
10 ሰኔ 2024
ተሻሽሏል ከ 3 ሰአት በፊት
የማላዊውን ምክትል ፕሬዝዳንት እና ሰኞ ዕለት በተሰወረው ወታደራዊው አውሮፕላን አብረዋቸው ሲገወዙ የነበሩ ሰዎች በሙሉ መሞታቸውን የአገሪቱ ፕሬዝዳንት አስታወቁ።
ፕሬዝዳንት ላዛረስ ቻክዌራ ዛሬ ማክሰኞ እኩለ ቀን ላይ ይፋ እንዳደረጉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ እና ሌሎቹ ተጓዦች አውሮፕላኑ ወድቆ ሲከሰከስ “በደረሰው አደጋ ሕይወታቸው አልፏል” ሲሉ ገልጸዋል።
የአውሮፕላኑ ስብርባሪ ከአንድ ኮረብታ አቅራቢያ “ሙሉ ለሙሉ ወድሞ” መገኘቱን እና አንድም በሕይወት የተረፈ ሰው እንደሌለ ገልጸዋል።
ምክትል ፕሬዝዳንት ሳውለስ ቺሊማን እና ሌሎች ዘጠኝ ሰዎች ሲጓዙበት የነበረው አውሮፕላን በሰሜን የአገሪቱ ክፍል በሚገኝ ጫካ ውስጥ ወድቆ ሳይከሰከስ እንዳልቀረ አንድ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣን ማክሰኞ ረፋድ ላይ ተናግረው ነበር።
በመጥፎ የአየር ሁኔታ ውስጥ እየበረረ እንደነበር የተነገረው ወታደራዊ አውሮፕላን በአገር ውስጥ በረራ ላይ ሳለ ነበር ከአየር ማረፊያ ራዳር ውጪ ሆኖ የተሰወረው።
የማላዊ መከላከያ ኃይሎች አዛዥ ፖል ቫለንቲኖ ፊሪ ዛሬ ማክሰኞ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በስፍራው ያለው ጭጋግ ዕይታን በማስተጓጎል የፍለጋ ጥረቱን ውስብስብ አድርጎታል።
የማላዊ መከላከያ ኃይል ንብረት የሆነው አውሮፕላን ከዋና ከተማዋ ሊሎንዌ ሰኞ ጠዋት ከተነሳ በኋላ “ከራዳር ዕይታ ውጪ” በመሆን መሰወሩን የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ ላይ ትናንት አስታውቋል።
አውሮፕላኑ ከዋና ከተማዋ ከተነሳ በኋላ ሰኞ ረፋድ ከአራት ሰዓት በኋላ በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ውስጥ ከሚገኘው ምዙዙ ኢንተርናሽናል አየር ማረፊያ ይደርሳል ተብሎ ሲጠበቅ ነበር።
የአገሪቱ የአቪዬሽን ባለሥልጣናት ከአውሮፕላኑ ጋር ግንኙነት ለማድረግ ሳይችሉ መቅረታቸውን ተከትሎ የማላዊው ፕሬዝዳንት የፍለጋ እና ነፍስ የማዳን ተልዕኮ እንዲካሄድ አዘው ነበር።
ከምክትል ፕሬዝዳንቱ በተጨማሪ በአውሮፕላኑ ውስጥ በርካታ የፓርቲያቸው ባለሥልጣናት ነበሩ።
የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ላዛረስ ቻክዌራ ሰኞ አመሻሽ ላይ ባደረጉት ንግግር ምክትል ፕሬዝዳንታቸው ያሉበትን አውሮፕላን የመፈለግ እና ነፍስ የማዳን ሥራው መቀጠሉን አሳውቀው ነበር።
ክስተቱን ልብ የሚሰብር ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ “ወታደሮች አደጋው ደርሶበታል ከተባለው ስፍራ ተሰማርተው ፍለጋ እያደረጉ ሲሆን፣ አውሮፕላኑ እስኪገኝ ድረስ ፍለጋው እንዲቀጥል ጥብቅ ትዕዛዝ አስተላልፊያለሁ” ብለዋል።
