
11 ሰኔ 2024, 07:08 EAT
ኡም ሁዳይፋ የአቡ በከር አል-ባግዳዲ የመጀመሪያ ሚስት ነበረች። ኢስላሚክ ስቴት [አይኤስ] በሶሪያ እና በኢራቅ ሰፊ ግዛቶችን በሚቆጣጠርበት ወቅት ባሏ የቡድኑ የበላይ ነበር።
ኡም ሁዳይፋ ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ምርመራ እየተደረገባት በአሁኑ ጊዜ በኢራቅ እስር ቤት ውስጥ ትገኛለች።
ይህቺ የቀድሞ የአይኤስ መሪ ሚስት ባልተለመደ መልኩ ከእስር ቤት ሆና ስለቀደመ ሕይወቷ ቃለ መጠይቅ ሰጥታለች።
እአአ በ2014 ኡም ሁዳይፋ ከባለቤቷ ጋር በሶሪያ የአይኤስ ጠንካራ ምሽግ በሆነችው ራቃ ውስጥ ትኖር ነበር።
በጥብቅ የሚፈለግ የጽንፈኛው ጂሃዲስት ቡድን መሪ እንደመሆኑ አቡ በከር አል ባግዳዲ ብዙውን ጊዜውን ቤት አይቀመጥም ነበር።
በአንድ አጋጣሚም ሁለቱን ወጣት ልጆቹን ለመውሰድ ወደ ቤቱ ጠባቂ ይልካል። “ዋና ለመማር እንደሚሄዱ ነገረኝ” ትላለች ኡም ሁዳይፋ።
ኡም ሁዳይፋ ባለቤቷ ቤት በማይኖርበት ጊዜ ከፍታ በድብቅ የምትመለከተው ቴሌቪዥን እንደነበር ትናገራለች።
ባሏ ግን ቴሌቪዥኑ እንደማይሠራ ነው የሚያውቀው።
ከዓለም ተቆራርጣ ነበር። ከ2007 (እአአ) ጀምሮ ቴሌቪዥን እንድትመለከት ወይም እንደ ሞባይል ያሉ ቴክኖሎጂዎችን እንድትጠቀም እንደማይፈቅድላት ተናግራለች።
ጠባቂው ልጆቹን ከወሰደ ከጥቂት ቀናት በኋላ ቴሌቪዥኑን ከፈተችው። ያልጠበቀችው ነበር የገጠማት። ባሏ በሰሜናዊ ኢራቅ በምትገኘው ሞሱል ከተማ በሚገኘው የአል-ኑሪ ታላቁ መስጂድ ንግግር እያደረገ ነበር።
ለመጀመሪያ ጊዜም የእስላማዊው ቡድን መሪ ሆኖ በይፋ ራሱን የገለጸበት ጊዜ ነበር። ይህንን ያደረገው ተዋጊዎቹ አካባቢውን ከተቆጣጠሩ ከሳምንታት በኋላ ነው።

አል-ባግዳዲ ከዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአደባባይ ታየ። ጺሙ ረዝሟል፣ ጥቁር ልብስ ለብሷል።
ሙስሊሞች አብረውት እንዲቆሙ የጠየቀበት መልዕክትም በመላው ዓለም ታየ።
ልጆቻቸው በኤፍራጥስ ወንዝ ዋና ከመለማመድ ይልቅ ከአባታቸው ጋር ሞሱል መታየታቸው ኡም ሁዳይፋን አስደንግጧታል።
በኢራቅ ዋና ከተማ ባግዳድ ከሚገኘው የተጨናነቀ እስር ቤት ሆና ነው ሁዳይፋ ይህንን ትዝታዋን የምትናገረው።
የኢራቅ ባለሥልጣናት በአይኤስ ውስጥ ያላትን ሚና እና የቡድኑን ወንጀሎች ለመመርመር በሚል ነው ያሰሯት።
የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚዎች እና በወሲብ ንግድ የተሰማሩትን ጨምሮ በተለያዩ ወንጀሎች የተከሰሱ እስረኞች ወዲያ ወዲህ ይላሉ። ምግብ ቋጥረው ወዳጆቻቸውን ለመጠየቅ የሚመጡ ሰዎች ሲጨመርበት አካባቢው በጩኸት ይሞላል።
