
11 ሰኔ 2024, 07:39 EAT
ተሻሽሏል ከ 2 ሰአት በፊት
አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን የሆኑ ስደተኞችን አሳፍራ ስትጓዝ የነበረች ጀልባ ከየመን የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ ተገልብጣ ቢያንስ 49 ሰዎች መሞታቸውን ተገለጸ።
ከአደጋው የተረፉ ሰዎች ለነፍስ አድን ሠራተኞች እንደተናገሩት ጀልባዋ 260 የሚጠጉ ሰዎችን አሳፍራ የነበረ ሲሆን፣ ለመገልበጥ የበቃችውም በካባድ ነፋስ ምክንያት ነው ተብሏል።
መሞታቸው ከታወቀው 49 ሰዎች ውጪ ሌሎች 140 ሰዎች እስካሁን የደረሱበት ያልታወቀ ሲሆን፣ እነሱን ለማግኘት ፍለጋ እየተደረገ ነው።
የተመድ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት በዚህ አሳዛኝ አደጋ ሕይወታቸውን ካጡት መካከል 31 ሴቶች እና ስድስት ሕጻናት ይገኙበታል ብሏል።
ከአደጋው የተረፉ ስደተኞች እንደሚሉት ከሆነ ይህን አደገኛ የባሕር ላይ ጉዞ 90 ሴቶች እና ሕጻናትን የሚጨርም 145 ኢትዮጵያውያን እና 115 ሶማሊያዊያን ከቦሳሶ የተነሱት እሁድ ሰኔ 2/2016 ዓ.ም. ንጋት ላይ ነበር።
ከየመን ዋና ከተማ አደን በስተምሥራቅ የምትገኘው የሩደም አካባቢ ባለሥልጣናት እንዳሉት አደጋው በደረሰባት ጀልባ ላይ ተሳፈረው ከነበሩት አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን እና ሶማሊያዊያን ስደተኞች ሲሆኑ፣ የመንን ወደ ባሕረ ሰላጤው አገራት ለመሸጋገሪያነት ይጠቀሙባታል።
የሩደም አካባቢ አስተዳዳሪ የሆኑት ሃዲ አል-ኹርማ ለሮይተርስ ዜና ወኪል እንደተናገሩት በጀልባዋ ላይ የመስመጥ አደጋው የደረሰው ወደ ባሕር ዳርቻው ከመቃረቧ በፊት ነው።
በስፍራው የነበሩ ሰዎች 250 የሚሆኑ ስደተኞችን አሳፍራ አደጋው የደረሰባት ጀልባ ላይ የነበሩ በርካታ ሰዎችን ሕይወት ማትረፋቸው ተነግሯል።
- ከ20 በላይ ኢትዮጵያውያን የሞቱበት የጀልባ አደጋ የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በስደተኛው አንደበት25 ሚያዚያ 2024
- የትግራይ ከተሞች ነዋሪዎችን በፍርሃት እያራደ ያለው የእገታ እና የዘረፋ መበራከት11 ሰኔ 2024
- በ2017 የፌደራል መንግሥት በጀት ላይ የ358.5 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ጉድለት መታየቱ ተገለጸ10 ሰኔ 2024
“ዓሳ አስጋሪዎች እና ነዋሪዎች አብረዋቸው በጀልባዋ ላይ የነበሩ 100 የሚሆኑት ሰዎች የደረሱበት አለመታወቁን የተናገሩ 78 ሰዎችን በሕይወት አድነዋል” ሲሉ ባለሥልጣኑ ተናግረዋል።
በአደጋው ምክንያት የጠፉትን ሰዎች ለማግኘት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም ቅኝት በሚያደርጉ ጀልባዎች እጥረት ምክንያት ፍለጋው በሚፈለገው መጠን ማከናወን እንዳልተቻለ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ገልጿል።
አይኦኤም ከአደጋ በሕይወት ለተረፉ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ሁለት ጊዜያዊ ክሊኒኮችን ማቋቋሙን የገለጸ ሲሆን 8 ስደተኞች ተጨማሪ የጤና ክትትል ስላስለፈለጋቸው ወደ ሆስፒታል መላካቸውን ጭምሮ ገልጿል።
ድርጅቱ ሕይወታቸው ያለፉ ስደተኞች በየመን አይን-ባማዴብ በተባለ የመቃብር ስፍራ ቀብራቸው መፈጸሙን በመግለጫው አመልክቷል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት እንደሚያመለክተው ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ብቻ 97,000 ስደተኞች በጦርነት ውስጥ ወደ ምትገኘው የመን ገብተዋል።
በየመን ያለው ጦርነት እና በቅርቡ የየመን ሁቲ ታጣቂዎች በቀይ ባሕር ላይ ጥቃት እየሰነዘሩ ቢሆንም ስደተኞች ወደ አገሪቱ በአደጋኛ የባሕር ጉዞ መግባታቸውን ቀጥለዋል።
ከጂቡቲ በመነሳት በሕገወጥ መንገድ በቀይ ባሕር በኩል ወደ ሳዑዲ አረቢያ እና ሌሎች የባሕረ ሰላጤው አገራት በሚጓዙ ስደተኞች ላይ ተመሳሳይ አደጋ በተደጋጋሚ ሲደርስ ቆይቷል።
በዚህ አደገኛ መንገድ የሚጓዙት አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፣ ለሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ከፍተኛ ገንዘብ ከመክፈላቸው በተጨማሪ እንግልት እና በደል እንደሚደርስባቸው ይናገራሉ።
ባለፈው ሚያዝያ ወር ላይ ብቻ በተከታታይ በደረሱ ሁለት አደጋዎች 60 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ባሕር ውስጥ ሰምጠው ለሞት መዳረጋቸው መዘገቡ ይታወሳል።