ዢያዎ እና ሁለት ልጆቿ
የምስሉ መግለጫ,ዢያዎ እና ሁለት ልጆቿ

ከ 5 ሰአት በፊት

“በየዓመቱ እጄ ላይ ምንም ገንዘብ የለም። በጣም ቢጨንቀኝም ምን ማድረግ እንዳለብኝ አላውቅም” ትላለች የ36 ዓመቷ ዢያዎ ዡዎ።

ዡዎ ከሁለት ልጆቿ ጋር በደቡብ ምሥራቅ ቻይናዋ ዢያሜን ከተማ ትኖራለች።

በኮቪድ ወረርሽን ወቅት ዡዎ እና ባሏ ደሞዛቸው 50 በመቶ ተቀነሰ። ይህ ለቤተሰቡ ትልቅ ችግር ይዞ መጣ። በተለይ ደግሞ ላለፉት 5 ዓመታት በካንሰር እየተሰቃዩ ያሉትን እናቷን ለምታግዘው ዣዎ ከባድ ሆነ።

ወጣት ቻይናውያን “ዳ ዚ” የሚሉት አዲስ ዘይቤ እየተለመደ መጥቷል። ተመሳሳይ ፍላጎት ያለው አጋር ማለት ነው። ነገር ግን አንድ ላይ ተገናኝቶ ስፖርት መሥራት አሊያም መጓዝ አይደለም ዓላማቸው።

ዢያዎ ዡዎ ገንዘብ መቆጠብ የሚፈልጉ ሰዎችን ነው የምታስሰው፤ ብቻዋን አይደለችም። “ሴቪንግ ዳ ዢ” የተሰኘው ቃል መጀመሪያ የታየው ዢያሆንግሹ የተባለው የቻይናው ኢንስታግራም ላይ ነው።

በአውሮፓውያኑ ከየካቲት 2023 ጀምሮ እስካሁን 1.7 ሚሊዮን ሰዎች ተጠቅመውታል።

ዌቦ የተሰኘው የቻይናው ማኅበራዊ ሚድያ ላይ ደግሞ በተመሳሳይ ሚሊዮኖች ይህን ርዕስ ጎብኝተውታል። ትክክለኛውን ቁጥር ማግኘት ባይቻልም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የቁጠባው የማኅበራዊ ሚድያ ቡድን አባል እንደሆኑ ይገመታል።

አብዛኞቹ አባላት ዕድሜያቸው ከ20 እስከ 40 የሚሆን ሴቶች ናቸው። በቁጥር የሚልቁት ደግሞ እናቶች ናቸው። ብዙዎች እንደሚሉት ገንዘብ የሚቆጥቡት እተወደደ ለመጣው የልጆቻቸው የትምህርት ቤት ክፍያ ነው።

ሌሎች ደግሞ ገንዘብ ቆጥበው አክሲዮን በመግዛት የተሻለ ነገን አልመው ተነስተዋል። የተቀሩት ደግሞ ምጣኔ ሀብቱ እየተዳከመ በመምጣቱ ገንዘብ ቆጥበው ተዘጋጅተው መጠበቅን ይሻሉ።

ቻይናዊያን በዓለማችን ካሉ ገንዘብ ቆጣቢ ከሚባሉ ሕዝቦች ቁንጮዎቹ ናቸው። እንዲህም ሆኖ ዜጎቸ ቁጠባቸውን የበለጠ ማዳበራቸው “በምጣኔ ሀብቱ መጪ ዕጣ ፈንታ ላይ ያላቸው እምነት መላሸቁን ያሳያል” ይላል የሲንጋፖር ናሽናል ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሯ ሉ ዢ።

አንዲት ቻይናዊት ስትገበያይ

ቻይናውያን ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት 138 ትሪሊዮን ዩዋን [የቻይና ገንዘብ] ቆጥበዋል። ይህ ወደ ዶላር ሲቀየር 19.1 ትሪሊዮን ይሆናል። ይህን ገንዘብ ገቢ ያደረጉት ባንክ ነው። ቁጠባው ካለፈው ዓመት 14 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

ቻይና ኮቪድን ለመግታት ጠበቀ ያለ ፖሊሲ ካወጣች በኋላ ወደ መደበኛው ምጣኔ ሀብቷ ለመመለስ ብዙ ጥራለች። የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት በተለያዩ ችግሮች ተተብትቧል።