በቤተ መጸሐፍቱ ውስጥ ጸጥ ያለ ቦታ በመገኘቱ ነው ለሁለት ሰዓታት ያህል የዘለቀ ቃለ መጠይቅ የተደረገላት።
በቆይታዋም ከባለቤቷ ለማምለጥ እንደሞከረች እና በማንኛውም የአይኤስ አረመኔያዊ ድርጊት ውስጥ እንዳልተሳተፈች ብቻ ሳይሆን፣ በዚህ ምክንያት መበደሏን ደጋግማ ገልጻለች።
ይህ ግን በአይኤስ አባላት ታፍነው የተደፈሩት የያዚዲ ማኅበረሰብ አባላት ለፍርድ ቤት ከሰጡት ቃል ጋር በእጅጉ ይቃረናል። በተጠለፉ ልጃገረዶች እና ሴቶች የወሲብ ባርነት ውስጥ እንዲገቡ ተባብራለች ሲሉ ሁዳይፋን ይከሷታል።
በቃለ መጠይቁ ወቅት ለአንድ ጊዜ እንኳን ጭንቅላቷን ካጎነበሰችበት ቀና አድርጋ አላወራችም። ከግንባሯ እስከ አፍንጫው ካለው ሰውነቷ ውጭ ከላይ እስከ ታች ጥቁር ለብሳለች።
ኡም ሁዳይፋ እአአ በ1976 ወግ አጥባቂ ከሚባል የኢራቅ ቤተሰብ ነው የተወለደችው። በ1999 ደግሞ ኢብራሒም አዋድ አል-ባድሪን አገባች። ይህ ግለሰብ በኋላ ላይ አቡ ባካር አል-ባግዳዲ በሚል ስሙ ታዋቂ ሆነ።

- የአይ ኤስ መሪ አቡ ባካር አል ባግዳዲ ማነው?28 ጥቅምት 2019
- የአይኤሱ መሪ አቡ ባክር አልባግዳዲ እንዴት ተገደለ?29 ጥቅምት 2019
- አይኤስ አል ባግዳዲን የሚተካውን አዲስ መሪ ይፋ አደረገ1 ህዳር 2019
ከባግዳድ ዩኒቨርሲቲ ሸሪዓ ወይም የእስልምና ሕግን ተማረ። በወቅቱ “ሃይማኖተኛ ቢሆንም አክራሪ አልነበረም… ወግ አጥባቂ ቢሆንም፣ ለነገሮች ክፍት ነበር” ትላለች።
እአአ በ2004 አሜሪካ መራሹ ጦር ኢራቅን ከወረረ ከአንድ ዓመት በኋላ የአሜሪካ ወታደሮች አል-ባግዳዲን አስረው ካምፕ ቡካ ውስጥ ለአንድ ዓመት ያህል አቆዩት። አብረውት የታሰሩትም የአይኤስ እና የሌሎች ጂሃዲስት ቡድኖች መሪ ለመሆን በቁ።
ከእስር ከተፈታ በኋላ ባሉት ዓመታት “ተናዳጅ እና በቁጣ የተሞላ ሆነ” በማለት መለወጡን ትናገራለች።
አል-ባግዳዲን የሚያውቁት ግን በቡካ ከመታሰሩ በፊትም ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ነበረው ይላሉ። እሷ ግን ይህ ለውጥ የመጣው ከዚያ በኋላ መሆኑን በመግለጽ ጽንፈኛ እየሆነ መምጣቱን ትናገራለች።
“በሥነ ልቦናዊ ችግሮች ይሰቃይ ጀመር” የምትለው ሚስቱ፣ ምክንያቱን ስትጠየቅም “‘ለማይገባችሁ’ ነገር ስለተጋለጠ” ትላለች።
ምንም እንኳን እሱ በግልጽ ባይናገርም “በታሰረበት ወቅት ወሲባዊ ስቃይ ይደርስበት ነበር” ብላ ታምናለች።
በተመሳሳይ ዓመት አቡጋሬይብ ከሚባል ሌላ በአሜሪካ ሥር ከሚተዳደር የኢራቅ እስር ቤት የወጡ ፎቶግራፎች እስረኞች ወሲባዊ ድርጊቶችን እንዲከውኑ እና አዋራጅ ነገሮችን እንዲያደርጉ መገደዳቸውን ያሳያሉ።
