ሜላኒ ሬይድ

ከ 7 ሰአት በፊት

14 ዓመታት ወደ ኋላ እንመለስ። ሜላኒ ሬይድ ፈረስ ስትጋልብ በደረሰባት አደጋ አንገቷ ይሰበራል። ግራ እጇም “እንደ ሙዝ ተቆልምሞ” አልታዘዝ ይላታል።

ዕድሜ ለኤሌክትሪክ ንዝረት ይሁንና ግራ እጇን ተጠቅማ ስልክ መደወል እንዲሁም ቀበቶዋን ማሰር እና መፍታትም ተችሏታል።

ይህ ዘዴ ከፊዚዮቴራፒ ጋር ተዳምሮ ከአንገት በታች ሽባ ለሆኑ ሰዎች በተወሰነ ደረጃ መፍትሔ የሆነ ይመስላል። በ60 ታካሚዎች ላይ በተደረገ ጥናት 43ቱ የእጃቸው አጠቃቀም ላይ መጠነኛ መሻሻል ታይቷል።

ቡድኑ በአሜሪካ ባሉ ሆስፒታሎች ውስጥ ታካሚዎችን ለማከም ዘዴውን እንዲጠቀም ቁጥጥር የሚደረግበት ፍቃድ ለማግኘት ጠይቋል።

ይህም ዘዴ በተጎዳው አካባቢ ኤሌክትሮዶችን በመጠቀም የሚተገበር ነው። ከፍተኛ ድግግሞሽ ያለው የኤሌክትሪክ ንዝረት ወደ ሰውነት ይላካል። ልክ አእምሯችን ወደ እጃችን ነርቮች የሚልከውን ዓይነት ንዝረት ማለት ነው። ሜላኒን በአከርካሪዋ ጉዳት ምክንያት ይህ አእምሮ ሥርዓቷ ተዳክሟል።

በስኮትላንድ ውስጥ በስተርሊንግሻየር የምትኖረው የ67 ዓመቷ ሜላኒ የታይምስ ጋዜጠኛ ናት። አዲሱን ዘዴ ለመሞከር ከታደሉ ከመጀመሪያዎቹ ታካሚዎች አንዷ ነች። የእጆቿ እንቅስቃሴ ተገድቧል። በተለይም የግራ እጇን ምንም ማንቀሳቀስ አትችልም ነበር።

ለሁለት ወራት የኤሌክትሪክ ንዝረት እና ከፍተኛ የፊዚዮቴራፒ እንዲሰጣት ተደረገ። ይህም በዕለት ተዕለት ሕይወቷ ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጡ አንዳንድ ጥቃቅን ማሻሻያዎችን ማምጣቱን ትናገራለች።

“የመኪና ወንበር ቀበቶዬን በግራ አውራ ጣቴ መፍታት እችላለሁ። ይህ እጄ አንድ ሲኒ ቡና እንደሚያነሳ ለማመን በቅቻለሁ። ትንንሽ ነገሮችን እንደ ማንሳት ያሉ ተግባራትን ማከናወን እችላለሁ” ብላለች።

ምሥል

በሙከራው ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ መሳሪያው ተገጥሞላቸው ሰዎች ተጨማሪ እንቅስቃሴ ማድርግ ቢችሉም፣ ያለመሳሪያው ድጋፍ ምን ያህል እንደሚንቀሳቀሱ እስካሁን ለመናገር አይቻልም። ከፊዚዮቴራፒ እና ከመሳሪያው የተገኘውን ውጤት ለየብቻ ማወቅም አልተቻለም።

“አንድን ሰው ጥናቱ ውስጥ በማካተት ለብዙ ወራት ትኩረት ሲሰጡበት የተወሰነ መሻሻል ይኖራል” ሲሉ በለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የኒውሮሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት ሮበርት ብራውንስተን ተናግረዋል።

ከፊዚዮቴራፒው በተጨማሪ የተስፋ እና ተጨማሪ ድጋፍ ማግኘት በህክምናው ውስጥ ለውጥ ሊያመጣ ይችላልም ብለዋል።

ሜላኒ መሳሪያው ሲገጠምላት ብቻ ልታደርጋቸው የምትችላቸው እንደ እቃ ማንሳት ያሉ አንዳንድ ነገሮች እንዳሉ ተናግራለች። ህክምናው ዘላቂ የሆነ የጥንካሬ መሻሻል እንዳደረገላትም ይሰማታል።

