
ከ 4 ሰአት በፊት
ሶማሊያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆና ተመረጠች።
በጦርነት ስትታመስ ለኖረችው ምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር የምክር ቤቱ አባል ሆና መመረጧ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል ተደርጎ ተወስዶላታል።
ሶማሊያ ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ከመግባቷ በፊት እአአ በ1970ዎቹ የምክር ቤቱ ተለዋጭ አባል ነበረች።
ሶማሊያ የምክር ቤቱ አባል መሆኗ ከጽንፈኛው እስላማዊ ቡድን አል-ሸባብ ጋር የምታደርገውን ውጊያ በተመለከተ ለተመድ ውሳኔ ግብዓት ትሆናለች።
የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት በመላው ዓለም ለሚፈጠሩ ግጭቶች ዓለም ምን አይነት ምላሽ መስጠት እንዳለበት ይወስናል።
የጸጥታው ምክር ቤት ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው አምስት ቋሚ አባላት ያሉት ሲሆን በየሁለት ዓመቱ የሚለዋወጡ 10 ተለዋጭ አባል አገራት አሉት።
አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ቻይና እና ሩሲያ ቋሚ አባላት ናቸው። ሶማሊያ ለቀጣይ ሁለት ዓመታት ተለዋጭ አባል ሆና እንድታገለግል ከዴንማርክ፣ ግሪክ፣ ፓኪስታን እና ፓናማ ጋር ተመርጣለች።
አንድ አገር ተለዋጭ አባል ሆኖ ለመመረጥ ቢያንስ በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የሁለት ሦስተኛ አባል አገራት ድጋፍን ማግኘት ይኖርበታል።
- የኢትዮጵያ ሠራዊት ከሶማሊያ መውጣት ለአልሻባብ የመጠናከር ዕድል ይፈጥራል?ከ 5 ሰአት በፊት
- እስካሁን ጥቅም ላይ ሲውል የነበረው ከልክ ያለፈ ውፍረትን የመለኪያ ዘዴ የተሳሳተ ነው ተባለከ 5 ሰአት በፊት
- ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከመንግሥት እና ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር የሚነጋገር ቡድን ሰየመች6 ሰኔ 2024
ሶማሊያ ይህን መቀመጫ ያገኘችው ለምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የተቀመጠውን ወንበር ያለተቀናቃኝ ከወሰደች በኋላ ሲሆን፤ ከ193 አባል አገራት የ179 ድምጽ ማግኘት ችላለች።
ሶማሊያ ያገኘችውን ድል ተከትሎ የልዑካን ቡድንን መርተው ወደ ኒው ዮርክ ያቀኑት የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሕመድ ፊቅ አገራቸው “በዓለም አቀፉ መድረክ የተሰጣትን ቦታ ትረከባለች” ብለዋል።
“በዓለማችን ሰላም እና ደኅንነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሶማሊያ የተሰጣትን ሚና ለመውጣት ዝግጁ ነች” ሲሉም አክለዋል።
እአአ 1991 ላይ የቀድሞ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ሲያድ ባሬ ከስልጣን መወገድን ተከትሎ ሶማሊያዊያን በጎሳ ተከፋፍለው ለበርካታ ዓመታት የእርስ በእስር ጦርነት ውስጥ መቆየታቸው ይታወቃል።
ባለፉት ዓመታት ተመድ እና የአፍሪካ ኅብረት በአገሪቱ ሰላም እና መረጋጋትን ለማስፈን እንዲሁም ማዕከላቂ መንግሥትን ለማቋቋም ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ለአል-ቃይዳ አጋርነቱን የገለጸው እና አሁንም ድረስ በርካታ የሶማሊያ አካባቢዎችን የሚያስተዳድረው አል-ሸባብ ለአገሪቱ መረጋጋት ትልቅ ስጋት ሆኖ የቀጠለ ቡድን ነው።

አል-ሸባብ የአገሪቱን መንግሥት በኃይል ከስልጣን አውርዶ በራሱ ጥብቅ እስላማዊ ሕግ ትርጓሜ አገሪቱን ማስተዳደር ይፈልጋል።
በቅርብ ወራትም ከማዕከላዊ መንግሥት ጋር የሚያደርገውን ትግል አጠናክሮ ቀጥሏል።
የተመድ ዋና ጸሐፊ የሶማሊያ ልዩ ተወካይ የሆኑት ጄምስ ስዋን አገሪቱ ሰላምን በማስከበር ሂደት ውስጥ ያላት ልምድ ለጸጥታው ምክር ቤት ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል።
“ሶማሊያ ሰላም፣ ልማት እና ደኅንነት ለማረጋገጥ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ብዙ ርቀት ተጉዛለች” ብለዋል።
የጸጥታው ምክር ቤት ሰላም አስከባሪ ኃይሎችን ማሰማራትን እና ዓለም አቀፍ ማዕቀቦችን መጣል የሚጨምር ትልቅ ስልጣን አለው።
ምክር ቤቱ ለበርካታ ዓመታት ሶማሊያ ላይ ጥሎት የነበረውን የጦር መሳሪያ ዝውውር በቅርቡ ማንሳቱ ይታወሳል።
ቋሚ ያልሆኑ የምክር ቤቱ አባላት የሚሰይሙት ከተለያዩ የዓለማችን ቀጠናዎች ሲሆን አገራቱ እንደ አምስቱ ቋሚ አባል አገራት ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት የላቸውም።
የአፍሪካ ኅብረት ከአፍሪካ የተወከለ አገር የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል እንዲሆን ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።