ይህንን ውንጀላ በተመለከተ ለአሜሪካ መከላከያ መሥሪያ ቤት ፔንታገን ቢቢሲ ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ አላገኘም።

ሁዳይፋ ከቆይታ በኋላ ባለቤቷ የአሸባሪ ቡድን አባል ስለመሆኑ መጠራጠር እንደጀመረች ትናገራለች። “ወደ ቤት ሲመለስ፣ ሻወር ሲወስድ ወይም ሲተኛ ልብሱን እፈትሽ ነበር። ቁስል ወይም ጉዳቶች ካሉት ብዬ ሰውነቱን እመለከት ነበር…ግራ ተጋባሁ” ትላለች።
ነገር ግን ምንም ፍንጭ አላገኘችም።
“አንድ ጊዜ ‘ተሳስታችኋል’ አልኩት . . . በንዴት ጦፈ” ትላለች።
ብዙ ጊዜ ቤት እንዴት እንደሚቀያይሩ፣ የውሸት ማንነት እንደነበራቸው እና ባሏ ሁለተኛ ሚስት እንዳገባ ትገልጻለች።
ኡም ሁዳይፋ በወቅቱ ፍቺ እንደጠየቀችም ተናግራለች። እሱ ደግሞ እንደ ቅድመ ሁኔታ ልጆቿን አሳልፋ እንድትሰጠው በመጠየቁ አብራው ቆየች።
ኢራቅ ከ2006 እስከ 2008 ባለው ጊዜ ደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ ወደቀች። እሱ የሱኒ ጂሃዲስት ቡድኖች ውስጥ ስለመሳተፉ ምንም ጥርጣሬ አልነበራትም። እአአ በ2010 ደግሞ የኢራቅ እስላማዊ መንግሥት መሪ ሆነ። ቡድኑ በ2006 የተቋቋመ ሲሆን የኢራቅ ጂሃድ ድርጅቶች አካል ነበር።
“እአአ ጥር 2012 ወደ ወደ ሶሪያዋ የኢድሊብ ገጠራማ አካባቢ ተዛወርን። እዚያ እያለንም እሱ አሚር [መሪ] መሆኑ ግልጽ ሆነልኝ” ስትል ኡም ሁዳይፋ ተናግራለች።
የኢራቅ እስላማዊ መንግሥት፣ ከጊዜ በኋላ በሸሪዓ ሕግ ለመተዳደር ያወጀው ዋናውን ኢስላሚክ ስቴት ቡድንን ለመመሥረት ከተባበሩት ቡድኖች አንዱ ነበር።
በዚያ ወቅትም የአፍጋኒስታኖችን ልብስ መልበስ ጀመረ። ጺሙን አሳድጎ፣ ሽጉጥ መታጠቁንም ትናገራለች።
በአገሪቱ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት በሰሜን ምዕራብ ሶሪያ የነበረው የፀጥታው ሁኔታ እየተባባሰ በመምጣቱ ወደ ራቃ ከተማ አመሩ። ከተማዋ በኋላ ላይ የአይኤስ ዋና ከተማ ተደርጋ ተወስዳለች።
ሁዳይፋ ባለቤቷን በቴሌቪዥን የተመለከተችው እዚያ ስትኖር በነበረበት ወቅት ነው።
አይኤስን ለመመሥረት የተሰባሰቡት ቡድኖች የፈጸሙት አረመኔያዊ ድርጊት አስቀድሞም የታወቀ ነበር። በአውሮፓውያን 2014 እና 2015 ግን ጭካኔው እየሰፋ እና ዘግናኝ እየሆነ መጣ።
የተባበሩት መንግሥታት ቡድን አይኤስ በኢራቅ የያዚዲ ማኅበረሰብ አባላት ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንደፈጸመ እና ግድያን፣ ማሰቃየትን፣ አፈናን እና ባርነትን ጨምሮ በሰው ልጆች ላይ ወንጀሎችን እንደፈፀመ የሚያሳይ ማስረጃ ማግኘቱን ዘግቧል።
