በጅምላ ለመቀበር የተዘጋጁ አሰክሬኖች
የምስሉ መግለጫ,ከጥቃቱ በኋላ በጅምላ ለመቀበር የተዘጋጁ አሰክሬኖች

ከ 1 ሰአት በፊት

በማዕከላዊ ሱዳን ከሀገሪቱ ጦር ጋር ውጊያ ላይ ያለው የሱዳን ፈጥኖ ዳራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) ተጠያቂ በተደረገበት የጅምላ ግድያ 35 ህጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 150 ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተዘገበ።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እና የሱዳን መንግሥት ጦር ሀገሪቱን ለመቆጣጠር የገቡበት ጦርነት 13ኛ ወሩን አስቆጥሯል።

አርኤስኤፍ በቀረበበት ክስ ላይ እስካሁን የሰጠው አስተያየት ባይኖርም ትላንት የሀገሪቱን ጦር ሁለት ይዞታዎች መውደሙን ገልጿል።

ከትላንት በስትያ ረቡዕ በጌዚራ ግዛት ዋድ አልኖራህ በተባለ አከባቢ ለቀብር የተዘጋጁ በነጭ ጨረቅ የተጠቀለሉ በርካታ አክሬኖችን በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጩ ቪዲዮዎች ላይ ታይተዋል።

በዚህ የጅምላ ግድያ 35 ህጻናት እንደሞቱ እና 20 ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው ዩኒሴፍ ገልጿል። የኤጀንሲው ኃላፊ ካትሪን ራሼል ሁኔታውን እጅግ የሚረብሽ ሲሉ ገልጸውታል።

ክስተቱ “የሱዳን ህጻናት በዚህ አሰቃቂ ጦርነት ምንያህል ዋጋ እየከፈሉ እንዳሉ ሌላ መጥፎ ማስታወሻ ነው” ሲሉም አክለዋል።

እንደ ኃላፊዋ ገለጻ ባለፉት ወራት በሱዳን በሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናት መገደላቸውን እና መጎዳታቸውን እንዲሁም ከ5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ከቤታቸው ለመሰደድ ተገደዋል። በተጨማሪም በርካታ ህጻናት ለጦርንት እንደተመለመሉ፣ እንደተጠለፉ እና እንደተደፈሩ ገልጸዋል።

ከትላንት በስትያ የተፈጸመው ይህ የጀምላ ግድያ እንዴት እንደተከሰተ ገልጽ አይደለም። የፍጥኖ ደራሽ ኃይሉ በአንድ ቀን ውስጥ ሁለት ጊዜ ግድያውን እንደፈጸመ ተነግሯል።

ጀስቲስ አፍሪካ የተሰኘው የሰብዓዊ እርዳታ ተቋም ባልደረባ ሀፊዝ ሞሀመድ አርኤስኤፍ አሁንም በአከባቢው ስለሚገኙ የሞቱ ሰዎችን መቁጠር አስቸጋሪ እንደሆነ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የሱዳን መንግሥት ይህንን ጥቃት ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ እንዲያወግዘው ጠይቋል።

የዩኬው ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቬድ ካሜሮን በኤክስ ገጻቸው “በንጹሃን ላይ የተፈጸመውን” ጥቃት ያወገዙ ሲሆን ተጠያቂው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ነው ብለዋል።

“ፍጥኖ ደራሽ ኃይሉ ይህንን አይነት ጥቃት ማቆመ አለበት። ዓለም እየተመለከተ ነው። ይህንን የፈጸሙት ይጠየቃሉ” ሲሉም አክለዋል።

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ከዋና ከተማዋ በዱቡባዊ አቅጣጫ በሚገኘው ተቆጣጥሮ በያዘው ጌዚራ ግዛት በርካታ ሲቪል ሰዎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚያደርስ ይነገራል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአርኤስኤፍ እና በሱዳን ጦር መካክል በምዕራባዊ የሀገሪቱ ክፍል በሚገኘው ኤል ፋሸር ዳርፉር ከተማ የሚያደረጉት ውጊያ ተጧጡፎ ቀጥሏል።

ከ13 ወራት በፊት በጀመረው ጦርነት ከ15 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች እንደተገደሉ ይታመናል።

ይህንን ጦርንት ለማክተም ተደጋጋሚ የሰላም ውይይቶች ቢደረጉም አንዳቸውም ፍሬ አላፈሩም።

የመንግሥታቱ ደርጅት ይህ ጦርነት የዓልም ከፍተኛ የተፈናቃይ ቀውስ እንዳስከተለ እና ሚሊዮኖችን ለርሃብ እንዳጋለጣው ገልጿል።

የድርጅቱ የሰብዓዊ ጉዳዮች ኃላፊ በሱዳን እስከ 5 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ርሃብ እንዳንዣበበባቸው ተናግረዋል።