
10 ሰኔ 2024, 16:25 EAT
ከአንድ ወር በኋላ በሚጀምረው የ2017 በጀት ዓመት መንግሥት ለመሰብሰብ ባቀደው እና በወጪው መካከል የ358.5 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ የበጀት ጉድለት መታየቱን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይህ የበጀት ጉድሉት ቢታይም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በመጪው 2017 በጀት ዓመት የ8.4 በመቶ ዕድገት ያስመዘግባል የሚል ትንበያ መኖሩን ገልጿል።
ይህ የተገለጸው የገንዘብ ሚኒስቴር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የ2017 በጀት ዓመት የበጀት መግለጫ ላይ ነው።
ቢቢሲ የተመለከተው ይህ የበጀት መግለጫ በ2017 በጀት ዓመት ጠቅላላ የፌደራል መንግሥት ገቢ 612.7 ቢሊዮን ብር ይሆናል ተብሎ እንደሚገመት ጠቅሷል። ይህ የፌደራል መንግሥት ገቢ የውጭ ዕርዳታን የሚያካታት ነው።
የ2017 በጀት ዓመት ገቢ በ2016 ዓ.ም ይሰበሰባል ተብሎ ከተገመተው ጠቅላላ ገቢ አንጻር 28.3 በመቶ ዕድገት እንዳለው መግለጫው ላይ ሰፍሯል።
ከጠቅላላ ገቢው ውስጥ 502.04 ቢሊዮን ብር የሚሆነው ገቢ ይሰበሰባል ተብሎ የተገመተው ከታክስ ገቢ ነው። ከዚህ በተጨማሪም 61.6 ቢሊዮን ብር ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች፣ 7.3 ቢሊዮን ብር ከአጋሮች የበጀት ድጋፍ እንዲሁም 41.8 ቢሊዮን ብር ደግሞ ከፕሮጀክቶች ዕርዳታ ይገኛል ተብሎ ተገምቷል።
በአንጻሩ የፌደራል መንግሥት የ2017 በጀት ዓመት ጠቅላላ ወጪ 971.2 ቢሊዮን ብር ነው። ይህ ወጪ ለ2016 ዓ.ም. ከጸደቀው ወጪ በጀት አንጻር የ21.1 በመቶ ዕድገት አለው።
ለ2017 ከተያዘው ጠቅላላ በጀት ውስጥ ለመደበኛ ወጪዎች የተመደበው 451.3 ቢሊዮን ብር ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል። ለካፒታል ወጪዎች ደግሞ የተመደበው በጀት 283.20 ቢሊዮን ብር ነው።
ለክልል መንግሥታት የበጀት ድጋፍ 222.69 ቢሊዮን ብር የተመደበ ሲሆን፣ ቀሪው 14 ቢሊዮን ብር ደግሞ ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ የተመደበ ድጋፍ ነው።
ለመደበኛ ወጪ ከተያዘው በጀት አንጻር 28.2 በመቶው ለደመወዝ፣ አበል እና ልዩ ልዩ ክፍያዎች የተመደበ ሲሆን፣ ቀሪው 71.8 በመቶ ደግሞ ለሥራ ማስኬጃ ተደግፎ የቀረበ ነው።
- የመጪው 2017 በጀት ከዘንድሮው በ169.5 ቢሊዮን ብር የበለጠ ሆኖ ተዘጋጀ7 ሰኔ 2024
- የፌደራል መንግሥት በኤሌክትሪክ እና በውሃ አገልግሎት ላይ ቫት የሚጥል ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ አቀረበ15 ግንቦት 2024
- የውጭ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ከወጪ እስከ ችርቻሮ ንግድ ዘርፍ መግባታቸው በረከት ወይስ ስጋት?20 ሚያዚያ 2024

በሌላ በኩል ለካፒታል ወጪዎች ከተያዘው በጀት ውስጥ 66.1 በመቶው የተመደበው “ቅድሚያ ትኩረት ለተሰጣቸው” ለመንገድ፣ ለትምህርት፣ ለግብርና እና መስኖ፣ ለመጠጥ ውሃ እና ሳኒቴሽን፣ ለጤና፣ ለገጠር እና ለከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ማስፈጸሚያ የተመደበ በጀት ነው።
ከዚህ በተጨማሪም በጦርነቱ ምክንያት የወደሙ ንብረቶች እና አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ወደ ነበሩበት ለመመለስ እና ለማቋቋም ለተጀመረው ፕሮጀክት ከመንግሥት ግምጃ ቤት 20 ቢሊዮን ብር ቀርቧል።
በዚህ የፌደራል መንግሥት የገቢ እና ወጪ በጀት መካከል የ358.5 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ የበጀት ጉድለት ታይቷል።
የበጀት መግለጫው “ይህን የበጀት ጉድለት ከአገር ውስጥ እና ከውጭ አገር በሚወሰድ ብድር ለመሸፈን ታቅዷል” ሲል ያትታል።
ከፍተኛውን የመንግሥት የበጀት ጉድለት ይሸፍናል ተብሎ የሚጠበቀው ከአገር ውስጥ የሚገኘው 325.58 ቢሊዮን ብር ብድር ነው። መንግሥት ቀሪውን የ32.92 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉደለት ሊሸፍን ያቀደው ደግሞ ከውጭ አገር ብድር ነው።
የበጀት መግለጫው “የአገር ውስጥ ብድር አወሳሰዱም የዋጋ ንረትን በማያስከትሉ የብድር መሳሪያዎች ማለትም የመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነዶችን እና የመካከለኛ ዘመን ቦንዶችን በመሸጥ ለመሸፈን የታቀደ ነው” ይላል።
ይህ የበጀት ጉድለት “መንግሥት የተረጋጋ ኢኮኖሚ ለማስፈን ካስቀመጠው ግብ ጋር የተጣጣመ” እንደሆነ የሚያስረዳው መግለጫው፤ በቀጣዩ በጀት ዓመት ይታያል ተብሎ የሚገመተውን የዕድገት ትንበያም አስቀምጧል።
የበጀት መግለጫው ከ2012 እስከ 2015 ባሉት አራት ዓመታት የ6.5 በመቶ አማካይ የዕድገት ምጣኔ መመዝገቡን አስታውሶ ይኼው ዕድገት በተያዘው እና በመጪው ዓመትም እንደሚቀጥል ተንብይዋል።
“ኢኮኖሚው ባለፉት ዓመታት ካጋጠሙት ጫናዎች በማገገም በያዝነው በጀት ዓመት የ7.9 በመቶ ዕድገት እንደሚያስመዘግብ” መግለጫው ትንበያ አስቀምጧል። በመጪው የ2017 በጀት ዓመት ደግሞ የአገሪቱ ኢኮኖሚ የ8.4 በመቶ ዕድገት እንደሚያስመዘግብ ተንብይዋል።
መንግሥት ከዚህ ትንበያ ላይ የደረሰው “የመስኖ ልማትን ለማስፋፋት” ያከናወናቸውን ተግባራት እና የመጪው ዓመትን የዝናብ ሽፋን መሠረት በማደረግ ነው።
የበጀት መግለጫው “ለግብርና ተግባር አመቺ የሆነ የዝናብ ሽፋን በአብዘኛው የአገሪቱ ክፍሎች መኖሩ ዘርፉ ለኢኮኖሚ ዕድገት ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው ይጠበቃል” ሲል ያትታል።