
ከ 6 ሰአት በፊት
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእስራኤል ጦር በህጻናት ላይ ጥሰቶችን በሚፈጽሙ ዝርዝር ውስጥ እንዲካተት ውሳኔ አስተላለፈ።
የመንግሥታቱ ድርጅት ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው ከመስከረም 26 በኋላ በጋዛ በእስራኤል ጥቃት የተገደሉ ህጻናት ከ15 ሺህ 500 በላይ መሆናቸው ከተገለጸ በኋላ ነው።
የእስራኤል ጦር ህጻናትን ከጉዳት መከላከል ባለመቻሉ በጥሰት ፈጻሚነት ዝርዝር ውስጥ መካተቱን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእስራኤል አምባሳደር ተናግረዋል።
አርብ ዕለት ውሳኔው እንደደረሳቸው የገለጹት አምባሳደር ጊላድ ኤርዳን እርምጃውን “አሳፋሪ” ሲሉ ነው የገለጹት።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እስራኤል ካትስ በበኩላቸው “እስራኤል ከተባበሩት መንግሥታት ጋር ባላት ግንኙነት ላይ መዘዝ የሚያስከትል ነው” ብለውታል።
የፍልስጤም ፕሬዚዳንት ቃለ አቀባይ የተባበሩት መንግሥታት ውሳኔ እስራኤል ለፈጸመቻቸው ወንጀሎች አንዱ ተጠያቂ የሚያደርጋት ነው ሲሉ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
እስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ በሐማስ ላይ እያካሄድኩት ነው በምትለው የተቀናጀ ጥቃት በሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናት እና ሴቶች ተገድለዋል።
- እስራኤል በዌስት ባንክ በአንድ ሕጻን ላይ የፈጸመችው ግድያ የጦር ወንጀል ሊኾን እንደሚችል የቢቢሲ ምርመራ አመላከተ3 ግንቦት 2024
- ፍልስጤማዊው ዶክተር በእስራኤል እስር ቤት ህይወታቸው አለፈ4 ግንቦት 2024
- የጋዛው ትልቁ ሆስፒታል በአስከሬኖች እንደተጨናነቀ ተገለጸ14 ህዳር 2023
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ይፋ ያደረጉት ዝርዝር በባለፈው ዓመት በግጭት ውስጥ የተገደሉ ህጻናትን፣ የእርዳታ አቅርቦትን ክልከላ እና ትምህርት ቤቶች እና ሆስፒታሎችን ኢላማዎች ያደረጉ ጥቃቶችን ይዟል።
ዝርዝሩም በሚቀጥለው ሳምንት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በሚቀርበው ሪፖርት ውስጥ ይካተታል።
ሐማስ እና የፍልስጤም እስላማዊ ጂሃድ በዝርዝሩ ውስጥ እንደሚካተቱ ዘገባዎች ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የተባበሩት መንግሥታትን ውሳኔ በማውገዝ ራሱን “በጥቁር የታሪክ መዝገብ” ውስጥ አስፍሯል ሲሉ ወቅሰውታል። አክለውም የእስራኤል ጦር “በዓለም ላይ ካሉት በሞራል ልዕልና የላቀ ሰራዊት ነው” ሲሉ አሞካሽተውታል።
እስራኤል በጋዛ ውስጥ እየፈጸመችው ባለው ጥቃት ከ34 ሺህ 180 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውንም በሐማስ አስተዳደር ስር ካለው የጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ አመልክቷል።
ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በደቡባዊ እስራኤል ውስጥ በፈጸመው ጥቃት 1 ሺህ 200 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 253 ታጋቾች ተወስደዋል።