የኤኤንሲ ደጋፊዎች

ከ 7 ሰአት በፊት

የጨቋኙ የአፓርታይድ ሥርዓት መገርሰስ ለሰውነታቸው መታወቂያ ሲታገሉ ለነበሩ ደቡብ አፍሪካውያን የነጻነት ችቦን የፈነጠቀ ነበር።

ከሰው በታች አድርጎ በቆዳ ቀለማቸው ምክንያት ያወረዳቸውን፣ ክብርን የነፈጋቸውን ሥርዓት ታግለው የጣሉበት ድል ነው።

የበርካታ ጥቁሮች ተስፋ በለመለመበት የመጀመሪያው ምርጫ የነጻነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ ወደ ሥልጣን መጡ።

ደቡብ አፍሪካውያንም የነጻነት ተምሳሌት ያደረጉት የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኤኤንሲ) ሥልጣን ጨበጠ።

የአዲሱን የጥቁሮች የብዙኃን መንግሥት መመሥረትን ተከትሎ ደቡብ አፍሪካውያን ብቻ ሳይሆኑ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የሌሎች አገራት ዜጎችም ለተሻለ ኑሮ ዐይናቸውን ወደ አዲሲቷ አገር ማማተር ጀመሩ።

በርካታ ኢትዮጵያውያን የጆሃንስበርግ ጂፒ ጎዳናን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች የንግድ ማዕከላትን መቆጣጠር ችለዋል።

ነገር ግን ጥቁር የአገሪቱ ዜጎች ተስፋ የጣሉበት ሥርዓት የገባውን ቃል ማሳካት ባለመቻሉ፣ እንዲሁም ከድህነት አረንቋ ማውጣት ባለመቻሉ ችግሩ መጤ በተባሉት የሌሎች አገር ዜጎች ላይ መሳበብ ጀመረ።

በቅርብ ዓመታት ውስጥ መጤ በተባሉት አፍሪካውያን ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ተፈጽመዋል። እንዲሁም መጤ ጠል የሆኑ ትርክቶችም በተለይም በቅርቡ በተደረገው ምርጫ ቅስቀሳ ወቅትም ተሰምተዋል።

ታሪካዊ በተባለው የደቡብ አፍሪካ ምርጫ የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኤኤንሲ) አብላጫ ድምጽ ማጣቱን ተከትሎ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ተጣምሮ የጋራ መንግሥት መመሥረት ግድ ሆኖበታል።

የጋራ መንግሥት ምሥረታው ቅራኔያቸው የማይታረቅ በሚመስለው በበርካታ ነጮች በሚደገፈው ዲሞክራቲክ አሊያንስ በተባለው ፓርቲ እና ጥቁሮችን ለማብቃት በሚታገለው ኤኤንሲ መካከል ጥምረት ቢፈጠር ምን ይሆናል? የሚለው በርካቶችን ግራ አጋብቷል።

የአገሪቱ የወደፊቱ ዕጣ ፈንታ ጥያቄ የፈጠረባቸው የደቡብ አፍሪካ ዜጎችን ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ ውስጥ በተለያዩ ሥራ ላይ የተሰማሩ የሚገኙ የውጭ አገር ዜጎችን ነው።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ አዲሱ ኤምኬ ፓርቲ በከፍተኛ ሁኔታ ድል ባገኘበት በክዋዙሉ ናታል ግዛት፣ ደርባን ከተማ ነዋሪ የሆነው ኢትዮጵያዊው ኮስሞስ ገብረ ሚካኤል የጥምር መንግሥቱ በውጭ አገር ሠራተኞች ላይ ባነጣጠሩ ጥቃቶች ዙሪያ ይህን ያህል ለውጥ ያመጣል ብሎ እንደማያምን ለቢቢሲ ተናግሯል።

