ዜና የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 129.7 ሚሊዮን መድረሱን ተመድ አስታወቀ

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: June 9, 2024

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 129.7 ሚሊዮን ደርሷል አለ፡፡

ኢትዮጵያ የሚገኘው የተመድ የሥነ ሕዝብ ፈንድ ድርጅት እ.ኤ.አ. የ2024 የኢትዮጵያን የሥነ ሕዝብ ሪፖርት የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የተመድና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በተገኙበት ይፋ አድርጓል፡፡ በሪፖርቱ እንደተመላከተው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቋጥር ዘንድሮ 129.7 ሚሊዮን መድረሱንና ቁጥሩም በ28 ዓመት ውስጥ ራሱን እጥፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

ከአጠቃላይ ሕዝቡ ከ0 እስከ 14 ዕድሜ 39 በመቶ፣ ከ10 እስከ 19 ዕድሜ 23 በመቶ፣ ከ10 እስከ 24 ዕድሜ 32 በመቶ፣ እንዲሁም ከ15 እስከ 64 ዕድሜ ክልል 55 በመቶ ውስጥ የሚገኝ መሆኑ ዓመታዊ ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

ከአገሪቱ ሕዝብ ሦስት በመቶው 65 እና ከዚያ በላይ ዕድሜ ያላቸው ዜጎች ሲሆኑ፣ የአገሪቱ የውልደት መጠን 3.9 በመቶ እና የመኖሪያ ዕድሜ ጣሪያ ወንዶች 64 እንዲሁም ሴቶች 70 መሆኑ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ውስን ሀብት የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን እንደገደበው ያመለከተው ሪፖርቱ፣ ተንቀሳቃሽ የጤና ባለሙያዎች 36 በመቶ የሚሆኑትን ዜጎች ብቻ እንደሚደርሱ ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡ በተጨማሪም ከከተሞች የራቁ አካባቢዎች የጤና አገልግሎት እንደማያገኙ ተገልጿል፡፡

 ሪፖርቱ ይፋ በተደረገበት ወቅት ንግግር ያደረጉት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ ወ/ሮ ሙና አህመድ፣ እ.ኤ.አ. የ2024 የሥነ ሕዝብ ሪፖርት በቀጣይ ለሚከናወኑ ስትራቴጂካዊ ዕቅዶች መነሻ እንደሚሆንና ሴቶችና ሕፃናት ካለባቸው ማኅበራዊ ችግር እንዲወጡ እንደ መሣሪያ ያገለግላል ብለዋል፡፡

ሪፖርቱ አገራዊ ሁኔታውን አመላካች ከመሆኑ ባለፈ የማኅበራዊ ፍትሕና የሰብዓዊ መብቶች መርሆች እንዲጠበቁ መሠረት የሚጣልበት፣ መርሆዎቹም ችግሮችን ለመፍታት ቁርጠኝነት የሚፈልጉ ማሳያዎች ናቸው ብለዋል፡፡ የሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር አብረው የሚመጡና ምላሽ የሚፈልጉ የትምህርት፣ የጤና፣ እንዲሁም የማኅበራዊ አገልግሎት ተደራሽነት ተመጣጣኝ ምላሽ እንዲኖር የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ትልቅ ሚና ሊጫወቱ ይገባል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣው የሕዝብ ቁጥር ከአጠቃላይ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር እንዴት ይታያል ተብሎ ሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የስታስቲክስ ባለሙያው እሸቱ ጉሩሙ (ፕሮፌሰር)፣ የሕዝብ ብዛት በራሱ ሀብት ነው ተብሎ መውሰድ እንደማይቻል፣ ይልቁንም አንድ ሕዝብ ለአንድ አገር ኢኮኖሚ እንደ ሀብት ነው ሊባል የሚቻለው አምራችና ሸማች ከሆነ ነው ይላሉ፡፡ ይህ ማለትም ጉልበቱንና ገንዘቡን ሥራ ላይ የሚያውልና በገንዘቡ ምርትና አገልግሎትን የሚገዛ ከሆነ፣ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ነገር ግን የማምረትም የመሸመት አቅም ከሌለው፣ ጥገኛና ተቀምጦ ምፅዋት ጠባቂ ከሆነ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የለውም ብለዋል፡፡ ስለዚህ አንድ ሕዝብ ራሱን የማይችልና በልቶ የማያድር ከሆነ ሀብት ነው ብሎ ለመውሰድ እንደሚቸግር ገልጸው፣ ቁጥሩ ብቻውን ኢኮኖሚውን ሊደግፍ አይችልም ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ዓመታዊ የውልደት ዕድገት 2.3 በመቶ መድረሱን የሚናገሩት  እሸቱ (ፕሮፌሰር)፣ በየዓመቱ በዚህን ያህል መጠን ለሚያድግ ሕዝብ የሚቀርበው ማኅበራዊ አገልግሎት ግን ተመጣጣኝ አለመሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ለአብነት እንኳ በየከተሞች ያለው የትራንስፖርት ችግር፣ በጤና ተቋማት የሚታየው የታካሚዎች ቁጥር መብዛት፣ የተረጂዎች ቁጥር መጨመር፣ የመኖሪያ ቤት ግንባታ እያደገ በዚያው ልክ የቤት ፈላጊው መብዛት፣ የቤት ኪራይና ሽያጭ መወደድ የሕዝቡን ዕድገት በሚመጥን ደረጃ አቅርቦቱ እየጨመረ አለመሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የቤት ግንባታ፣ የሥራ ዕድል መፈጠር፣ የኤሌክትሪክና የውኃ አቅርቦት ከሕዝቡ ፍላጎት ጋር ሊመጣጠን አለመቻሉን ጠቅሰው ይህም  በአገሪቱ እየጨመረ ያለው የሕዝብ ቁጥር ከአገራዊ ጠቅላላ ምርት ጋር ተመጣጣኝ አለመሆኑን ማሳያ ነው ይላሉ፡፡ ሁለቱ ተመጣጥነው መሄድ ካልቻሉ የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ሀብት መሆኑ ቀርቶ ዕዳ ይሆናል ሲሉ አክለዋል፡፡