
6 ሰኔ 2024
አርቲስት አማኑኤል ሀብታሙ፣ የቴአትር አዘጋጅ ዳግማዊ ፈይሳ እና በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ታዋቂ የሆነችው ፍላጎት አብርሃምን ጨምሮ 20 ግለሰቦች “ገንዘብ ለሽብር ቡድን ሎጂስቲክ መግዣ ለማዋል” እንዲሁም “ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን በትጥቅ ትግል ለመቀየር” በመንቀሳቀስ ተጠርጥረው ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀረቡ።
ጉዳዩን የተመለከተው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት፤ በተጠርጣሪዎቹ ላይ 13 የምርመራ ቀናት እንደፈቀደ ጠበቃ አያሌው ቢታኔ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከ10 እስከ 70 ቀናት በእስር ላይ የቆዩት ተጠርጣሪዎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረቡት ትናንት ረቡዕ ግንቦት 28/2016 ዓ.ም. ከሰዓት እንደሆነ ጠበቃው አስረድተዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መሥሪያ ቤት በሚገኘው ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ከታሰሩት ተጠርጣሪዎች ውስጥ ተዋናይ አማኑኤል ሀብታሙ ይገኝበታል። በ2006 ዓ.ም. ለዕይታ በቀረበው “ረቡኒ” ፊልም ላይ በነበረው ትወና ለመጀመሪያ ጊዜ ለዕውቅና የበቃው አርቲስት አማኑኤል፤ በተለያዩ ፊልም እና ቲያትሮች ላይ ተሳትፏል።
የአርቲስቱ የመጨረሻ ሥራ “እብደት በሕብረት” የተሰኘው ባለአንድ ሰው ቴአትር ሲሆን ሚያዝያ 14/2016 ዓ.ም. በቁጥጥር ስር የዋለውም ይህንኑ ሥራውን በእስራኤል ሀገር ለማቅረብ ሊጓዝ በነበረበት ወቅት ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ነው።
የዚሁ ቴአትር አዘጋጅ ዳግማዊ ፈይሳ ደግሞ ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት በተመሳሳይ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሏል። አንጋፋ የኪነ ጥበብ ባለሙያ ዳግማዊ፤ ለዕይታ ካበቃቸው ሥራዎቹ ውስጥ “የቃቄ ውርድወት” እንዲሁም አርቲስት አማኑኤል የተወነበት “የኮከቡ ሰው” የተሰኙት ቴአትሮች ተጠቃሽ ናቸው።
- ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከመንግሥት እና ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር የሚነጋገር ቡድን ሰየመች6 ሰኔ 2024
- በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታሰሩ እንዲፈቱ እና የእንቅስቃሴ ገደቦች እንዲነሱ ኢሰመኮ ጠየቀ6 ሰኔ 2024
- በወልዲያ ከተማ የመንግሥት ኃላፊዎች ላይ ያነጣጠሩ ሦስት የቦምብ ጥቃቶች መፈጸማቸው ተነገረ5 ሰኔ 2024
ከኪነ ጥበብ ባለሙያዎቹ ጋር በአንድ ላይ የቀረበችው ሌላኛዋ በሕዝብ ዘንድ እውቅና ያላት ግለሰብ፤ “የልጅ ማኛ” በሚለው የማኅበራዊ ሚዲያ ስሟ የምትታወቀው ፍላጎት አብርሃም ነች። የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪነቷ እና የቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢነቷ የምትታወቀው ፍላጎት፤ ቲክቶክ በተሰኘው የቪድዮ ማጋሪያ መተግበሪያ ላይ 600 ሺህ ገደማ ተከታዮች አሏት።
ፍላጎት፤ ባለፈው ዓመት በተካሄደው ዘጠነኛው የጉማ አዋርድ ላይ ከታየችበት ትዕምርታዊ መልዕክት አስተላላፊ ሜክአፕ እና ልብስ እንዲሁም በዕለቱ የፕሮግራሙ አዘጋጅ ዮናስ ብርሃነ መዋ ከመታሰሩ ጋር ተያይዞ የብዙዎችን ትኩረት ስባ ነበር።
በፕሮግራሙ ላይ የለበሰችው ሜክ አፕ ግንባሯ ላይ በጥይት የተመታች እና እንዳትናገር ከንፈሯን የተሰፋች የሚያስመስል ሲሆን፣ ያደረግችው ነጭ ቀሚስ ደግሞ ከስሩ የኢትዮጵያ ሰንደቅ የሚታይበት ነበር።
ከእነዚህ ታዋቂ ሰዎች ባሻገር የፖሊስ ማዕረግ ያላቸው አምስት ግለሰቦች፤ ከሃያዎቹ ተጠርጣሪዎች ውስጥ እንደተካተቱ በረቡዕ የችሎት ውሎ ላይ የመርማሪ ፖሊስ ባቀረበው የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ላይ ተዘርዝሯል።
