
ከ 36 ደቂቃዎች በፊት
በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ላይ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ሲሰሙ፣ በእነ አቶ ዮሐንስ ቧያለው መዝገብ ስር ያሉ ተከሳሾች ደግሞ የክስ መቃወሚያቸውን አቀረቡ።
ፀረ ሰላም ኃይሎችን በመደገፍ እና ጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት በሚል የተከሰሱት የቀድሞው የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ታዬ ደንዳአ ላይ የዐቃቤ ሕግ የሰው ምስክሮች ተሰምተዋል።
ሐሙስ ግንቦት 29/2016 ዓ.ም. የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሕገ መንግሥት እና የሽብር ወንጀል ችሎት ዐቃቤ ሕግ በአቶ ታዬ ላይ ያቀረባቸውን የሁለት ምስክሮች ቃልን ተቀብሏል።
አቶ ታዬ በችሎቱ ላይ ታራሚዎች የሚለብሱትን ቢጫ ልብስ ልብሰው የዐቃቤ ሕግ በተሰሙበት ችሎት ላይ ከጠበቃቸው ጋር ተገኝተዋል።
ሁለቱ ግለሰቦች ቃላቸውን የሰጡት ከጦር መሳሪያ ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ ግለሰቦቹ የአቶ ታዬ መኖሪያ ቤት በፖሊስ ሲፈተሽ በስፍራው የነበሩ የዐይን እማኞች ናቸው ተብሏል።
የአቶ ታዬ ጠበቃ ግን ምስክሮቹ በሁለት ምክንያቶች ቃላቸውን መስጠት የለባቸውም ሲሉ ተከራክረዋል። ጠበቃው ምስክርነት ለመስጠት ከቀረቡበት መካከል አንዷ በክስ ላይ “ወ/ሮ” ተብለው ተጠቅሰው ሳለ ችሎት ላይ የቀረቡት ግን ወንድ ናቸው ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪም የምስክሮቹ አድራሻን በተመለከተ ልዩነት ስላለ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ቃላቸውን መስጠት የለባቸውም ብለዋል።
ይሁን እንጂ ፍርድ ቤቱ የምስክሮቹን መታወቂያ ከተመለከተ በኋላ ቃላቸውን ተቀብሎ ውሳኔ ለምስጠት ለሰኔ 18/2016 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
- የኢትዮጵያ ሠራዊት ከሶማሊያ መውጣት ለአልሻባብ የመጠናከር ዕድል ይፈጥራል?ከ 5 ሰአት በፊት
- እነ አርቲስት አማኑኤል ሀብታሙ ‘ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን በትጥቅ ትግል ለመቀየር’ በመንቀሳቀስ ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ቀረቡ6 ሰኔ 2024
- በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታሰሩ እንዲፈቱ እና የእንቅስቃሴ ገደቦች እንዲነሱ ኢሰመኮ ጠየቀ6 ሰኔ 2024
የአቶ ታዬ ቅሬታ
በችሎቱ ማብቂያ ላይ አቶ ታዬ ደንዳአ ለዳኞች ቅሬታቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም አቤቱታ ያቀረቡበት የእርሳቸው እና የባለቤታቸው የባንክ አካውንት አሁንም እንዳይንቀሳቀስ ተዘግቶ ስለሚገኝ ቤተሰባቸው በችግር ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
ችሎቱም የባንክ ሂሳባቸው የታገደው የፌደራል ፍርድ ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በመሆኑ ለዚያ ፍርድ ቤት አቤቱታቸውን እንዲያቀርቡ አዟል።
አቶ ታዬ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ሆነው በመንግሥት ውስጥ የሚፈጸሙ ተገቢ አይደሉም የሚሏቸውን ድርጊቶች ለመገናኛ ብዙኃን በመናገር እና በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በማስፈር ይታወቃሉ።
የቀድሞው ባለሥልጣን በቀጥታ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጻፈ የስንብት ደብዳቤ ከኃላፊነታቸው በተነሱበት ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩን አጥብቆ የሚያወግዝ ጽሁፍ በፌስቡክ ላይ አስፍረው ነበር።
አቶ ታዬ ከሥልጣን መነሳታቸው ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የተቹበትን ጽሁፍ ካሰፈሩ ከሰዓታት በኋላ ነበር በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር የዋሉት።
የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አባል የሆኑት የቀድሞ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ታዬ ደንዳአ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በምክር ቤቱ ያለመከሰስ መብታቸው መነሳቱ ይታወሳል።
የክስ መቃወሚያ
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሌላ የፍርድ ቤት ውሎ በእነ አቶ ዮሐንስ ቧያለው መዝገብ የተከሰሱ 52 ተከሳሾች ሐሙስ ግንቦት 29/2016 ዓ.ም. የክስ መቃወሚያቸውን ለፍርድ ቤት በጽሁፍ አቅርበዋል።
በ12 ገጾች የተዘጋጀው መቃወሚያው የቀረበው መዝገቡን እየተመለከተው ለሚገኘው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የሕገ መንግሥት እና የሽብር ወንጀል ችሎት ነው።
ተከሳሾች መቃወሚያ ያቀረቡበት የመጀመሪያው ጉዳይ ከዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ጥበቃ ጋር የተያያዘ ነው።
ዐቃቤ ሕግ በክስ ሠነዱ ላይ “ለምስክሮች ጥበቃ” ማደረጉን አስፍሯል። ተከሳሾች በመቃወሚያቸው “[ዐቃቤ ሕግ] በራሱ ጊዜ የተከሳሾችን ራሳቸውን የመከላከል መብት በሚያጣብብ መልኩ ያደረገው ክልከላ ተነስቶ የምስክሮች ዝርዝር እንዲደርሰን እንዲረግልን እናመለክታለን” ብለዋል።
ሌላኛው መቃወሚያ አንደኛ ተከሳሽ ሆነው የቀረቡትን አቶ ዮሐንስ ቧያለው የሚመለከት ነው። አቶ ዮሐንስ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል በመሆናቸው ያላቸው ያለመከከስ መብት አለመነሳቱ በመቃወሚያው ላይ ተጠቅሷል።
ሕገ መንግሥቱ “ማንኛውም የፌደሬሽን ምክር ቤት አባል ከባድ ወንጀል ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በስተቀር ያለ ምክር ቤቱ ፈቃድ አይያዝም በወንጀል አይከሰስም” ይላል።
ይህን የሕገ መንግሥት ድንጋጌ የጠቀሰው የተከሳሾች መቃወሚያ፤ “በ1ኛ ተከሳሽ ላይ የቀረበው የወንጀል ክስ ተቋርጦ ከእስር እንዲፈቱ” የሚል ጥያቄ አቅርቧል።
ተከሳሾች ጉዳያቸውን እየተመለከተ ከሚገኘው ፍርድ ቤት የዳኝነት ሥልጣን ጋር የተያያዘ መቃወሚያም አቅርበዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ቀዳሚው የተከሳሾች መቃወሚያ፤ “ፍርድ ቤቱ አማራዊ ማንነትን ለመዳኘት ሥልጣን [የለውም]” የሚል ነው።
የችሎቱ ሥልጣን
በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ በተወሰኑ ተከሳሾች ላይ “የአስተዳደር አካባቢ የዳኝነት ሥልጣን የለውም” የሚል መቃወሚያ ቀርቧል።
ወንጀሉ ተፈጸመ የተባለው በአማራ ክልል መሆኑን ያስታወሱት ተከሳሾች፤ “ይህን ጉዳይ ለማየት ሥልጣን ያለው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነው በማለት ጉዳዩን ወደ አማራ ክልል እንዲልከው በማክበር እንጠይቀለን” ብለዋል።
“ክሱ ግልጽነት የጎደለው እና በአግባቡ ራሳችንን ለመከላከል የማያስችለን [ነው]” ያሉት ተከሳሾች፤ “ዐቃቤ ሕግ ክሱን አሻሽሎ በተገቢ ግልጽነት አዘጋጅቶ እንዲቀርብ እንዲታዘዝልን” ሲሉ ጠይቀዋል።
ተከሳሾች አክለውም “ዐቃቤ ሕግ ክሱን ለማሻሻል የማይችል ወይም የማይፈልግ ቢሆን ክሱ ዋጋ እንደማይኖረው ሕግ የሚደነግግ ስለሆነ የተከበረው ፍርድ ቤት መዝገቡን ዘግቶ ከክሱ እንዲያሰናብተን በማክበር እንጠይቃለን” ብለዋል።
ዐቃቤ ሕግ በእነ አቶ ዮሐንስ ቧያለው ላይ ከሁለት ወራት በፊት በመሠረተው ክስ ተፈጸመ ባለው ወንጀል ከ1100 በላይ የፀጥታ እና የሲቪል ሰዎች መሞታቸውን እና ሌሎች ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጾ ነበር።
ተከሳሾች በመቃወሚያቸው ላይ “እንዴት አድርገን ይህን ጉዳት እንዲከሰት እንዳደረግን ክሱ የማያስረዳ በመሆኑ፣ የመከላከል መብታችንን የሚጋፋ በመሆኑ ክሱ ተስተካክሎ እንዲቀርብ፤ ይህ ባይሆን ደግሞ ክሱ ዋጋ የለውም እንዲባል” ጠይቀዋል።
ችሎቱ በቀረበው ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለሰኔ 12/2016 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቶ ተነስቷል።