አክሎም በተለያዩ አካባቢዎች በመንገድ ላይ የሚፈጸሙ አላግባብ የገንዘብ ብዝበዛዎች እና እገታዎች መቀጠላቸውን ገልጾ መንግስት የዜጎችን ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት አክብሮ እንዲያስከብር ጥሪ አቅርቧል።
ግንቦት 18 ቀን 2016 በኦሮሚያ ክልል በኢሉባቡር ዞን በጉርዶም ድቻኖ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን በጊዜያዊነት በተሰጠ የአምልኮ ስፍራ የእምነቱ ተከታዮች ያልሆኑ ሰዎች ወደ አምልኮ ስፍራው በመግባት የአምልኮ ስፍራውን እንዳቃጠሉ እና የቤተ ክርስቲያኑን ንብረትም ያወደሙ መሆኑን አረጋግጫለሁ ሲል ኢሰመጉ ገልጿል።