አይኤስ የታጋቾችን አንገት መቅላትን እና አንድ ዮርዳኖሳዊ አብራሪን ከነሕይወቱ ማቃጠልን ጨምሮ የፈጸመውን አሰቃቂ ድርጊት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አሰራጭቷል።
በሌላ አጋጣሚ ደግሞ ከካምፓቸው ወደ ቤታቸው የሚመለሱ አንድ ሺህ ሰባት መቶ የኢራቅ ሠልጣኝ ወታደሮችንም ፈጅቷል።
አንዳንድ ከአይኤስ ጋር ለመኖር የሄዱ ሴቶችም ምን ውስጥ እየገቡ እንደሆነ እንዳልገባቸው ገልጸዋል። ኡም ሁዳይፋም ስለጉዳዩ ስትጠየቅ ያኔ ድርጊቱን የሚገልጹ ምሥሎችን ማየት እንዳልቻለች ገልጻለች።
“ትልቅ ድንጋጤ፣ ኢ-ሰብአዊነት እና በግፍ ደም ማፍሰስ በጣም ዘግናኝ ነገር ነው። እናም በዚህ ረገድ የሰውን ልጅ ክብር ድንበር አልፈዋል።”
ኡሙ ሁዳይፋ “የእነዚያ ንጹሃን ሰዎች ደም” በእጁ ላይ እንዳለ ለባለቤቷ በመንገር እንደሞገተችው እና “በእስልምና ሕግ መሠረት ከፈጣሪ ምህረት ለመጠየቅ ሊደረጉ የሚችሉ አማራጮች እንዳሉ” ነግረዋለች።
ባለቤቷ ላፕቶፑን ተጠቅሞ ከአይኤስ መሪዎች ጋር እንዴት ይነጋገር እንደነበርም ትገልጻለች።
ኮምፕዩተሩን ዘግቶ በቦርሳው ውስጥ ያስቀምጠዋል። “ምን እየሆነ እንደሆነ ለማወቅ ፈልጌ ለመስበር ሞከርኩኝ፤ ነገር ግን የቴክኖሎጂ መሃይም ስለነበርኩኝ ሁልጊዜም የይለፍ ቃል ይጠይቀኝ ነበር” ብላለች።

ሁዳይፋ ከባሏ ለማምለጥ ብትሞክርም፣ በፍተሻ ጣቢያ ያገኟት የታጠቁ ሰዎች እንድታልፍ ግን አልፈቀዱላትም። ወደ ቤቷም መልሰዋታል።
እስከምታውቀው ድረስ ባለቤቷ “በምንም ዓይነት ጦርነት ውስጥ” እንዳልተሳተፈ ገልጻለች። አይኤስ ሞሱልን ሲቆጣጠር ባለቤቷ በራቃ እንደነበርም ተናግራለች። አል ባግዳዲ ወደ ሞሱል ተጉዞ ንግግር ያደረገው በኋላ ላይ ነው።
ከንግግሩ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ደግሞ አል-ባግዳዲ የ12 ዓመት ሴት ልጃቸው ኡማይማን ለጓደኛቸው መንሱር ዳራት። መንሱር ቤተሰቡን እንዲጠብቅ አደራ ተሰጥቶትም ነበር። ኡም ሁዳይፋ ጋብቻውን ለማስቀረት ሞክራ አልተሳካላትም።
የኢራቅ የደኅንነት ምንጮች ግን ኡማይማ በስምንት ዓመቷ ቀደም ብላ ነው ለሶሪያው አይኤስ ቃል አቀባይ የተዳረችው ሲሉ ገልጸዋል።
የመጀመሪያው ጋብቻ የተደረገው በቤተሰብ ይሁኝታ መሆኑን እና ሰውዬው አል-ባግዳዲ በማይኖርበት ጊዜ ወደ ቤቱ እንዲገባ ቢፈቀድለትም ከልጅቱ ጋር ወሲባዊ ግንኙነት አልነበረውም።
ነሐሴ 2014 (እአአ) ደግሞ ኡም ሁዳይፋ ናሲባን የተባለች ሌላ ሴት ልጅ ወለደች። ናሲባን በተፈጥሮ የልብ ህመም ነበረባት። ይህ ወቅትም መንሱር ዘጠኝ የያዚዲ ልጃገረዶችን በባርነት ለቤተሰቡ ካመጣበት ወቅት ጋር ተገጣጠመ። ሴቶቹ ዕድሜያቸው ከዘጠኝ እስከ 30 አካባቢ ይገመት ነበር።
