
ከ 15 ደቂቃዎች በፊት
ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ በማዕከላዊ ሶማሊያ ማሬሃን እና ዲር በተባሉ ጎሳዎች መካከል በተከሰተ ግጭት ቢያንስ 40 ሰዎች መገደላቸው ሲገለጽ፣ የአልሻባብ ኃይሎች ጥቃት ሰንዝረው በርካቶች መሞታቸው ተገለጸ።
ቅዳሜ ሰኔ 1/2016 ዓ.ም. በጋልሙዱግ ግዛት በጎሳ አባላቱ መካከል የተከሰተው ግጭት እንዲረግብ የፌደራል መንግሥቱ እና የግዛቲቱ አስተዳደር ጠይቀዋል።
የአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ የጋልሙዱግ ግዛት ፕሬዝዳንት አሕመድ አብዲ ካሬ በጎሳ መካከል የተፈጠረውን ግጭት በንግግር ለመፍታት የእርቅ ኮሚቴ አቋቁመዋል።
አንዳንድ የሶማሊያ መገናኛ ብዙኃን በዚህ የጎሳ ግጭት የሞቱ ሰዎች ቁጥርን 60፤ የቆሰሉትን ደግሞ 80 ያደርሱታል።
ላንደሄር እና ቃለቃሎ በተባሉ መንደሮች አካባቢ የተከሰተውን ይህንን የጎሳ ግጭት ማስቆም የተቻለው የግዛቲቱ እና የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ኃይሎች ከተሰማሩ በኋላ ነው።
በሁለቱ የጎሳ አባላት መካከል ግጭቱ የተከሰተው በግጦሽ መሬት እና በውሃ ጉድጓዶች ይገባኛል ጥያቄ ምክንያት መሆኑን ኩልሚዬ የተባለው የሬዲዮ ጣቢያ ዘግቧል።
ግጭቱ የተከሰተው የዳሮድ ንዑስ ጎሳ በሆኑት ማሬሃን እና ሱሬ በሚባሉ ጎሳዎች መካከል ነው።
በሁለቱ ጎሳዎች መካከል ግጭት ሲከሰት ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ከሁለት ወራት በፊት በተመሳሳይ ግጭት ተከስቶ የግዛቱ አስተዳዳሪዎች የሁለቱን ጎሳ አባላት ለማስታረቅ ያደረጉት ጥረት አልተሳካም።
- ሩሲያ ታላላቅ ሳይንቲስቶቿን እያሰረች በአገር ክህደት የምትከሰው ለምንድን ነው?ከ 5 ሰአት በፊት
- የአውሮፓ ፓርላማ ምርጫን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ማክሮን የፈረንሳይ ፓርላማን በተኑከ 4 ሰአት በፊት
- በእስራኤል ያለውን ክፍፍል በሚያሳይ ውሳኔ የጦር ካቢኔ ሚኒስትር ቤኒ ጋንትዝ ስልጣን ለቀቁከ 4 ሰአት በፊት
ይህ ግጭት የተከሰተው ከአል ቃኢዳ ጋር ግንኙነት ባለው እስላማዊው ቡድን አል-ሸባብ እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል የጎሳ ግጭቱ ከተከሰተበት አካባቢ በቅርብ ርቀት ላይ ከባድ የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸው ከተሰማ በኋላ ነው።
ቅዳሜ ሰኔ 1/2016 ዓ.ም. በጋልጉዱዱ ግዛት ኤል-ዴር ከተማ በሚገኝ ወታደራዊ ካምፕ ላይ አል-ሸባብ ድንገተኛ ጥቃት ፈጽሟል።
ይህን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ የሶማሊያ መንግሥት ከአጎራባች አካባቢዎች ተጨማሪ ኃይል በማሰማራት ከ47 በላይ የቡድኑ አባላትን መግደሉን እና የተሰነዘረውን ጥቃት ማክሸፉን አስታውቋል።
የሶማሊያ የማስታወቂያ፣ የባህል እና የቱሪዝም ሚኒስቴር ቅዳሜ ዕለት ባወጣው መግለጫ በአየር ኃይል የታገዘ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ በማካሄድ ኤል-ዴር ከተማ በሚገኘው የጦር ሰፈር ላይ ጥቃት የፈጸሙ 47 የቡድኑ አባላት ላይ እርምጃ ተወስዷል ብሏል።
አል-ሸባብ በበኩሉ ጥቃቱን ከፈጸመ በኋላ ባወጣው መግለጫ በመንግሥት ኃይሎች ላይ ድልን ተጎናጽፊያለሁ ብሏል።
ለአል-ሸባብ ቅርበት ያለው ሶማሊ ሚሞ የተባለው ድረ-ገጽ በጥቃቱ ሁለት አዛዦችን ጨምሮ 59 የመንግሥት ወታደሮች ተገድለዋል ብሏል።
ኤል-ዴራ በምሥራቅ አቅጣጫ ከሶማሊያ መዲና ሞቃዲሹ 287 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ስፍራ ነው።