አማኑኤል፣ ፍላጎት እና ያሬድ ገብረፃዲቅ (በማኅበራዊ ሚዲያ ስሙ ያያ ዘልደታ) በሦስት ጠበቃዎች እንደተወከሉ ጠበቃ አያሌው ገልጸዋል። ሌሎች ሦስት ጠበቃዎች ደግሞ አዘጋጁን ዳግማዊን እና ሌሎች ሁለት ተጠርጣሪዎችን በተናጠል እንደወከሉ ጠቅሰዋል።
ሌሎቹ ተጠርጣሪዎች ያለ ጠበቃ መቅረባቸውን የሚናገሩት አቶ አያሌው፤ በዚህ ምክንያት ሦስቱ የእነ አማኑኤል ጠበቆች “ከሙያዊ ግዴታ” በመነሳት የተቀሩትንም ግለሰቦች መወከላቸውን ገልጸዋል።

መርማሪ ፖሊስ፤ “ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም [አዲስ አበባ] ከተማ ውስጥ ‘ቦንብ ሊፈነዳ ነው፣ ሽብር ጥቃት ሊደርስ ነው’ የሚሉ አሸባሪ መረጃዎችን በማጋራት የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት የሚያውክ ተግባር ፈጽመዋል” በማለት ሃያዎቹ ግለሰቦች የተጠረጠሩበትን ጉዳይ ለችሎቱ ማስረዳቱን ጠበቃው አስታውቀዋል።
ተጠርጣሪዎቹ፤ “ገንዘብ ለሽብር ቡድኑ ሎጀስቲክስ መግዣ ለማዋል ሕገ መንግሥቱን እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል፣ በትጥቅ ለመቀየር ሲንቀሳቀሱ” እንደተገኙም በመርማሪ ፖሊስ ማመልከቻ ላይ ተጠቅሷል።
በአዲስ አበባ ከተማ “ከፍተኛ ሁከት እና ብጥብጥ እንዲነሳ” በአማራ ክልል ካለ “ፅንፈኛ ቡድን ተልዕኮ” ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ እንደነበርም ማመልከቻው ላይ ሰፍሯል።
መርማሪ ፖሊስ የተጠርጣሪዎችን ስልክ እና ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች በብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ለማስመርመር እንዲሁም አባሪዎቻቸውን ለመያዝ 14 የምርመራ ቀናት እንዲፈቀድለት ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ ማቅረቡን ጠበቃው አስረድተዋል።
ተጠርጣሪዎቹን የወከሉት ጠበቆች በበኩላቸው ከ10 እስከ 70 ቀናት በእስር ላይ መቆየታቸውን በመጥቀስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መጠየቁ የሚያሳየው “ፖሊስ ሥራውን አለመሥራቱን ነው” በሚል ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ መከራከራቸውን አቶ አያሌው ገልጸዋል። “ደንበኞቻችን በእስር ላይ የቆዩባቸው ቀናቶች ማስረጃዎችን አጠናቅሮ ለመምጣት፣ ክስም ለመመሥረት ከበቂ በላይ ነው” ሲሉም መቃወማቸውን አስታውሰዋል።
ሃያዎቹ ግለሰቦች የፈጸመዋል የተባለው ወንጀል በተናጠል አለመዘርዘሩም በመከራከሪያነት መቅረቡን የሚናገሩት አቶ አያሌው፤ “የሽብር ቡድን” ተብሎ የተጠቀሰው አካል የትኛው እንደሆነ ግልፅ አለመሆኑንም ጠበቆች ለፍርድ ቤቱ ማስረዳታቸውን ጠቅሰዋል።
ጠበቃው፤ “የሽብር ጉዳይ ከሆነ ፍርድ ቤቱ ይህንን ጉዳይ የማየት የሥረ ነገር ሥልጣን የለውም። በሽብር ሕጉ ምንም አይነት የሽብር ጉዳዮችን የጊዜ ቀጠሮም ቢሆን የማየት ሥልጣን ያለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው” ማለታቸውን ተናግረዋል።
ጉዳዩ ሁከት እና ብጥብጥን የሚመለከት ከሆነ ደግሞ ይህ ዓይነቱ ጉዳይ “የዋስትና መብትን የሚያስከለክል አይደለም” የሚል መከራከሪያ በማቅረብ የተጠርጣሪዎቹ የዋስትና መብት እንዲከበር መጠየቁን ገልጸዋል።
ጠበቆች የፍርድ ቤቱን ሥልጣን በተመለከተ ላነሱ መከራከሪያ መርማሪ ፖሊስ፤ “እኛ ማቅረብ ያለብን ክስ ነው። በሽብር ነው ወይም በሁከት እና ብጥብጥ ነው የሚለውን የመለየት ሚና የዐቃቤ ሕግ ነው” ሲል ምላሽ መስጠቱን አቶ አያሌው ተናግረዋል።
የተጠርጣሪዎቹ ድርጊት ተነጣጥሎ አልቀረበም የሚለውን መከራከሪያ በተመለከተ ደግሞ በሁሉም ተጠርጣሪዎች ላይ ማስረጃዎች ማደራጀቱን መርማሪ ፖሊስ ገልጿል ተብሏል።
የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት፤ መርማሪ ፖሊስ ከጠየቀው 14 የምርመራ ቀን ውስጥ 13 ቀን መፍቀዱን ጠበቃው አቶ አያሌው ገልጸዋል።