በቻይና ሴቶች የዕለተ ዕለት ተግባራትን የመከወን ኃላፊነት አለባቸው። በርካታ ሴቶች ቁጠባን ባህላቸው አድርገዋል ማለት ሥራ አጥነት እየተስፋፋ መጥቷል ማለት ነው ይላሉ ዶ/ር ሉ።

የሥራ አጥነት መጠኑ ባለፉት ሦስት ወራት በተከታታይ ከፍ እያለ መጥቷል ይላል የቻይና መንግሥት መረጃ።

ዜጎች ቁጠባን የበለጠ እያዳበሩ መምጣታቸውን ለቻይና መንግሥት ሌላ ማነቆ ነው። ዜጎች በጣም ቆጠቡ ማለት መንግሥት ምጣኔ ሀብቱን ማመጣጠን ይሳነዋል ማለት ነው።

ባለፉት ዓመታት የነበረው ዕድገት በመሠረተ-ልማት ግንባታ እና በዝቅተኛ ዋጋ የሚመረቱ ዕቃዎች ላይ የተመሠረተ ነበር። ነገር ግን ባለሙያዎች የቻይና ምጣኔ ሀብት እየበለጸገ ሲመጣ የአገር ውስጥ ፍጆታ መጨመር አለበት ይላሉ።

ዶ/ር ሉ እንደሚሉት ቻይና ልክ ጃፓን በ1990ዎቹ የገጠማት ዓይነት የምጣኔ ሀብት ቀውስ ሊገጥማት ይችላል። ዜጎች ገንዘብ ወጪ ማድረግ አሊያም ኢንቨስት ማድረግ ሲያቆሙ ምጣኔ ሀብቱ መንቀሳቀስ ያቆማል ማለት ነው።

ጭንቀት እና ጓደኝነት

ዢያዎ ዡዎ በንፁህ ኢነርጂ ዘርፍ ተሰማርታ በመሥራቷ ዕድለኛ ነኝ ትላለች። ይህ ዘርፍ ባለፈው ዓመት ለቻይና ኢኮኖሚ 40 በመቶውን ድርሻ አበርክቷል። ቢሆንም “ለአደጋ ጊዜ መዘጋጀት” እንዳለባት ታስባለች። ምክንያቱም ሌላው ቀርቶ ሆስፒታል እና ትምህርት ቤት የሚሠሩ ቤተሰቦቿ እና ጎደኞቿ ሥራቸውን ሲያጡ ተመልክታለች።

ባለፈው የካቲት ዡዎ የተለያዩ ቁጠባን የሚያበረታቱ ቡደኖችን ተቀላቅላለች። የማኅበሩ አባላት በጀታቸውን እና ወጪያቸውን ይለጥፋሉ። አልፎም አላስፈላጊ ወጪ እንዳያወጡ ምክር ይለግሳሉ።

አንድ የማኅበሩ አባል 5 ሺህ ዩዋን የሚያወጣ ቅንጡ ቦርሳ ለመግዛት አስባ የማኅበሩን አባላት ካማከረች በኋላ ከ1 ሺህ በታች ዋጋ ያለው ያገለገለ ቦርሳ ገዝታለች።

የቻይናው የቁጠባ መተግበሪያ
የምስሉ መግለጫ,በልብ ቅርፅ የተሠራው የቻይናው የቁጠባ መተግበሪያ

ዡዎ ከዚህ ማኅበር የተለያዩ የገንዘብ መቆጠቢያ መንገዶችን ተምራለች። ለምሳሌ አንድ የልብ ቅርፅ ያለው የገንዘብ መቆጠቢያ መተግበሪያ አውርዳለች። ይህ መተግበሪያ 365 ቀናት አንዴት ገንዘብ መቆጠብ እንደሚቻል የሚያሳይ ነው። በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 35 ሺህ ዩዋን ልትቆጥብ ትችላለች።

