
ከ 4 ሰአት በፊት
በእስራኤል መንግሥት ውስጥ ያለውን ጥልቅ ክፍፍል በግልጽ ያሳያል በተባለ ውሳኔ የአገሪቱ የጦር ካቢኔ ሚኒስትር ቤኒ ጋንትዝ የአስቸኳይ ጊዜ መንግስቱን ለቀቁ።
የሚንስትሩ ውሳኔ ከጋዛ ጦርንት በኋላ ባለው ዕቅድ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር የተፈጠረው ልዩነት ማሳያ ተደርጓል።
ጋንትዝ እሑድ ዕለት በቴል አቪቭ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን ሲያሳውቁ ውሳኔውን “ቀልል አልነበረም” ብለዋል።
“እንደ አለመታደል ሆኖ ኔታንያሁ ወደ እውነተኛው ድል እንዳንቀርብ እየከለከለን ነው። ይህም ለቀጠለው ቀውስ ማሳያ ነው” ብለዋል።
በአንዳንዶች የእስራኤል ቀጣዩ ጠቅላይ ሚንስትር ለመሆን ዕድል እንዳላች የሚነገርላቸው ጋንትዝ፤ ኔታንያሁ የምርጫ ቀን እንዲወስኑ ጠይቀዋል።
ኔታንያሁ በኤክስ ላይ በሰጡት አስተያየት “ቤኒ አንድ የምንሆንበት አንጂ ይህ ኃላፊነት የምንሸሽበት ጊዜ አይደለም” ብለዋል።
የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ያየር ላፒድ በበኩላቸው ጋንትዝን ውሳኔ “አስፈላጊ እና ትክክለኛ” ሲሉ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ደግፈዋል።
ውሳኔውን ተከትሎ ቀኝ አክራሪው የብሔራዊ ደህንነት ሚኒስትር ኢታማር ቤን-ጊቪር በጦር ካቢኔው ውስጥ ለመካተት ጠይቀዋል።
ቤን-ጊቪር የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ያቀረቡትን የተኩስ አቁም ሃሳብ እስራኤል የምትቀበለው ከሆነ ስልጣን ለቀው መንግሥት እንደሚያፈርሱ ሲዝቱ ነበር።
- ሩሲያ ታላላቅ ሳይንቲስቶቿን እያሰረች በአገር ክህደት የምትከሰው ለምንድን ነው?ከ 5 ሰአት በፊት
- ቻይናውያን ሴቶች ማኅበራዊ ሚዲያን ገንዘብ ለመቆጠብ እየተጠቀሙበት ነውከ 5 ሰአት በፊት
- የቀደምት አፍሪካውያን ቋንቋ ነው የሚባለው እና ሊጠፋ የተቃረበው ኢትዮጵያዊው ቋንቋ – ጫቡ9 ሰኔ 2024
ጋንትዝ ባለፈው ወር በጋዛ ያለው የሐማስ አገዛዝ የሚያበቃበትን እና ሲቪል አስተዳደር መመስረትን ጨምሮ እስራኤል ልታከናውናቸው የሚገቡ ስድስት “ስትራቴጂካዊ ግቦችን” እንዴት እንደምታሳካ ፍኖተ ካርታ እንዲያዘጋጁ ለኔታንያሁ ቀነ-ገደብ አስቀምጠው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ በሰጧቸው አስተያየቶቸ ጉዳዩን “ስሜት የማይሰጥ” ከማለት ባለፈ “ለእስራኤል ሽንፈት” ነው ሲሉ አጣጥለውታል።
ኔታንያሁን በተደጋጋሚ ሲተቹ የሚደመጡት ጡረተኛው የጦር ጀነራል ጋንትዝ፤ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ከመከላከያ ሚኒስትሩ ዮአቭ ጋላንት ጋር በመሆን የእስራኤል ቁልፍ ውሳኔ ሰጪ የሆነው “የጦር ካቢኔ” አባል ነበሩ።
ጋንትዝ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ወቅት ከመንግሥት ኃላፊነት የለቀቁት በግል ብቻ ሳይሆን የሚመሩትን የብሔራዊ አንድነት ፓርቲንም ይዘው በመውጣት ጭምር መሆኑን ገልጸዋል።
ኔታንያሁ አሁንም 120 መቀመጫ ባለው ክኔሴት (የእስራኤል ፓርላማ) 64 አባላትን በመያዝ አብላጫ ድምጽ ስላላቸው የጋንትዝ እርምጃ የእስራኤልን መንግሥት አያፈርስም።

ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትሩን የበለጠ የሚያገል እና ጦርነቱን በሚመሩበት መንገድ ላይ ያለውን ጥልቅ የፖለቲካ ክፍፍል በግልጽ ያሳያል ተብሏል።
ጋንትዝ ከኃላፊነት የለቀቁት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ወደ ቀጣናው የሦስት ቀናት የሥራ ጉዞ ከማድረጋቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ነው። ብሊንከን ግብጽን፣ ዮርዳኖስን እና ኳታርን በመጎብኘትም የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ግፊት ለማድረግ አቅደዋል።
በሌላ ዜና ደግሞ የአገሪቱን ጦር የጋዛ ክፍልን የሚመሩ ከፍተኛ አዛዥ የመስከረም 26ቱን ጥቃት ለመከላከል ባለመቻላቸው ከሥራ መልቀቃቸውን የእስራኤል ጦር አስታውቋል።
ብርጋዴር ጄኔራል አቪ ሮዘንፈልድ ከጥቃቱ በኋላ ኃላፊነታቸውን የለቀቁ የመጀመሪያው የአገሪቱ ጦር አዛዥ ሆነዋል።