“መሻሻሉ የመጣው በኤሌክትሪክ ንዝረቱ ብቻ አይደለም። ሆኖም ግን በመሳሪያው የተፋጠነ እና የተሻሻለ እንደሆነ ይሰማኛል” ብለዋል።

“በአከርካሪ አጥንት ላይ ምንም ዓይነት ተአምር ባይፈጠርም [ግን] ይህ መሳሪያ ምግብ ለመጉረስ ወይም ውሃ ለመጠጣት ከረዳ ሕይወትን የሚለውጥ ነው” ብላለች።”

የአከርካሪ ጉዳት ያለባቸው ታካሚዎች ከጉዳታቸው በኋላ በፍጥነት ህክምና ከጀመሩ በተሻለ ሁኔታ መሻሻል የሳያሉ። ለጥናቱ የተመረጡት ከአንድ እና 34 ዓመታት በፊት አደጋ ያጋጠማቸው ናቸው። በተጨማሪም አነስተኛ ወይም ምንም መሻሻል ያላሳዩም መሆን ይጠበቅባቸዋል።

በግላስጎው በሚገኘው የኩዊን ኤልዛቤት ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል የኢኖቬሽን ማዕከል የጥናት ዳይሬክተር የሆኑት ማሪኤል ፐርሴል ከ14 ዓመት በፊት ጀምሮ ሜላኒን ሲያክሙ ቆይተዋል።

ማዕከሉ ለጥናቱ የተጋበዘው በዘርፉ በዓለም ደረጃ ቀዳሚ የምርምር ማዕከል በመሆኑ ነው።

የኤሌክትሪክ ንዝረቱ ቀደም ሲል ስባ ለሆኑ ሰዎች ጥቅም ላይ ይውል ነበር

ከዚህ በፊት ይህን ያህል ለቆየ ህመም እንደዚህ አይነት መሻሻል አይታ እንደማታውቅ ትናግራለች።

“በአሁኑ ጊዜ ፈቃድ ያገኘ እና ለታካሚዎች የሚሰጥ አንድም መድኃኒት ወይም መሳሪያ የለም” ብላለች።

መሳሪያው በሎዛን በሚገኘው የኢፒኤፍኤል የሕክምና ምርምር ላብራቶሪ ባልደረባ በፕሮፌሰር ግሬጎየር ኮርትይን ተባባሪነት የሚመራ የስዊትዘርላንድ ቡድን ውጤት ነው።

እስካሁን ድረስ ከአንገት በታች የአከርካሪ ጉዳት የደረሰባቸው 26 ሰዎችን አከርካሪ የሚያነቃቁ በቀዶ ሕክምና የሚተከሉ መሳሪያዎችን በመጠቀም እንደገና እንዲራመዱ ረድተዋል። ይህ ሁሉ የሆነው ግን በቤተ ሙከራ ደረጃ ብቻ ነው።

ምንም ዓይነት ቀዶ ሕክምና የማያስፈልገው አዲሱ አሠራር የቡድኑ የመጀመሪያ ምርምር ሲሆን፣ አንገታቸው ተሰብሮ እጃቸው አልንቀሳቀስ ላላቸው ሰዎችም ሕክምና ለመስጠት የሚያግዝ ነው።

ፕሮፌሰር ኮርቲን የኤሌክትሪክ ንዝረቱ ከፊዚዮቴራፒ ጋር ተዳምሮ የተጎዱትን ነርቮች እንደሚያድስ የሚያሳይ ጽሑፍ አሳትመዋል።

“ለእነዚህ ታካሚዎች ሕይወትን የሚቀይር ቴክኖሎጂ ለማምጣት በጣም ተቃርበናል” ሲል ለቢቢሲ ኒውስ ተናግረዋል።

የአሜሪካው የምግብ እና የመድኃኒት አስተዳደር (ኤፍዲኤ) በበኩሉ ቴክኒኩ ደኅንነቱ የተጠበቀ መሆኑን እና አለመሆኑን ለመገምገም በኔቸር ሜዲሲን መጽሔት ላይ ታትሞ ከወጣው ክሊኒካዊ ጥናት የተገኘውን መረጃ በማጥናት ላይ ይገኛል።

ኤጀንሲው በውጤቱ ከረካ በአሜሪካ ሆስፒታሎች ውስጥ ጥቅም ላይ እንዲውል ለሕክምና መሳሪያው ፍቃድ ይሰጣል።

መሳሪያው በአሜሪካ ውስጥ ፈቃድ ካገኘ ቴክኖሎጂው በሌሎች የዓለም ክፍሎችም ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቃድ ይጠየቅበታል ተብሎ ይጠበቃል።