
ከ 5 ሰአት በፊት
በሚሊዮን የሚቆጠሩ በመካከለኛ ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች እጅግ ከልክ ያለፈ ውፍረት እንዳላቸው በስህተት እንዲያምኑ ተደርገዋል ሲል በጣሊያን የተካሄደ ጥናት ይፋ አደረገ።
ጥናቱ ትኩረት ያደረገውም የሰውነት ክብደት ከቁመት አንጻር ሳይሆን በሰውነት ውስጥ በተካማጨ ስብ መጠን ላይ መሆኑን አመልክቷል።
ይህ በስብ መጠን ላይ የሚያተኩረው ከልክ ያለፈ ውፍረትን የመለካት አካሄድ በውፍረት ማን እንደተጎዳ ትክክለኛውን ምስል ይሰጣል ይላሉ ተመራማሪዎቹ።
ዕድሜ ሲጨምር ጡንቻ እየቀነሰ፣ በወገብ አካባቢ ስብ ቢከማችም ብዙውን ጊዜ በክብደት ላይ ለውጥ አይኖርም።
ፈተናው የሚሆው በቀላሉ ውፍረትን የሚለካ መሳሪያ ማግኘቱ ላይ ነው።
የሰዎችን ክብደት ለመለካት የሚኬድበት መደበኛው መንገድ ቢኤምአይን በማስላት ነው። ይህም የአንድን ሰው ክብደት በኪሎ ግራም መዝኖ ከቁመቱ አንጻር በማስላት ምን ያህል ተመጣጣኝ መሆኑ የሚለካበት ነው።
ይህም ሲሰላ ለምሳሌ አንድ ሰው ቁመቱ 1.52 ሜትር ቢሆን 1.52ን በ1.52 እናባዛለን (2.31 ሜትር ይሆናል)። በመቀጠል ለሰውየው ክብደት (60 ኪሎ ቢሆን) እናካፍልበታለን። በዚህም 60ን በ2.31 በማካፈል የግለሰቡ አጠቃላይ የሰውነት መጠን ይዞታ አመላካች (ቢኤምአይ) 25.96 መሆኑን እንደርስበታለን።
- ከ18.5 – 25 ቢኤምአይ ጤናማ ክብደትን እንደሚጠቁም ይነገራል
- ከ25 – 29 ቢኤምአይ ያላቸው ከመጠን በላይ ወፍራም የሚባሉ ናቸው
- 30 እና ከዚያ በላይ የሆኑት ደግሞ ከልክ ያለፈ ውፍረት የሚባለው ውስጥ ይካተታሉ።
- ማጨስን ያገዱ አገራት የትኞቹ ናቸው? እነዚህ እገዳዎችስ ምን ውጤት አስገኙ?30 ግንቦት 2024
- አስጊው የወንድ ብልት ካንሰር9 ግንቦት 2024
- ብዙ ንጥረ-ነገሮች የሚጨመሩባቸው በፋብሪካ የሚቀነባበሩ ምግቦች እና በጤና ላይ የሚያስከትሉት ጠንቅ30 መጋቢት 2024
አማራጭ ፍለጋ
ይህም የሰውነትን ውፍረት ሁኔታ ለማወቅ ፈጣን እና ቀላል ዘዴ ከመሆን ባለፈ በዓለም ጤና ድርጅት የተደገፈ መንገድ ነው።
ነገር ግን ይህ ስሌት የብዙ ሰዎችን ትክክለኛ ውጤት ቢያሳውቅም በስብ፣ በጡንቻ እና በአጥንት መካከል ያለውን ልዩነት ማሳየት ግን አይችልም።
በሮም በሚገኘው የቶር ቬርጋታ ዩኒቨርሲቲ የተመራው እና በአውሮፓ በውፍረት ላይ በተካሄደው ኮንግረስ ላይ በቀረበው እና ዕድሜያቸው ከ40 እስከ 80 የሆናቸው 4800 ሰዎች ላይ የተደረገ ጥናት የሰውነት ስብ በመቶኛ የሚታይበት ተጨማሪ አማራጭን አቅርቧል።
በዚህ የልኬት ዘዴ ከወንዶች 38 በመቶዎቹ እና ከሴቶች ደግሞ 41 በመቶዎቹ ከ30 በላይ ቢኤምአይ የነበራቸው ቢሆንም የሰውነታቸው ስብ በመቶኛ ሲሰላ 71 በመቶ እና 64 በመቶው መሆኑ ታይቷል።
“የዓለም ጤና ድርጅትን መስፈርት መጠቀማችንን ከቀጠልን ብዙ ጎልማሶች እና አዛውንቶች ውፍረት-ነክ ለሆኑ እንደ የስኳር በሽታ፣ የልብ ህመም እና አንዳንድ የካንሰር ዓይነቶች መጋለጣቸውን ላንመለከት እንችላለን” ሲሉ የጥናቱ ተባባሪ የሆኑት ፕሮፌሰር አንቶኒኖ ዲ ሎሬንዞ ተናግረዋል።
ወደፊት 27 ቢኤምአይ ከልክ ያለፈ ውፍረትን ለመለየት ጥቅም ላይ መዋል አለበትም ብለዋል ተመራማሪዎቹ።
ፕሮፌሰር ዴ ሎሬንዞ አክለውም “ይህን አዲስ የቢኤምአይ መስፈርት መጠቀም ከመጠን በላይ ውፍረትን ለመከላከል እና በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች ጤና ጠቃሚ ይሆናል” ብለዋል።
‘ቀላል መሣሪያ’
ጥናቱ ባለፉት ዓመታት ለቢኤምአይ የተለየ መቁረጫ ነጥብን ከጠቆሙት ውስጥ አንዱ ነው።
ሆኖም ቢኤምአይ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከጥቅም ውጪ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም። የሰውነት ውስጥ ያለ ስብን በትክክል ለመለካት ከሚደረገው ሂደት አንጻርም በጣም ርካሹ መንገድ ነው።
ውጤቱን ለማረጋገጥ በሌሎች አገራት ሰፊ ጥናቶች እንደሚያስፈልጉ ተመራማሪዎቹ አምነዋል። ይህ ጥናት በጣሊያን አንድ ክልል ያሉ አዋቂዎች ላይ ብቻ አተኩሯል። በሰዎች አካል ውስጥ ያለውን የስብ ሥርጭት ሳይሆን በስብ የተሠራውን የሰውነት ክፍል መቶኛ ብቻ አስቀምጧል።
አንዳንድ ሰዎች ለምን ከሌሎቹ በበለጠ ለውፍረት ሊጋለጡ እንደሚችሉ ለመለየት ስለአመጋገባቸው ወይም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ልምዶቻቸው አልጠየቀም።
የሰውነት ስብ በራሱ ትክክለኛ መለኪያ መሆን አለመሆኑም ግልጽ አይደለም ተብሏል።
የሞዴና እና የሬጂዮ ኤሚሊያ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር እና የጥናቱ ተባባሪ የሆኑት ማርዋን ኤል ጎች “በማንኛውም ሰው ሊገኝ የሚችለውን ውፍረትን ለመለየት ቀላል የሆነ መሣሪያ እንፈልጋለን” ብለዋል።
የግላስጎው ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ናቪድ ሳታር በበኩላቸው “ውፍረትን ለመለየት ቢኤምአይን ወደ 27 ከመቀነስ ይልቅ ከመጠን በላይ ክብደት ያላቸው ሰዎችን ልዩ ማሳያዎች እና ምልክቶች የበለጠ መረጃ ሰጪ ሊሆኑ ይችላሉ” ብለዋል።