ለዓመታት ያህል ሲንከባለል የመጣው የመጤዎች ጥላቻ አሁንም ሰፍኗል የሚለው ኮስሞስ፤ በአዲሱ መንግሥት ምሥረታ ማግስት ይህን ያህል ነገሮች ይቀየራሉ ብሎ እንደማያስብ ነው የሚናገረው።

ኮስሞስ የበለጠ ትኩረት የሰጠው ደቡብ አፍሪካ ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮንቬንሽን ስምምነቶች እንድትወጣ ዕቅድ የያዘው እና አወዛጋቢ የተባለው የአገሪቱ የኢሚግሬሽን ማሻሻያ ረቂቅ ሕግ ላይ ነው።

በአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር አሮን ሞትሶአሌዶ የቀረበው ይህ ረቂቅ የአገሪቱ የኢሚግሬሽን ሕግጋት ጠበቅ ያሉ እንዲሆኑ እና የዜግነት እንዲሁም የጥገኝነት ሂደቶችን ማሻሻያዎችን ይዟል።

“ጥምር መንግሥቱ ሲመሠረት የአሁኑ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር በሥልጣን ላይ እንደማይሆኑ ተስፋ እናደርጋለን፣ እያንዳንዱ ስደተኛ ይህንን እየጠበቀ ነው” ብሏል።

አክሎም “ለእኔ ትልቁ ስጋት ይህ ነው። አሁን ካለው የከፋ የስደተኛ ሕጎች አልጠብቅም” ሲል ለቢቢሲ አስረድቷል።

ከ17 ዓመታት በፊት ወደ ደቡብ አፍሪካ የመጣው እና በአስተርጓሚነት ስራ ተሰማርቶ የሚገኘው ኮስሞስ
የምስሉ መግለጫ,ከ17 ዓመታት በፊት ወደ ደቡብ አፍሪካ የመጣው እና በአስተርጓሚነት ሥራ ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው ኮስሞስ

ከ17 ዓመታት በፊት ወደ ደቡብ አፍሪካ የመጣው እና በአስተርጓሚነት ሥራ ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው ኮስሞስ፣ መጪውን ጥምር መንግሥት በጥንቃቄ እንደሚያየው ይናገራል።

በተለይም የቀኝ አክራሪ የሚባለው ፓትሪየቲክ አሊያንስ እና አክሽን ሳውዝ አፍሪካ የተሰኙት ፓርቲዎች በስደተኞች ላይ ያላቸውን ዕይታ “በጣም አደገኛ” ሲል ነው ኮስሞስ የሚገልጸው።

ኮስሞስ ብቻ ሳይሆን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችም በእነዚህ ፓርቲዎች ፖሊሲዎች ላይ ተቃውሞዎችን ሲያሰሙ ይደመጣል።

ሆኖም በቅርቡ የተቋቋመውን የዙማን ኡምኾንቶ ዌስዝዌ (ኤምኬ) ፓርቲን ጨምሮ፣ ኤኤንሲ እና ዲሞክራቲክ አሊያንስ ፓርቲዎች እንደማያሳስቡት ነው ኮስሞስ የሚያስረዳው።

“[እነዚህ ፓርቲዎች] በስደተኞች ላይ ግልጽ የሆነ አመለካከት አላቸው። ፀረ ስደተኛ አይደሉም” ብሏል።

በአገሪቱ ውስጥ በከፋ ሁኔታ እየጨመረ ያለው የሥራ አጥነት መጠን ወደ 32.6 በመቶ አሻቅቦ ከዓለም ከፍተኛው ከሚባሉት መካከል አንዱ ሆኖ ተመዝግቧል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ለተሻለ ኑሮ ወደ አገሪቷ የሚገቡ ስደተኞች ሥራ፣ መኖሪያ ቤት እና ሌሎች ዕድሎችን ከአገሬው እየነጠቁ ነው የሚሉ ዜጎች ቁጣ በርትቶ በተደጋጋሚ ይሰማል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ በርካታ ስደተኞች ሥራ እና የተለያዩ ዕድሎችን ተሻምተውናል ከሚሉ መጤ ጠል (ዜኖፎቢክ) የአገሪቱ ዜጎች ጥቃቶች ያጋጥማቸዋል።