ሌሎች እንደሷ ያሉ ሰዎች ገንዘብ መቆጠብ እንደሚሹ ማወቋ አስገርሟታል። ከማኅበሩ አባላት ጋር ጓደኝነት መመሥረትም ችላለች።

በተለይ ደግሞ ከአንድ የዳ ዢ ማኅበር አባል ጋር ጓደኝነት መሥርታለች። ጓደኛዋ አስተማሪ ስትሆን የመጀመሪያ ልጇን ለመውለድ በመጠባበቅ ላይ ናት።

ዡዎ የወር ቁጠባዋን ባሳካች ጊዜ አበባ ገዝታ 2 ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ለምትገኘው ጓደኛዋ ልካለች።

ከዚህ ቀደም ባላስፈላጊ መልኩ ታወጣው የነበረውን ወጪም መቀነስ ችላለች። ከዚህ ቀደም ወደ ገበያ ወጥታ ያማራትን ነገር ነበር ዘንቢሏ ውስጥ የምትከተው። አሁን ግን መግዛት የምትፈልገውን ነገር መዝግባ ነው የምትወጣው። ከዚያ ውጪ ምንም ነገር አትሸምትም።

የቁጠባ ጓደኞች ካፈራች በኋላ ወርሀዊ ወጪዋን 40 በመቶ መቀነስ ችላለች። ከአንድ ዓመት በኋላ 100 ሺህ ዩዋን መቆጠብ ነው ዓላማዋ።

ዡዎ ብቻ ሳትሆን ሌሎች በርካታ ሴቶች “ዳ ዢ” ቁጠባን አስተምሮናል ይላሉ። አንድ አባል እንድምትለው አሁን ቤት ውስጥ አብስላ መብላት እና አላስፈላጊ ወጪዎችን መቀነስ ችላለች። አንዲት ሴት ደግሞ ራሷን በሥራ በመጥመድ እና ወጪ የሌላቸውን ልምዶችን በማዘውተር መቆጠቧን ትናገራለች።

ቼን፣ ባሏ እና ሁለት ልጆቿ
የምስሉ መግለጫ,ቼን፣ ባሏ እና ሁለት ልጆቿ

ገንዘብ ንጉሥ ነው

አንዳንድ ሴቶች ባህላዊ የሚባለውን የቁጠባ ዘዴ እየተገበሩ ነው – ገንዘብ በቤታቸው ማስቀመጥ። ይህ ጥሬ ገንዘብ ብዙም ጥቅም ላይ በማይውልባት ቻይና የተለመደ አይደለም። ስታቲስታ የተሰኘው መረጃ አውጭ እንደሚለው 70 በመቶ ቻይናውያን ‘ሞባይል መኒ’ እንጂ ጥሬ ገንዘብ አይጠቀሙም።

በማዕከላዊ ሄናን ግዛት ውስጥ የውበት ሳሎን ያላት የ32 ዓመቷ ቼን “የጥሬ ገንዘቡ መጠን እየጨመረ ሲሄደ ስመለከት እርካታ ይሰማኛል” ትላለች።

በየወሩ ከባንክ ገንዘቧን አውጥታ ቁልፍ ባለው ሳጥን ውስጥ ታስቀምጠዋለች። 50 ሺህ ዩዋን ሲደርስ “የማይንቀሳቀስ ሒሳብ” ውስጥ ታደርገዋለች።

ለግብይትም ቢሆን የምትጠቀመው ጥሬ ገንዘብ ነው። እርግጥ ነው በጥሬ ገንዘብ መገበያያት አይመችም። ነገር ግን ይህ ብዙ ወጪ እንዳላወጣ ያደርገኛል ትላለች።

ምጣኔ ሀብቱ እየደቀቀ ሲመጣ ቼን መቆጠብ የሚፈልጉ በርካታ ደንበኞቿን አጥታለች። ቼን እና ባሏ ለቤተሰቦቻቸው ብቸኛ ልጆች ናቸው። ይህ ማለት አራት ወላጆቻቸውን መደገፍ አለባቸው ማለት ነው።

ቼን ለሁለት ወንድ ልጆቸው በየዓመቱ አንድ ሚሊዮን ዩዋን መቆጠብ ትሻለች። ቻይና ውስጥ ወንዶች ትዳር ሲመሠርቱ ቤት ሊኖራቸው ይገባል። ቤተሰቦች ለወንድ ልጆቻቸው ቤት ሲገዙ ማየት የተለመደ ነው።