
ከ 8 ሰአት በፊት
በቆጵሮስ ዝነኛ የሆነው ዩቲዩበር በግሉ ተወዳድሮ የአውሮፓ ኅብረት የፓርላማ አባል ሆኖ ተመረጠ።
ፊዲያስ ፓናዮቶት የተባለው ዩቲዩበር ቀደም ሲል ራሱን “ስህተት የመሥራት ባለሙያ” ሲል በሹፈት ይገልጽ ነበር።
ወጣቱ ለየት ያሉ የዩቲብ ይዘቶችን በማቅረብ የሚታወቅ ሲሆን፣ ኤላን መስክን ጨምሮ 100 ዝነኛ ሰዎችን አቅፎ ሰላም ለማለት በመሞከር እና በአስክሬን ሳጥን ውስጥ ሳምንታትን ማሳለፍ ከሚጠቀሱለት ሥራዎቹ ናቸው።
የ24 ዓመቱ ዩቲዩበር ከ2.6 ሚሊዮን በላይ ተካታዮች (ሰብስክራይበር) ያሉት ሲሆን፣ ምንም አይነት የፖለቲካ ልምድ ሳይኖረው የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ አባል መሆኑን አረጋጧል።
ፊዲያስ ፓናዮቶት በምርጫው ፉክክር 19. 4 በመቶ ድምጽ በማግኘት ሦስተኛው ከፍተኛ ደምጽ ያገኘ ተመራጭ ሆኗል።
“በጣም የሚገርም ነው። የሆነው ተአምር ነው” ሲል ለመገናኛ ብዙኃን የተናገረው ዩቲዩበሩ “ፓርቲዎች ይህንን እንደማስጠንቀቂያ ሊወስዱት ይገባል። ከዘመኑ ጋር ሊሄዱ እና ሕዝባቸውን ሊስሙ ይገባል” ሲልም አክሏል።
ይህ ዩቲዩበር ባለፈው ዓመት ጃፓን ውስጥ የሠራውን ቪዲዮ ተከትሎ በተፈጠረው ቅሬታ ይቅርታ ለመጠየቅ ተገዶ ነበር።
በዚህ ቪዲዮ ወጣቱ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ገብቶ ከተመገበ እና በባቡር ከተሳፈረ በኋላ ሂሳብ ሳይከፍል ይታያል።
ይህ በሚሊኖች የሚቆጠር ዕይታን ባስገኘው እና በጃፓን ባደረገው ጉዞ ላይ የሠራው ቪዲዮ የባበሩር ጣቢያ መጸዳጃ ቤት ውስጥ ለመደበቅ እና የታመመ ሰው መስሎ ሂሳብ ከመክፈል ለመሸሽ ሲሞክር ታይቷል።
ዩቲዩበሩ ከትላንት በስትያ የአውሮፓ ኅብረት ተመራጭ አባል መሆኑን ሲያረጋግጥ በደሴቲቷ አገር ዋና ከተማ ኒኮስያ አደባባይ ተገኝቶ ንግግር አደርጓል።
“በቆጵሮስ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ታሪክ እየጻፍን ነው” ሲል ተደምጧል።
ፓናዮቶት ለዚህ ምርጫ ተወዳዳሪ እንደሆነ ይፋ የተደረገው ባለፈው ጥር ወር ነበር።
ወጣቱ በአንድ መገናኛ ብዙኃን ላይ ቀርቦ ድምጽ ሰጥቶ እንደማያውቅ፣ ስለፖለቲካ እና የአውሮፓ ኅብረት ያለው ዕወቀት ዝቅ ያለ እንደሆነ አልሸሸገም ነበር። ሆኖም ከዚህ በኋላ ለፖለቲካ ባይተዋር እንደማልሆን ቃል እገባለሁ ብሏል።
ዩቲዩበሩ ባለፈው ሚያዝያ ወር የዕጩነት ምዝገባውን ሲያከናውን “ግቤ መመረጥ አይደለም ይልቅስ ወጣቶችን በፖለቲካ እንዲሳተፉ ማነቃቃት ነው” ብሎ ነበር።
በሜዲትራኒያን ባሕር ዙሪያ የምትገኘው ደሴቷ አገር ቆጵሮስ 900 ሺህ ሕዝብ የሚኖርባት ሲሆን፣ ለዚህ ምርጫ 683 ሺህ ሰዎች ተመዝግበው ነበር።
በአውሮፓውያኑ 2019 በቆጵሮስ በተደረገው ምርጫ ድምጽ ለመስጠት የወጡት ዜጎች ቁጥር ከአሁኑ ጋር ሲነጻጸር ዝቅ ያለው። ተንታኞች የዘንድሮ መራጮች ከፍ ባለቁጥር ለመውጣታቸው የዩቲዩበሩ ድርሻ ከፍ ያለ እንደሆነ ይገልጻሉ።
የ24 ዓመቱ ተመራጭ ካሸነፈበት ጠቅላላ ድምጽ 40 በመቶ የሚሆነውን ያገኘው ከ18 እስከ 24 የዕድሜ ክልል ውስጥ ካሉ ወጣቶች ሲሆን፣ 28 በመቶ ሚሆነውን ድምጽ ደግሞ የሰጡት ከ25 እስከ 34 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው።
በዚህ ምርጫ ስድስት ሰዎች ቆጵሮስን ወክለው ወደ አውሮፓ ፓርላማ ያቀናሉ።
በአገሪቱ ዝነኛ የሆኑት ወግ አጥባቂው ፓርቲ 25 በመቶ ሲያኙ ለምርጫ ካቀረባቸው ሁለት ተወዳዳሪዎች አንዱ በቂ ደምጽ ያጣበት የኮሚኒስት ፓርቲ 22 በመቶ ድምጽ አግኝቷል። ሦስተኛውን ከፍተኛ ድምጽ ያገኘው ደግሞ በግሉ የተወዳደረው ዩቲዩበር ነው።