የአፍሪካ የፍልሰት እና ማኅበረሰብ ማዕከል ከአውሮፓውያኑ 1994 ጀምሮ በአገሪቱ መጤ ጠል የሆኑ ጥቃቶችን ተከታሏል።

እንደ ተቋሙ ከሆነ ከፍተኛ ጥቃቶች የተመዘቡት በአውሮፓውያኑ 2008 እንዲሁም 110 ጥቃቶች በተመዘገቡበት በአውሮፓውያኑ 2022 ነው።

በባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት 61 መጤ ጠል ጥቃቶች የተፈጸሙ ሲሆን፣ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውንም አስፍሯል።

በተለይም በምርጫ ቅስቀሳዎች ወቅት ዕጩዎች ስደተኞች ላይ ባነጣጠሩ ትርክቶቻቸው ምክንያት መጤ ጠልነት የሚቀጣጠልበት ሁኔታዎች ተፈጥረዋል።

የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻዎች ትኩረት

“በሚያሳዝን ሁኔታ ፀረ ስደተኛ ትርክቶችን ማምጣት ከመራጮች ድምጽ ለማግኘት አስችሏል” የሚሉት በጆሃንስበርግ ነዋሪነታቸውን ያደረጉት የፖለቲካ ተንታኝ ማሪሳ ሎሬንሶ ናቸው።

በዚህም ምክንያት በርካታ ፓርቲዎች መጤ ጠል ትርክቶችን ሲያስተጋቡ መስማት የተለመደ ሆኗል ይላሉ።

ተንታኟ እንደሚሉት የሥራ ዕድሎቻችንን የውጭ አገር ሠራተኞች እየተሻሙ ነው የሚሉ ቅሬታዎች ከዚህ ቀደም እንዲጎሉ ባይደረግም በዘንድሮው ምርጫ ግን የፖለቲካው ማዕከላዊ ጉዳይ ሆነው ታይተዋል።

የበርካታ ፓርቲዎች የዘመቻ ስትራቴጂ አካል እንደነበርም ያስረዳሉ። ትርክቶቹ በጥቁር አፍሪካውያን ላይ ያጣጠሩ ቢሆንም፣ በአገሪቷ ባሉ የደቡብ ምሥራቅ እስያ ማኅበረሰብ አባላት ላይም ጭምር ተጽዕኖ እንዳላቸው ያስረዳሉ።

በጆሃንስበርግ ለአራት ዓመታት ከኖረ በኋላ በአውሮፓውያኑ 2018 ለሥራ ወደ ክዋዙሉ ናታል ግዛት የተዛወረው ጋናዊው ኢማኑኤል ባኒ በንግድ ሥራ ይተዳደራል። ከዚህም በተጨማሪ በአከባቢው ያለውን የጋና ሠራተኞች ማኅበርን ይመራል።

በደቡብ አፍሪካ በርካታ ስደተኞች የሚያጋጥማቸው ዋነኛ ችግር ከመኖሪያ እና ከሥራ ፈቃድ ጋር የተገናኘ እንደሆነ ያስረዳል። የአገር ውስጥ ጉዳይ ቢሮ ካለው ቢሮክራሲ ጋር ተያይዞ ወረቀት ማግኘት ቀላል አይደለም ይላል።

ዋነኛው ውጥረት ግን የሚከሰተው ከአዳዲስ የሥራ ዕድሎች ጋር በተገናኘ እንደሆነም ይገልጻል።

ኢማኑኤል በአካባቢው ባለው ማኅበረሰብ ድጋፍ ተቋቁሞ የራሱን ሥራ ስለሚሠራ ምንም ችግር አላጋጠመውም። እንዲያውም በአካባቢው ከሚኖሩት የዙሉ ማኅበረሰብ አባላት “እርዳታ እንደሚያገኝ” ይናገራል።

