ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ
የምስሉ መግለጫ,ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ

ከ 9 ሰአት በፊት

የተለያዩ ታክሶችን ለመጣል በታቀደው የፋይናንስ ረቂቅ ሕግ ምክንያት ደም አፋሳሽ ተቃውሞ የገጠማቸው የኬንያው ፕሬዝዳንት ሕጉ ተግባራዊ እንዲሆን የሚፈቅደውን ፊርማቸውን እንደማያኖሩ አስታወቁ።

ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ማክሰኞ ሰኔ 18/2016 ዓ.ም. በዋና ከተማዋ ናይሮቢ እና በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች የተካሄደውን ተቃውሞ ተከትሎ ቢያንስ 20 ሰዎች ከተገደሉ በኋላ ነው አወዛጋቢውን የፋይንስ ሕግ ተግባራዊ እንደማይሆን ያስታወቁት።

በአገሪቱ ያለውን የኑሮ ውድነት ያባብሰዋል በሚል በወጣት ኬንያውያን በተመራው ተቃውሞ ሰልፈኞች የአገሪቱን ፓርላማ አጥር ጥሰው በመግባት ተቃውሟቸውን አሰምተው የነበረ ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ በርካታ ሰዎች ለሞት እና ለጉዳት ተዳርገዋል።

የተፈጠረው ቀውስ ከፖሊስ ቁጥጥር በላይ በመሆኑ ምክንያትም የአገሪቱ ጦር ሠራዊት እንዲሰማራ ተደርጎ ቁጥጥር እያደረገ ሳለ ነው ፕሬዝዳንቱ ከከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸው ጋር ሆነው አወዛጋቢው የፋይናንስ ሕግ ተግባራዊ እንደማይሆን ያስታወቁት።

“ኬንያውያን በሕጉ ዙሪያ ያሰሙትን ተቃውሞ በደንብ ተከታትያለሁ፤ ስለዚህም ሕጉን እንደማይፈልጉት በግልጽ ተናግረዋል፤ ይህንንም ተቀብዬ በሕጉ ላይ አልፈርምም፣ ስለዚህም ቀሪ ይሆናል። ሕዝቡ ፍላጎቱን አሳውቋል” ሲሉ ለኬንያውያን አሳውቀዋል።

ከባዱ ተቃውሞ እየተካሄደ ሳለ ተሰብስበው የነበሩት የሕዝብ እንደራሴዎች ፓርላማው በተቃዋሚዎች ከመወረሩ በፊት ሕጉን በአብላጫ ድምጽ አጽድቀውት ነበር።

ሕጉ በፓርላማው ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ተግባራዊ ለመሆን በሁለት ሳምንታት ውስጥ በፕሬዝዳንቱ ፊርማ ይሁንታን ማግኘት ነበረበት።

ፕሬዝዳንት ሩቶ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ካጋጠሟቸው ተቃውሞዎች ውስጥ ከባድ ተቃውሞዎች መካከል አንዱ ለሆነው ለዚህ ሕዝባዊ ቁጣ እጃቸውን በመስጠት አዲሱ የታክስ ሕግ ተግባራዊ እንደማይሆን ገልጸዋል።

ሩቶ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ለሕዝቡ በተሰራጨው ንግግራቸው ሕዝቡ ረቂቅ ሕጉን እንደማይፈልገው በመግለጹ “በዚህ ተስማምቻለሁ” በማለት ነው በሕጉ ላይ ፊርማቸውን እንደማያኖሩ የተናገሩት።

ማክሰኞ ዕለት በተካሄደው ተቃውሞ ቢያንስ 22 ሰዎች መገደላቸውን መንግሥታዊው የኬንያ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ድርጅት አስታውቋል።

ፕሬዝዳንት ሩቶ ጨምረውም ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ግዙፍ ነው የተባለው ተቃውሞውን ካንቀሳቀሱት ወጣቶች ጋር እንደሚወያዩም ገልጸዋል።