
ከ 8 ሰአት በፊት
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አሜሪካ ያቀረበችውን የእስራኤል እና የጋዛ የተኩስ አቁም ዕቅድ በመደገፍ ድምጽ ሰጠ።
በቀረበው ሃሳብ መሠረት “ሙሉ እና ሁሉን አቀፍ የተኩስ አቁም ስምምነት” እንዲደረስ፣ በሐማስ የተያዙ ታጋቾች እንዲለቀቁ፣ የሞቱ እስረኞች አስከሬን እንዲመለስ እና የፍልስጤም እስረኞች እንዲፈቱ የሚያደርግ የተለያዩ ሁኔታዎችን አስቀምጧል።
ከ15ቱ የፀጥታው ምክር ቤት አባላት 14ቱ አሜሪካ ያቀረበችውን የውሳኔ ሃሳብ ደግፈዋል። ሩሲያ በድምፀ ተአቅቦ አልፋዋለች።
የውሳኔ ሃሳቡ እስራኤል የተኩስ አቁም ሃሳቡን እንደተቀበለች እና ሐማስም እንዲስማማበት አሳስቧል።
በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ይፋ የተደረገውን እና ሦስት ክፍሎች ያሉትን የተኩስ አቁም ዕቅድ ከፀጥታው ምክር ቤት በተጨማሪ የቡድን 7 አባል አገራት እና ሌሎችም መንግሥታት ድጋፋቸውን ችረውታል።
ድጋፉ ግጭቱን ለማስቆም ለዕቅዱ አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጡ በሁለቱም ወገኖች ላይ ጫና ሊያሳድር ይችላል ተብሏል።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን ጨምሮ የሌሎች አገራት መሪዎችን በማነጋገር ለሰላም ስምምነቱ ድጋፍ እንዲሰጡ ለማድረግ ከሞከሩ በኋላ የመጣ ድጋፍ ነው።
የመንግሥታቱ ድርጅት ድምጽ ከመስጠቱ ከጥቂት ሰዓታት በፊት ብሊንከን ለቀጣናው መሪዎች ያስተላለፉት መልዕክት “የተኩስ አቁም ከፈለጋችሁ ሐማስ ሃሳቡን እንዲቀበል ጫና አድርጉበት” ሲል ተናግረዋል።
ሐማስ ቀደም ሲል ዕቅዱን እንደሚደግፍ ገልጾ የነበረ ሲሆን፣ ሰኞ ዕለት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔን “እንደሚቀበለው” የሚገልጽ መግለጫ አውጥቷል።
- አብዛኞቹ ኢትዮጵያውን ስደተኞችን የያዘች ጀልባ ተገልብጣ ቢያንስ 38 ሞቱከ 2 ሰአት በፊት
- የትግራይ ከተሞች ነዋሪዎችን በፍርሃት እያራደ ያለው የእገታ እና የዘረፋ መበራከት11 ሰኔ 2024
- የሟቹ የአይኤስ መሪ የአቡ በከር አል ባግዳዲ ሚስት ይፋ ያደረገቻቸው ያልተሰሙ ታሪኮች11 ሰኔ 2024
ሐማስ ዕቅዱ ወደ ቋሚ የተኩስ አቁም እንደሚሸጋገር እና እስራኤላውያን ከጋዛ ሰርጥ ሙሉ ለሙሉ ለመውጣት የሚያስችል ዋስትና ሊጠይቅ ይችላልተብሏል።
የአሜሪካ እና የእስራኤል ባለሥልጣናት እንዳሉት ከሆነ በዶሃ ያለው የሐማስ የፖለቲካ አመራር ለሃሳቡ መደበኛ የሆነ ምላሽ አልሰጠም።
በዕቅዱ መሠረት በግጭቱ ውስጥ ክፉኛ የወደመው ጋዛ ግዙፍ የመልሶ ግንባታ ዕቅድ ተይዞለታል።
የመጀመሪያው ምዕራፍ የታጋቾች እና የእስረኞች መለዋወጥ እንዲሁም የአጭር ጊዜ የተኩስ አቁምን ይመለከታል።
በዩናይትድ ስቴትስ የቀረበው ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ እንደሚያመለክተው በሁለተኛው ምዕራፍ የእስራኤል ጦር ከጋዛ ሙሉ በሙሉ መውጣትን እና “የጦርነት ዘላቂ ማቆም” ያካትታል።
ሦስተኛው ምዕራፍ የሚያተኩረው በረጅም ጊዜ ለጋዛ ለበርካታ ዓመታት በሚደረግ የመልሶ ግንባታ ዕቅድ ላይ ያተኩራል።
የሰኞው የተባበሩት መንግሥታት ውሳኔ የተሰጠው ፕሬዝዳንት ባይደን እስራኤላውያን በዕቅዱ መስማማታቸውን ከገለፁ ከ10 ቀናት በኋላ ነው። ኔታንያሁ ግን የአሜሪካንን ሃሳብ እስካሁን አላጸደቁትም።
ባይደን የሰላም ሃሳቡን የእስራኤል አድርገው ቢያቀርቡትም የእስራኤል ጥምር መንግሥት ዕቅዱ በፍላጎት ማጣት እየተመለከተው ነው። ስምምነቱ ከተደረሰ ጥምር መንግሥቱ እንደሚያበቃለት በመግለጽ አንዳንድ የቀኝ አክራሪ ሚኒስትሮች በይፋ ተቃውሞ አሰምተዋል።
እሑድ ዕለት የቀድሞ የጦር ጄኔራል ቤኒ ጋንትዝ ከአገሪቱ የጦር ካቢኔ አባልነት መልቀቃቸው ያለውን የውጥረት ስሜት አባብሶታል።
የፕሬዝዳንት ባይደን በኤክስ ገጻቸው ላይ “ሐማስ የተኩስ አቁም እፈልጋለሁ ብሏል። ይህ ስምምነት ፍላጎታቸውን ስለመጠበቃቸው የሚገልጽ ዕድል ነው” ብለዋል።
በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ “ዛሬ ለሠላም ድምጽ ሰጥተናል” ብለዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደር ባርባራ ዉድዋርድ ደግሞ በጋዛ ያለውን ሁኔታ “አሰቃቂ” ሲሉ ገልጸው “ስቃዩ በጣም ለረጅም ጊዜ ቀጥሏል” ብለዋል።
“ሁሉም ወገኖች ይህንን ዕድል ተጠቅመው ለእስራኤልም ሆነ ለፍልስጤም ሕዝቦች ደኅንነት እና መረጋጋት ወደሚያመጣ ዘላቂ ሠላም እንዲሸጋገሩ እንጠይቃለን” ብለዋል።