ሆኖም ኩባንያዎች ከደቡብ አፍሪካውያን ዜጎች በበለጠ የውጭ አገር ዜጎችን በሚቀጥሩባቸው አንዳንድ አጋጣሚዎች ውጥረት እንደሚከሰት ያስረዳል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት ወደ ደቡብ አፍሪካ የመጣው ናይጄሪያዊው የዶክትሬት ተማሪ ቶማስ በአገሪቱ መጤዎች ላይ ያነጣጠረ ጥላቻ እንዳለ ግልጽ ቢሆንም ይህ ግን የሚከፋው ሰነድ በሌላቸው ስደተኞች ላይ እንደሆነ ነው ይናገራል።

ሆኖም በአገሪቱ የሰፈነው መጤ ጠል ፖለቲካዊ ሁኔታ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለትምህርት የሚመጡ ተማሪዎችን ቁጥር ቀንሷል ብሎ ያምናል።

“ለእኔ በግሌ የትኛውም አካል ሥልጣን ላይ ቢመጣም ሕጋዊ ስለሆንኩኝ የሚነካኝ ነገር አይኖርም። የሚያስፈራኝ ነገርም የለም” ብሏል።

በአሁኑ ጊዜ በኬፕታውን መምህር የሆኑት ሩዋንዳዊው የማኅበራዊ ሳይንስ ምሁር አልበርት ምፓዛያቦ ለ27 ዓመታት በኖሩባት በዚህች አገር ምርጫዎች ላይ የሚከሰቱ ነገሮችን መከታተላቸውን ያስረዳሉ።

ስደተኞችን፣ ጥገኝነት ጠያቂዎችን እና የውጭ አገር ሠራተኞችን ምንም ልዩነት ሳይኖር በአንድ ላይ ባጣመረ መልኩ ፖሊሲ አውጪዎች ማምለጫ አድርገዋቸዋል ይላሉ።

ደቡብ አፍሪካ ከድኅረ አፓርታይድ በኋላ የገጠማት ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ተግዳሮቶችን የውጭ አገር ሠራተኞች እንዳመጧቸው ትርክቶች መሰማታቸው “ኢ-ፍትሐዊ” ነው ይላሉ።

የምርጫው ውጤት ሲነገር

ባለፈው ሳምንት በተደረገው ታሪካዊ ምርጫ አብላጫ ድምጽ በፓርላማ ያጣው የደቡብ አፍሪካ ገዢ ፓርቲ የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኤኤንሲ) የጋራ ብሔራዊ መንግሥት የመመሥረት ሃሳብ አቅርቧል።

ለሁሉም ፓርቲዎች ጥሪ ማድረጉን ያስታወቀው ፓርቲው “የምርጫው ውጤቶች ደቡብ አፍሪካውያን ሁሉም ፓርቲዎች እንዲተባበሩ ይፈልጋሉ” ሲሉ የኤኤንሲ ቃለ አቀባይ ማህሌንጊ ብሄንጉ ሞትሲሪ በዚህ ሳምንት ተናግረዋል።

የቻተም ሐውስ ተንታኝ ክሪስቶፈር ቬንዶም የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ የበላይነት አብቅቶ የመድብለ ፓርቲ አገዛዝ መምጣቱ እንደ ጥሩ መሻሻል ሊታይ ይችላሉ ይላሉ።

ሆኖም የጥምረት ፖለቲካ ፓርቲዎች በደቡብ አፍሪካ ጥሩም ደካማም የሚባል ታሪክ እንዳላቸው በመጥቀስ፣ ቀጣዩ የአምስት ዓመት ወቅት “የማይጠበቁ ነገሮች የሚከሰቱበት ሊሆን ይችላል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

አርማ