እነዚህ በአይኤስ በባርነት ከተያዙ በሺህዎች የሚቆጠሩ የያዚዲ ሴቶች እና ሕጻናት በጣት የሚቆጠሩት ናቸው። ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ተገድለዋል።
ኡም ሁዳይፋ በዚህ “እጅግ መደንገጧን እና ማፈሯን” ገልጻለች።

ለባርነት ወደ እነ ሁዳይፋ ቤት ከተወሰዱ የያዚዲ ልጃገረዶች መካከል ሳማር እና ዜና [ስማቸው የተለወጠ] የተባሉ ልጃገረዶች ነበሩበት።
እነዚህ ልጃገረዶች ራቃ ወደሚገኘው ቤቷ ከመዛወራቸው በፊት ለጥቂት ቀናት ብቻ እንደቆዩ ኡም ሁዳይፋ ተናግራለች። ቤተሰቡ ወደ ሞሱል ሲዘዋወር ሳማር እንደገና በመምጣት አብራቸው ለሁለት ወራት ያህል ቆይታለች።
የሳማር አባት የሆነው ሐሚድ ልጁ የተወሰደችበትን ቅጽበት በእንባ ያስታውሳል።
ሐሚድ ሁለት ሚስቶች ነበሩት። ሚስቶቹ ከ26 ልጆቹ፣ ሁለት ወንድሞቻቸው እና ቤተሰቦቻቸው ጋር ኻንሱር ሲንጃር ነበር የታገቱት። እሱ በአቅራቢያው ወደሚገኙት ተራሮች ሸሸ።
ሳማርን ጨምሮ 6 ልጆቹ እስካሁን አልተገኙም። የተወሰኑት ገንዘብ ከተከፈ በኋላ የተመለሱ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ የታሰሩባቸው ቦታዎች ነፃ ከወጡ በኋላ ወደ ቤት መጥተዋል።
የእህቱ ልጅ የሆነችው ዜና በሰሜናዊ ሶሪያ ውስጥ እንደምትገኝ ይገመታል። የዜና እህት ሶአድ ደግሞ በባርነት ተገዝታለች፤ ተደፍራለች፤ ለሰባት ጊዜም ተሸጥታለች።
ሐሚድ እና ሶአድ የያዚዲ ልጃገረዶችን በማፈን እና በባርነት በማሳተፍ በኡም ሁዳይፋ ላይ ክስ መስርተዋል።
ረዳት የሌላት ተጎጂ አለመሆኗን እና ሁዳይፋ የሞት ፍርድ እንደሚገባት እየገለጹ ነው።
“ለሁሉም ነገር ተጠያቂ ነች። ለባሏ እና ለእሷ የሚሠሩትን በመምረጥ ረገድ ሚና ነበራት. . . እህቴ ከእነዚያ ልጃገረዶች አንዷ ነበረች” ትላለች ሶአድ። ይህንንም የምትለው ወደ ቤታቸው ከተመለሱት ሌሎች ሴቶች ከሰማችው ምስክርነት ተነስታ ነው።
“እሷ የወንጀለኛው አቡበከር አል-ባግዳዲ ሚስት ነች፤ እሷም እንደ እሱ ወንጀለኛ ነች” ትላለች።
ከሶአድ ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ ኡም ሁዳይፋ እንድትሰማው የተደረገ ሲሆን፣ እሷም “ባለቤቴ ወንጀለኛ መሆኑን አልክድም። በእነሱ ላይ በደረሰው ነገር በጣም አዝኛለሁ” በማለት የቀረበባትን ውንጀላዎች ውድቅ አድርጋለች።

ኡም ሁዳይፋ ጥቂት ቆይታ በአውሮፓውያኑ 2015 ታግታ የነበረችውን አሜሪካዊቷን የእርዳታ ሠራተኛ ኬይላ ሙለርን ለአጭር ጊዜ አግኝታት እንደነበር ገልጻለች። ሙለር ለ18 ወራት ታግታ በቆየችበት ሕይወቷ አልፏል።
