
ከ 7 ሰአት በፊት
የማላዊውን ምክትል ፕሬዝዳንት ሳውለስ ቺሊማን እና ሌሎች ዘጠኝ ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ አውሮፕላን መሰወሩን የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የማላዊ መከላከያ ኃይል ንብረት የሆነው አውሮፕላን ከዋና ከተማዋ ሊሎንዌ ዛሬ ሰኞ ጠዋት ከተነሳ በኋላ “ከራዳር ዕይታ ውጪ” በመሆን መሰወሩን ጽህፈት ቤቱ ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክቷል።
የአገሪቱ የአቪዬሽን ባለሥልጣናት ከአውሮፕላኑ ጋር ግንኙነት ለማድረግ ሳይችሉ መቅረታቸውን ተከትሎ የማላዊው ፕሬዝዳንት የፍለጋ እና ነፍስ የማዳን ተልዕኮ እንዲካሄድ አዘዋል።
አውሮፕላኑ ከዋና ከተማዋ ከተነሳ በኋላ ረፋድ ከአራት ሰዓት በኋላ በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ውስጥ ከሚገኘው ምዙዙ ኢንተርናሽናል አየር ማረፊያ ይደርሳል ተብሎ ሲጠበቅ ነበር።
ከምክትል ፕሬዝዳንቱ በተጨማሪ በአውሮፕላኑ ውስጥ በርካታ የፓርቲያቸው ባለሥልጣናት ነበሩ።
- ሩሲያ ታላላቅ ሳይንቲስቶቿን እያሰረች በአገር ክህደት የምትከሰው ለምንድን ነው?10 ሰኔ 2024
- ኢራን ፕሬዝዳንቷን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯን ያጣችበት የሄሊኮፕተር አደጋ21 ግንቦት 2024
- የኢራኑ ፕሬዝዳንት ስለሞቱበት የሄሊኮፕተር አደጋ እስካሁን የምናውቀው20 ግንቦት 2024
ምክትል ፕሬዝዳንቱን የያዘው አውሮፕላን መጥፋት በአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት አዛዥ ከተነገራቸው በኋላ የማላዊው ፕሬዝዳንት ላዛረስ ቻክዌራ ወደ በውጭ ሊያደርጉት የነበረውን ጉዟቸውን ሰርዘዋል።
የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ “የተረጋገጡ መረጃዎች በተገኙ ጊዜ ለሕዝቡ ይፋ ይደረጋል” ብሏል።
የአገሪቱ ጦር አዛዥ ጄኔራል ቫለንቲኖ ፊሪ ለፕሬዝዳንቱ ክስተቱን ባሳወቁበት ጊዜ ለአውሮፕላኑ መሰወር ምክንያቱ ምን እንደሆነ እንዳልታወቀ ተናግረዋል።
የማላዊ ማስታወቂያ ሚኒስትር ሞሰስ ኩንኩዩ ለቢቢሲ አውሮፕላኑን ለማግኘት የሚደረገው ፍለጋ “ተጠናክሯል” ብለዋል።
የተጓዙበት አውሮፕላን የደረሰበት ያልታወቀው ምክትል ፕሬዝዳንቱ መንግሥትን ወክለው በአንድ የቀድሞ የምክር ቤት አባል የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት በመጓዝ ላይ ነበሩ።
ምክትል ፕሬዝዳንቱ ወደ ፖለቲካው ዓለም ከመግባታቸው በፊት ዩኒሊቨር እና ኮካኮላን በመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ውስጥ በከፍተኛ የመሪነት ቦታ ላይ ሠርተዋል።
ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት የሆኑት የ51 ዓመቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ቺሊማ ደቡባዊ አፍሪካዊቷ አገር ማላዊ ምክትል ፕሬዝዳንት በመሆን ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ እያገለገሉ ነው።