“ሁላችንም ፈርተናል፤ እኔም በእጅጉ ተጨንቄያለሁ። ነገር ግን አውሮፕላኑን ፈልጎ ለማግኘት እና በሕይወት የተረፉትንም ለመታደግ ማድረግ የምንችለውን ነገር ሁሉ እናደርጋለን” ብለው ነበር።
- ሩሲያ ታላላቅ ሳይንቲስቶቿን እያሰረች በአገር ክህደት የምትከሰው ለምንድን ነው?10 ሰኔ 2024
- ኢራን ፕሬዝዳንቷን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯን ያጣችበት የሄሊኮፕተር አደጋ21 ግንቦት 2024
- የኢራኑ ፕሬዝዳንት ስለሞቱበት የሄሊኮፕተር አደጋ እስካሁን የምናውቀው20 ግንቦት 2024
ነገር ግን የምክትል ፕሬዝዳንቱ ፓርቲ በተካሄደው የፍለጋ እና የነፍስ አድን ሥራ “ደስተኛ አለመሆኑን” አሳውቋል።
የፓርቲው ባለሥልጣናት እንዳሉት የምክትል ፕሬዝዳንቱ አውሮፕላንን ፍለጋ የተጀመረው መጥፋቱ ከታወቁ ከሰዓታት በኋላ ነው በማለት ቅሬታውን ገልጿል።
የማላዊ ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንቱ በ2020 የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ በተፈጠረ ጥምረት ከተለያዩ ፓርቲዎች የመጡ ናቸው።
ምክትል ፕሬዝዳንቱን የያዘው አውሮፕላን መጥፋት በአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት አዛዥ ከተነገራቸው በኋላ የማላዊው ፕሬዝዳንት ላዛረስ ቻክዌራ ሰኞ ምሽት ወደ ውጭ አገር (በሃማስ) ሊያደርጉት የነበረውን ጉዟቸውን ሰርዘዋል።
የአገሪቱ ጦር አዛዥ ጄኔራል ቫለንቲኖ ፊሪ ለፕሬዝዳንቱ ክስተቱን ባሳወቁበት ጊዜ ለአውሮፕላኑ መሰወር ምክንያቱ ምን እንደሆነ እንዳልታወቀ ተናግረው ነበር።
የተጓዙበት አውሮፕላን አደጋ የደረሰበት ምክትል ፕሬዝዳንቱ መንግሥትን ወክለው ከሦስት ቀናት በፊት ባረፉት በአንድ የቀድሞ የምክር ቤት አባል የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት በመጓዝ ላይ ነበሩ።
ምክትል ፕሬዝዳንቱ ወደ ፖለቲካው ዓለም ከመግባታቸው በፊት ዩኒሊቨር እና ኮካኮላን በመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ውስጥ በከፍተኛ የመሪነት ቦታ ላይ ሠርተዋል።
ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት የሆኑት የ51 ዓመቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ቺሊማ የደቡባዊ አፍሪካዊቷ አገር ማላዊ ምክትል ፕሬዝዳንት በመሆን ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ እያገለገሉ ነበር።
በአውሮፓውያኑ 2022 ምክትል ፕሬዝዳንት ቺሊማ ገንዘብ ተቀብለው የመንግሥት ኮንትራቶችን ከተገቢው ሂደት ውጪ ሰጥተዋል በሚል ተከሰው በቁጥጥር ሥር ውለው ነበር።
ነገር ግን ባለፈው ወር ጉዳዩን የተመለከተው ፍርድ ቤት ምንም ዓይነት ምክንያት ሳይሰጥ በምክትል ፕሬዝዳንቱ ላይ የቀረበውን ክስ ውድቅ አድርጎታል።