የሁቲ ታጣቂዎች
የምስሉ መግለጫ,የሁቲ ታጣቂዎች የየመንን መዲና ሰንዓን እና የአገሪቷን ሰሜን ምዕራብ ክፍል ይቆጣጠራሉ።

ከ 6 ሰአት በፊት

የተባበሩት መንግሥታት በየመን በሁቲ አማጺያን የተያዙ 11 ሠራተኞቹ በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ጠየቀ።

ሠራተኞቹ የጦርነት ቀጠና ከሆነችው የመን የተቀናጀ በሚመስል ሁኔታ ከተለያዩ አካባቢዎች መወሰዳቸውንም ድርጅቱ ገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪች እንዳሉት ድርጅቱ የሠራተኞቹን ደኅንነት ለማረጋገጥ እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ለማድረግ የሚቻለውን ሁሉ እያደረገ ነው።

ታጣቂው ቡድን ራሱን በኢራን የሚመራው የአማጺ ክንፍ አድርጎ የሚመለከት ሲሆን እስራኤልን ፣ አሜሪካን እና ምዕራባውያንን በመቃወም በጋዛ ለፍልስጤማውያን ድጋፍ እንደሚያደረግ ገልጿል።

ሁቲዎች ከዚህ ቀደም በቀይ ባሕር ላይ የንግድ መርከቦችን ኢላማ ያደረጉ ሲሆን ይህም አሜሪካ እና አጋሮቿ የአጸፋ ምላሽ ለመስጠት የአየር ጥቃት እንዲፈፅሙ ምክንያት ሆኗል።

በየመን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው መንግሥት ባለሥልጣናትን ዋቢ በማድረግ የሚወጡ ዘገባዎችም የሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በርካታ ሠራተኞችም በአማጺው ቁጥጥር ሥር እንደሚገኙ አመልክተዋል።

የሁቲ ታጣቂዎች በቀይ ባሕር ላይ በንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት ከሰነዘሩ ከወራት በኋላ በሠራተኞቹ መኖሪያ ቤት እና ቢሮ ላይ በፈፀሙት ወረራ ስልኮችን እና ኮምፒዩተሮችን ወስደዋል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ማዩ እንዳለው የሁቲ የደኅንነት ሰዎች በተመሳሳይ ሰዓት በአምራን፣ ሁዳይዳህ ፣ ሳዳ እና ሰንዓ የሚሰሩ 18 የሰብዓዊ እርዳታ ሠራተኞችን ኢላማ አድርገዋል።

በአሜሪካ የሚደገፈው ‘ናሽናል ዴሞክራቲክ ኢንስቲቲዩት (ኤንዲአይ) አባላትም ኢላማ እንደነበሩ ባለሥልጣናት ለሮይተርስ የዜና ወኪል ገልጸዋል።

የሠራተኞቹ መታሰር በአገሪቷ ከ150 ሺህ በላይ ሰዎችን በገደለው፣ አስከፊ የሰብዓዊ ቀውስ ባስከተለውና ከአስር ዓመታት በላይ በቆየው የእርስ በእርስ ጦርነት የእርዳታ ሠራተኞች እየተጋፈጡት ያለውን አደጋ የሚያሳይ ነው።

የሠራተኞቹ መያዝ የተሰማውም ሁቲዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመጣው የኢኮኖሚ ችግር እየተፈተኑ እና በአሜሪካ በሚመራው ጥምር ኃይል የአየር ጥቃት እየደረሰባቸው ባለበት ወቅት ነው።

ታጣቂው ቡድን የየመንን መዲና ሰንዓን እና የአገሪቷን ሰሜን ምዕራብ አካባቢ የተቆጣጠረ ሲሆን ከነዋሪዎች ግብር ይሰበስባል፤ገንዘብም ያትማል።

ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው የየመን መንግሥት ደግሞ በአገሪቷ ደቡባዊ የወደብ ከተማ ኤደን መቀመጫውን አደርጓል።