June 23, 2024 – Konjit Sitotaw

” ከ4 በላይ ወረርሽኞች ተከስተዋል። ከ2,400 በላይ ሰዎች በወረርሽኙ ተጠቅተዋል። ከፍተኛ ሞት አለ ” – የዋግኸምራ ብሔረሰብ ጤና መምሪያ

በአማራ ክልል ፤ በዋግኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ከተከሰተ በሰነበተው ድርቅ ሳቢያ ከአራት በላይ ወረርሽኞች መከሰታቸውን ተከትሎ ሰዎችና እንስሳት እየሞቱ መሆኑን ዞኑ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገለጸ።

የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊው አቶ አሰፋ ነጋሽ በሰጡት ቃል፣ ” ከ4 በላይ ወረርሽኞች ተከስተዋል። ከ2,400 በላይ ሰዎች በወረርሽኙ ተጠቅተዋል። ከፍተኛ ሞት አለ ” ብለዋል።

በወረርሽኙ ምን ያህል ሰዎች ሞተዋል ? ለሚለው ጥያቄ፣ ” ሞቱ ከፍተኛ ነው። ቁጥሩን Specifically ለመናገር እርግጠኛ አይደለሁም ” ነው ያሉት።

ቢያንስ ከ5,000 በላይ እንስሳት እንደሞቱ፣ ለመከተብ አቅም እንዳልተገኘ፣ በሽታው (አባሰንጋ) ከእንስሳት ወደ ሰው እየተላለፈ መሆኑን ገልጸው፣ ከአንድ ወረዳ ብቻም ወደ  140 ሰዎች አባሰንጋ እንደተላለፈባቸው አስረድተዋል።

– ኮሌራ
– ኩፍኝ
– እከክና
– አባሰንጋ (የከብት በሽታ) እና ሌሎች ወረርሽኞች በሁሉም በሚባል ደረጃ በብሔረሰብ አስተዳደሩ ላይ ተከስተዋል ሲሉ ተናግረዋል።

” ኩፍኝ በሁሉም ወረዳዎች ተከስቷል። በጣም ብዙ ቁጥር ያላቸው ህፃናት ታመውብናል ” ያሉት አቶ አሰፋ፣ ” ለወረርሽኙ ምላሽ ክትባት እየሰራን ነው ” ብለዋል።

” እከክ በተለይ ድርቁ በስፋት ባጠቃቸው ወረዳዎች ተከስቶ ነበር ለመቆጣጠር እየተሞከረ ነው። የውሃ አቅርቦት፣ የንጽህ እና መጠበቂያ ግብዓት ካልቀረበ እሱንም መቅጣጠር እጅግ አስቸጋሪ ነው ” ነው ያሉት።

ድርቅ ከመከሰቱ በፊትም አካባቢው ትርፍ አምራች ስላልነበር የምግብ እጥረት እንደነበር አሁን የድርቁ መከሰት የምግብ እጥረቱን እጅጉን እንዳባባሰው ፤ የሥርዓተ ምግቡን ችግርም መቀልበስ እንዳልተቻለ አስረድተዋል።

ሞቱን ለመከላከል የሚሰጠውን ህክምና አጠናክረው እንደቀጠሉ የገለጹት ኃላፊው፣ ” በተለይ መካከለኛ የምግብ እጥረት ያለባቸውን ህጻናትና እናቶች ተደራሽ ለማድረግ የጸጥታ ችግሩ በጣም አስተቸጋሪ ሆኗል ” ብለዋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም እርዳታዎች እንደተቀዛቀዙ አስረድተው፣ ” በጸጥታ ምክንያት ተደራሽ ያልሆኑ እናቶችና ህጻናት ምንም እየተደረገላቸው አይደለም ” ብለዋል።

ያለው የምግብ እጥረት በቋሚነት ካልተቀረፈ ችግሩን መቀልበስ ፈተና ስለሆነ አጋር ድርጅቶች ርብርብ ኦንዲያደርጉ ዞኑ ጥሪ አቅርቧል።