
6 ሰኔ 2024, 07:08 EAT
በአማራ ክልል ከተከሰተው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ የታሰሩ እንዲፈቱ፣ መደበኛ ሕግ ተግባራዊ እንዲሆን እና የእንቅስቃሴ ገደቦች እንዲነሱ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጠየቀ።
ባለፈው ዓመት ማብቂያ አካባቢ በአማራ ክልል ያለው የፋኖ ታጣቂዎች እንቅስቃሴ ከአቅሙ በላይ መሆን በመግለጽ የአማራ ክልል መስተዳደር የፌደራል መንግሥቱን ጣልቃ ገብነት መጠየቁን ተከትሎ የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተግባራዊነት ጊዜ ማብቃቱን ተከትሎ ነው ኮሚሽኑ ጥሪውን ያቀረበው።
ኢሰመኮ ባወጣው መግለጫ “በእስር ላይ የቆዩ ሰዎችን የመልቀቅ ሂደት እንዲቀጥል” መንግሥትን ያሳሰበ ሲሆን፣ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ የነበሩ ሁኔታዎች እንዲሻሻሉ “መደበኛው የሕግ ሂደት ተግባራዊ እንዲሆንም” ጠይቋል።
በተጨማሪም በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተጣሉ የእንቅስቃሴ ገደቦች እንዲነሱ እና ማኅበረሰባዊ አገልግሎቶች ሥራቸውን እንዲጀምሩ እንዲደረግ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽኑ ለመንግሥት ጥሪ አቅርቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ ለተለያዩ ጊዜያት በእስር ላይ የቆዩ ከ100 በላይ ግለሰቦች ላይ ትናንት ረቡዕ ግንቦት 28/2016 ዓ.ም. ክስ መመሥረቱ ተዘግቧል።
- በወልዲያ ከተማ የመንግሥት ኃላፊዎች ላይ ያነጣጠሩ ሦስት የቦምብ ጥቃቶች መፈጸማቸው ተነገረ5 ሰኔ 2024
- 10 ወራት ያስቆጠረው የአማራ ክልል ግጭት እና ሊጠናቀቅ የተቃረበው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ4 ሰኔ 2024
- በአዲስ አበባ የተገደለው የፋኖ አባል ሽኝት አስክሬን በሌለበት ጎንደር ውስጥ ተደረገ3 ሰኔ 2024
የፋኖ ታጣቂዎች ያካሄዱት በትጥቅ የተደገፈ እንቅስቃሴ የክልሉን ዋና ከተማ ባሕር ዳርን ጨምሮ በርካታ ከተሞች ላይ ስጋት በመፍጠሩ ነበር ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም. የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአማራ ክልል ላይ እና እንዳስፈላጊነቱ በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች ላይ የደነገገው።
የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት እና የፀጥታ ኃይሎች ወደ አማራ ክልል በማሰማራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተግባራዊ ያደረገ ሲሆን፣ ሕግ የማስከበሩ ሥራ ባለመጠናቀቁ በሚልም ድንጋጌው ለተጨማሪ አራት ወራት እንዲራዘም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መወሰኑ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ የምክር ቤት አባላትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ በሚገኙ እስር ቤቶች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት ለእስር ተዳርገው ቆይተዋል።
በዚህ ሳቢያ ከታሰሩ ሰዎች አብዛኞቹ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ እና ክስ ሳይመሠረትባቸው ለወራት በእስር ላይ ያሳለፉ ሲሆን፣ በተለያዩ ጊዜያት የተለቀቁም አሉ።
አንድ ዓመት ሊሞላው ሁለት ወራት የቀሩት በአማራ ክልል የተከሰተው አለመረጋጋት አሁንም መቋጫ ያላገኘ ሲሆን፣ ባለፉት ሳምንታትም በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭቶች እየተካሄዱ መሆናቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ።
አስካሁን በተካሄዱ ግጭቶች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንን ጨምሮ የተለያዩ ወገኖች በሚያወጧቸው መግለጫዎች ላይ ሪፖርት ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወቃል።
ኢሰመኮ በግጭቱ እየደረሰ ካለው ጉዳት ባሻገር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም በሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ያለውን ተጽዕኖ በተመለከተ ክትትል እና ምርመራ በማድረግ ሪፖርቶችን ሲያወጣ ቆይቷል።
መጀመሪያ ለስድስት ወራት ከዚያም ለአራት ወራት የተራዘመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ረቡዕ ግንቦት 28/2016 ዓ.ም. ያበቃ ቢሆንም፣ ከመንግሥት በኩል እስካሁን ድንጋጌው ባለበት ስለመቀጠሉም ሆነ የተግባራዊነት ጊዜው ስለማብቃቱ የተባለ ነገር የለም።