ሁዳይፋ ራቃ ወደሚገኝ መጠለያ ቤት ከተወሰደች በኋላ ከላይ ካለው ክፍል ድምጽ በመስማቷ መመርመር ጀመረች። መኝታ ክፍሉ ውስጥ ኬይላን አገኘቻት። “ደስተኛ ትመስል ነበር . . . የሼኹ ባለቤት እንደሆነች ነገረችኝ . . . ባለቤቴን ማለቷ እንደሆነ ገባኝ።”
ኬይላ ስለእሱ “በፍቅር” ስለምታወራ ቅናት ወረረኝ ትላለች። ይህ የሆነው የታመመችውን ልጇን ናሲባን ለማዳን በምትታገልበት ጊዜ ነበር። ልጇ በኋላ ላይ ሕይወቷ አልፏል።
ይህ ግን ከኬይላ ጋር ታስረው የነበሩ ሰዎች ከሰጡት ምስክርነት በእጅጉ ይለያል። ኬይላ ከሞተች በኋላ እናቷ ማርሻ ከሌሎች እስረኞች በሰማችው ላይ ተመሥርታ እንደተናገረችው ከሆነ “ያ ሰው አላገባትም። ይልቁንም አል-ባግዳዲ በኃይል ወስዶ ደፈራት። ከክፍሉም እያለቀሰች ተመልሳለች።”
ከፖሊስ ጋር አብሮ የሠራ አንድ ባለሙያ በበኩሉ ኬይላ፣ ኡም ሁዳይፋ የገለፀችውን ካደረገች፣ ለመትረፍ ስትል ያደረገችው አንደኛው ብልሃቷ ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል።
በኬይላ አሟሟት ዙሪያ ያለው ሁኔታ እስካሁን አይታወቅም። በወቅቱ አይኤስ በዮርዳኖስ የአየር ጥቃት መገደሏን ተናግሯል። አሜሪካ ግን አስተባብላለች። የኢራቅ የደኅንነት ምንጭ ደግሞ በአይኤስ መገደሏን ነው የሚያመለክቱት።
እአአ በ2019 የአሜሪካ ጦር አል-ባግዳዲ ያለበትን ቦታ ወረረ። ባግዳዲ በዋሻ ውስጥ ራሱ ላይ ያጠመደውን ፈንጂ ካፈነዳ በኋላ እራሱን እና ሁለት ልጆቹን ሲገድል፣ ከአራቱ ሚስቶቹ ሁለቱም ተገደሉ።
ኡም ሁዳይፋ ግን እዚያ አልነበረችም። እአአ በ2018 በተያዘችበት ቱርክ ውስጥ ማንነቷን ቀይራ ትኖር ነበር። በተመሳሳይ ዓመትም ወደ ኢራቅ ተላከች። በእስር ላይ ሆና ከአይኤስ ጋር ያላት ግንኙነት እየተመረመረ ነው።
ትልቋ ልጇ ኡማይማ ከእርሷ ጋር ታስራለች። የ12 ዓመቷ ፋጡማ ደግሞ በወጣቶች እስር ቤት ውስጥ ትገኛለች። አንድ ልጇ በሶሪያ በሆምስ አቅራቢያ በሩሲያ የአየር ጥቃት ተገድሏል። ሌላኛው ደግሞ ከአባቱ ጋር በዋሻው ውስጥ ሞቷል። ትንሹ ልጇ ደግሞ በሕጻናት ማሳደጊያ ውስጥ ነው።
ሁዳይፋ ቃለ መጠይቁን ስትጨርስ ፊቷን ቀና አደረገች። በፊቷ ላይ የሚነበብ ምንም ነገር አልነበረም። የደኅንነት ኃላፊው ሲወስዳት ስለትንንሽ ልጆቿ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ስትማጸን ነበር።
ሁዳይፋ አሁን ወደ እስር ቤት ክፍሏ ተመልሳ የወንጀል ክስ ይቀርብባት እንደሆነ ለማወቅ በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች።