ጥቃት የደረሰበት ትምህርት ቤት

ከ 4 ሰአት በፊት

ሐሙስ ማለዳ ተፈናቃዮች በተጠለሉበት የማዕከላዊ ጋዛ ትምህርት ቤት በርካታ ሕጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 35 ሰዎችን ተገድለውበታል ስለተባለው የአየር ጥቃት እስራኤል ሙሉ በሙሉ “ግልጽ” መሆን እንዳለባት አሜሪካ አሰሰበች።

የአካባቢው ጋዜጠኞች ለቢቢሲ እንደተናገሩት አንድ የጦር አውሮፕላን በኑሴይራት ከተማ የስደተኞች መጠለያ በመሆን በሚያገለግለው ትምህርት ቤት የላይኛው ወለል ላይ በሚገኙ የመማሪያ ክፍሎች ላይ ሁለት ሚሳኤሎችን መተኮሱን ተናግረዋል።

የእስራኤል ጦር በትምህርት ቤቱ ውስጥ በሚገኘው “የሐማስ ግቢ” ላይ “ዒላማውን የጠበቀ” ጥቃት አድርሻለሁ ቢልም በጋዛ የሚገኘው እና በሐማስ የሚመራው የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ይህን አስተባብሏል።

እስራኤል ገድያለሁ ያለቻቸውን የሐማስ ተዋጊዎች በይፋ ማንነታቸውን እንድታስታውቅ አሜሪካ ጠይቃለች።

እስራኤላውያን “ዒላማ ያደረጉባቸው ከ20 እስከ 30 የሚደርሱ ታጣቂዎች እንዳሉ ነግረውናል። ገድለናል ብለው ያሰቧቸውን ታጣቂዎች ስም ይፋ ያደርጋሉ” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር ጠይቀዋል።

“እናሳውቀዋለን ያሉትም ይህንን ነው። ያን እንዲያደርጉ እና በክስተቱ ዙሪያ ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችንም እንጠብቃለን” ብለዋል።

የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ዳንኤል ሃጋሪ በተመሳሳይ ጊዜ በሰጡት መግለጫ በጥቃቱ ተገድለዋል ያሏቸውን ዘጠኝ የሐማስ እና የእስልሚክ ጂሃድ ተዋጊዎችን ስም ይፋ አድርገዋል። “መረጃውን የማጣራት” ሥራ ከተሠራ በኋላ ተጨማሪ መረጃ እንደሚገለጽ ተናግረዋል።

ሚለር በበኩላቸው በጥቃቱ 14 ህጻናት መገደላቸውን የሚገልጹ ሪፖርቶችን አይተናል ብለዋል።

“14 ህጻናት መገደላቸው ትክክል ከሆነ አሸባሪዎች አይደሉም ማለት ነው” ብለዋል።

የአካባቢው ጋዜጠኞች እና ነዋሪዎች እንደተናገሩት የአሁኑ ጥቃት የተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲ የሆነው አንርዋ በርካታ ስደተኞች ተጠልለው ድጋፍ በሚሰጥበት አል-ሰርዲ ትምህርት ቤት ላይ ነው።

በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ የተጋሩ ቪዲዮዎች እንደሚያሳዩት የትምህርት ቤቱ ህንጻ ውስጥ የሚገኙ በርካታ የመማሪያ ክፍሎች ከመጎዳታቸውም ባላይ በርከታ አስከሬኖች ተሸፍነው ይታያሉ።

የሞቱ እና የቆሰሉ ሰዎች ወደ አል-አቅሳ ሰማዕታት ሆስፒታል ተወስደዋል።

ቢቢሲ በኑሴይራት ካምፕ የደረሰውን ጥቃት ለማጣራት እየሠራ ነው። የሟቾችን ትክክለኛ ቁጥር በተመለከተ የሚወጡ ዘገባዎች የተለያዩ ናቸው።

በጥቃቱ ቦታ ሃዘናቸው የሚገልጹ ሰዎች

በጋዛ በሐማስ የሚመራ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር 14 ህጻናት እና ዘጠኝ ሴቶችን ጨምሮ 40 ሰዎች መሞታቸውን እና 74 ደግሞ ቆስለዋል ብሏል።

የአንርዋ ዋና ኮሚሽነር ፊሊፕ ላዛሪኒ በበኩላቸው ቢያንስ 35 ሰዎች መገደላቸውን እና በርካቶች መቁሰላቸውን ተናግረዋል። የኤጀንሲው የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ጁሊየት ቱማ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ቁጥሩ የተገኘው በስፈራው ከሚገኙ “የአንርዋ ባልደረቦች” ነው።

ጥቃቱን ተከትሎ የደረሰውን ውድመት የዓይን እማኞች ገልጸዋል።

በትምህርት ቤቱ የሚኖረው ኡዳይ አቡ ኤልያስ “ጥቃቱ ሲፈጸም ተኝቼ ነበር” ሲል ለቢቢሲ አረብኛ ተናግሯል።

“ድንገት ከፍተኛ ፍንዳታ ሰማን። እናም የተሰባበረ መስታወት እና የህንጻው ፍርስራሽ በላያችን ላይ ወደቀ። ጭስ አየሩን ስለሞላው ምንም ነገር ማየት አልቻልኩም። በህይወት እተርፋለሁ ብዬ አልጠበኩም። አንድ ሰው በሕይወት የተረፉ ሰዎች እንዲወጡ ሲጣራ ሰማሁ። ብዙ ሰማዕት የሆኑ ሰዎች ወድቀው ስለነበር ለመመልከት ተቸግሬ ነበር።”

አንርዋ በወቅቱ ስድስት ሺህ ተፈናቃዮች በትምህርት ቤቱ ግቢ ውስጥ ተጠልለው ነበር ብሏል።

1.7 ሚሊዮን ሰዎች ትምህርት ቤቶችን እና ሌሎች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቋማትን እንደ መጠለያ ተጠቅመዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ጥቃቱን በቃል አቀባያቸው በኩል አውግዘዋል።