የወልዲያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች
የምስሉ መግለጫ,የወልዲያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች

26 ሰኔ 2024, 15:24 EAT

የገንዘብ ሚኒስቴር ለመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች የሚመደበው የተማሪዎች የምግብ በጀት በሚቀጥለው ትምህርት ዘመን እንደሚሻሻል አስታወቀ።

ይህን በጀት ለማሻሻል የገንዘብ እና ትምህርት ሚኒስቴሮች እንዲሁም የስታትስቲክስ አገልግሎት በጋራ ጥናት እያካሄዱ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር የበጀት ጉዳዮች አማካሪ አቶ ተፈሪ ደመቀ ተናግረዋል።

አቶ ተፈሪ ይህን ተናገሩት የ2017 ዓ.ም. የፌደራል መንግሥት በጀትን አስመልክቶ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባካሄደው የሕዘብ ውይይት ላይ ነው።

በዛሬው የውይይት የተገኙ ሁለት የዩኒቨርሲቲ ተወካዮች የትምህርት ተቋማት ተማሪዎቻቸውን ለመመገብ እየተቸገሩ መሆኑን ለቋሚ ኮሚቴው እና ለገንዘብ ሚኒስቴር አመራሮች አስረድተዋል።

ከእነዚህ ተወካዮች መካከል እንዱ የሆኑት የአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ለሚ ጉታ፤ “የተማሪ ቀለብ አሁን ባለበት [ሁኔታ] የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት 2017 ላይ ተማሪን ተቀብሎ ማስተማር የምንቸገርበት ሁኔታ ነው ያለው” ሲሉ ተናግረዋል።

“ጥናት እየተካሄደ መሆኑን እንሰማለን” ያሉት ዶ/ር ለሚ፤ “ይሄ ጥናት ተጠናቅቆ የሚመለከተው አካል የመፍትሔ ሃሳብ እንዲሰጥ” ጠይቀዋል። ዶ/ር ለሚ መፍትሔ ካልተሰጠ፤ “አሁን ባለው ሁኔታ በሚቀጥለው ዓመት የመማር ማስተማሩን ለማስቀጠል የምንቸገር ይሆናል” ብለዋል።

እንደ ዶ/ር ለሚ ሁሉ የሰመራ ዩኒቨርሰቲን ወክለው የመጡ አቶ ሀሰን ተባሉ የውይይቱ ተሳታፊ፤ “ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ተቋቁመን መግፋት ስለማንችል የመማር ማስተማር ሂደቱም እየከበደን ስለሆነ ክቡር ምክር ቤቱ ይሄን ነገር [እንዲያይልን]” ሲሉ ጠይቀዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስቴር የበጀት ጉዳዮች አማካሪ አቶ ተፈሪ ደመቀ፤ “አሁን ያለው የተማሪዎች የምግብ በጀት አነስተኛ ነው ይታወቃል” ሲሉ በዩኒቨርሲቲ ተወካዮች የተነሳውን ሃሳብ አስተጋብተዋል።

ይህን የበጀት ጉዳይ ማሻሻል እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት አቶ ተፈሪ፤ “ይኼንን ለማሻሻል ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር እና የስታትስቲክስ አገልግሎትም ያለበት ጥናት እየተካሄደ ነው” ብለዋል።

አቶ ተፈሪ “መንግሥትን አቅም እና አሁን ያለውን የዋጋ ንረት በተወሰነ ደረጃ በማጣጣም የሚሠራ ነው” ያሉት ይህ ጥናት “በቀጣይ ዓመት የትምህርት ካላንደር ከመጀመሩ በፊት ተጠናቅቆ” ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ ገልጸዋል።

ጥናቱ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ውሳኔ ካገኘ በኋላ በጀቱ “ከመጠባበቂያ በጀት የሚሸፈን” መሆኑን አማካሪው አክለዋል።

ከአስር ቀናት በኋላ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይጸድቃል ተብሎ የሚጠበቀው የ2017 ዓ.ም. በጀት፤ “አሁኑ ባለው የተማሪ ቁጥር፣ ባለው ተመን መሠረት” መያዙን አቶ ተፈሪ ለቋሚ ኮሚቴው ተናግረዋል።

አቶ ተፈሪ አክለውም፤ “በቀጣይ ሊኖር የሚችለው የተማሪ ቁጥር መሠረት ያደረገ በሚወሰነው ውሳኔ መሠረት የምግብ በጀቱ ተሰልቶ ለእያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ በጀት መልክ ከመጠባበቂያ በጀት የሚሸፈን [ነው]” ብለዋል።

የገንዘብ ሚኒስቴር ዲኤታው ዶ/ር እዮብ ተካልኝ በበኩላቸው፤ “አሁን ያለው አሠራር አይቀጥልም” ሲሉ ተናግረዋል።

ሚኒስቴር ዲኤታው አክለውም፤ “ይሄ ጥናት ትምህርት ከመጀመሩ በፊት [በሚኒስትሮች] ምክር ቤት ጸድቆ ተግባራዊ እንዲሆን አቅደን ያንን የጊዜ ሰሌዳ የጠበቀ ሥራ እየሠራን ነው” ብለዋል።

ባለፉት ወራት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ለተማሪ የቀን ቀልብ በሚመደብላቸው 22 ብር ተማሪዎቻቸውን ለመመገብ አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው ሲገልጽ ነበር።