የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አባላት
የምስሉ መግለጫ,የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አባላት

6 ሰኔ 2024, 14:12 EAT

የቤተከርስቲያኗን ጉዳይ እና ፍላጎትን በተመለከተ ከመንግሥት እና ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር የሚገናኝ ቡድን ማዋቀሩን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ገለጸ።

ሲኖዶሱ ይህንን እና ሌሎች ውሳኔዎቹን ያሳወቀው ከግንቦት 21 እስከ ግንቦት 28/2016 ዓ.ም. ድረስ ሲያካሂደው የቆየው የርክበ ካህናት መደበኛ ስብሰባውን ሲያጠናቅቅ ባወጣው መግለጫ ነው።

በስብሰባው መጀመሪያ ላይ ቤተክርስቲያኗ በአሁኑ ወቅት ከውስጥ እና ከውጭ በከባድ ፈተና ውስጥ መሆኗን የተናገሩት አቡነ ማቲያስ፣ ይህም ተልዕኮዋን በአግባቡ እንዳትወጣ እንቅፋት እየሆነባት መሆኑን ገልጸው እንደነበር ይታወሳል።

በተጠናቀቀው የሲኖዶሱ መደበኛ ስብሰባም በተለያዩ የቤተክርስቲያኗ ጉዳዮች ላይ በመምከር ውሳኔዎችን አሳልፏል።

ከእነዚህም መካከል ከመንግሥት ጋር ስለሚኖራት ግንኙነት እና በሀገራዊው ምክከር ውስጥ የሚኖራትን ሚና በተመለከተ ልዑክ ሰይሟል።

በዚህም በቤተ ክርስቲያንኗ እና በመንግሥት መካከል “ሊኖር ስለሚገባው መልካም የሥራ ግንኙነት” ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር “የሚመካከር” በቅዱስ ፓትርያርኩ የሚመራ ልዑክ በቅዱስ ሲኖዶስ መሰየሙ የተገለጸ ሲሆን፣ በምን ጉዳዮች ላይ እንደሚነጋገር ግን የተጠቀሰ ነገር የለም።

በተለያዩ ጊዜያት በቤተክርስቲያኗ እና በተከታዮችዋ ላይ ጥቃት መፈጸሙን እና መንግሥት አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርግ ቤተክርስቲያኗ ስትጠይቅ እንደነበር ይታወሳል።

በተጨማሪም ባለፈው ጥር ወር ማብቂያ ላይ ከአሜሪካ ሲመለሱ ወደ ሀገር እንዳይገቡ የተከለከሉት የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ እና የኒው ዮርክ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የአቡነ ጴጥሮስ ጉዳይም በእንጥልጥል ያለ ቤተክርስቲያኗ ለመንግሥት ጥያቄ ያቀረበችው መሆኑ ይታወቃል።

በተጨማሪም ሲኖዶሱ በመግለጫው ላይ በግልጽ ስም ባይጠቅስም የቅዱስ ሲኖዶስ አባል እና የምሥራቅ አውስትራሊያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት አቡነ ሉቃስ ያደረጉትን መንግሥትን ያስቆጣ አወዛጋቢ ንግግር በተመለከተ አቋሙን ገልጿል።

ሲኖዶሱ “በሀገራችን ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተፈጠሩ አለመግባባቶች የተከሰቱትን ወቅታዊ ችግሮች አስመልክቶ እየተላለፉ ያሉ ቤተ ክርስቲያንን የማይወክሉ መልዕክቶችን” እንደማይቀበላቸው እና በጥብቅ የሚቃወማቸው መሆኑን አሳውቋል።

ይህን ጳጳሱ ያደረጉት ንግግርን ተከትሎ፣ መንግሥት ቤተክርስቲያኗ በይፋ እንድታወግዝ ፍላጎት እንደነበረው በወቅቱ ሲገለጽ ነበር።

ዐቃቤ ሕግም በውጭ ሀገር በሚገኙት ጳጳስ ላይ ክስ መስርቶ ባለፈው ሳምንት የስድስት ዓመት ጽኑ እስራት በሌሉበት ተፈርዶባቸዋል።

በሀገሪቱ በሚፈጠሩ ግጭቶች፣ አለመግባባቶች እና የሰላም ዕጦት በርካታ የሰው ሕይወት መጥፋት እና የንብረት ውድመት መቀጠሉ እንዳሳዘነው ቅዱስ ሲኖዶስ፤ ለችግሮቹ በውይይት እና በምክክር መፍትሄ እንዲፈለግ ጥሪው አቅርቧል።

የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ እየተከናወነ ባለው ሥራ ውስጥ የበኩሏን አስተዋጽኦ እንድታደርግ የሚያስችል ጥሪ ሳይደረግላት “የተሳታፊ ልየታን እና የአጀንዳ መረጣ አጠናቆ ወደ ምክክር እየገባ መሆኑ” ቅር እንዳሰኘው በመግለጫው አመልክቷል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንድትሳተፍ እና “አጀንዳ የማቅረብ መብቷ እንዲረጋገጥ” ከኮሚሽኑ ጋር የሚነጋገር እና አስፈላጊውን ሥራ የሚያከናውን ኮሚቴ ቅዱስ ሲኖዶስ መሰየሙ ተገልጿል።