
26 ሰኔ 2024, 15:31 EAT
ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባን ጨምሮ በአማራ ክልል ሰባት ዞኖች ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ለተካሄዱ ውይይቶች ማጠቃለያ ነው የተባለ ‘የሰላም ጉባኤ’ ሰኔ 17 እና 18/2016 ዓ.ም. በባሕር ዳር ተካሂዷል።
ከተለያዩ ዞኖች የተወከሉ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ናቸው የተባሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት ጉባኤው ሲቪል ባለሥልጣናት እና የመከላከያ አዛዦችንም ያካተተ ሲሆን፤ ለክልሉ የሰላም እጦት መላ ለመፈለግ ያለመ እንደነበር በጉባኤው መግቢያ ላይ ተገልጿል።
ከ600 እስከ 700 ይሆናሉ የተባሉ ሰዎች የተሳተፉበት ጉባኤው፤ በሁለት ቀናት ቆይታው በክልሉ ላለው ቀውስ መፍትሄ ለመፈለግ የወጠነ እንደነበር አንድ የስብሰባው ተሳታፊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በጉባኤው ላይ “ከፍተኛ እሮሮ” ቀርቧል ያሉት ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉት ታዳሚ፤“ክልሉ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ድቀት ውስጥ እየገባ ነው፤ ይሄ ጦርነት አሸናፊ የሌለው የእርስ በእርስ ጦርነት ነው፤ ወንድም ወንድሙን እየገደለበት ያለ ጦርነት ነው. . .” የሚል ጥቅል ሀሳብ በአመዛኙ መነሳቱን ገልጸዋል።
የንጹሃን ግድያም በስብሰባው ተካፋዮች ዘንድ በስፋት እንደተነሳ የጠቆሙት የስብሰባው ተካፋይ፤ አጠቃላይ ክልሉ ቀውስ ውስጥ መግባቱ ከትምህርት ገበታቸው የራቁ ተማሪዎችን እና ህክምና ማግኘት ያልቻሉ እናቶችን በአስረጅነት በማቅረብ በስብሰባው ታዳሚዎች መነሳቱን ገልጸዋል።
“. . . ‘[በጦርነት] ማሸነፍም መሸነፍም ያለ ነው፤ ግን በመሃል ንጹሃን እየተጎዱ ነው።ንጹሃን በየቀኑ እየሞቱ ነው፤ ከመሞቱም [በተጨማሪ] እየታገተ በሚሊዮኖች ብር እየተጠየቀበት ነው’ የሚለው ነገር በስፋት ተነስቷል” ብለዋል።
በጉባኤው ለአማራ ክልል ቀውስ መፍትሄው መነጋገር እንደሆነ በተሳታፊው በስፋት መነገሩን የገለጹት ተሳታፊው፤ በታዳሚው ስምምነት ላይ እንደተደረሰበት ተናግረዋል።
“ገደብ የሌለው፤ ቅድመ ሁኔታ ያልተቀመጠበት ንግግር ይደረግ፤ በንግግር ይፈታ፤ ንግግሩ እንደ ሁኔታው በክልል ደረጃ ሊፈታ ይችላል፤ በአገር ደረጃ ሊፈታ ይችላል፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ተሳትፎበት ሊፈታ ይችላል፤ ብቻ በየትኛውም [መንገድ] ይሁን የአማራን ሕዝብ ጥቅም ይዤ ወጥቻለሁ ከሚለው ኃይል ጋር ድርድር እንዲደረግ በሚል ነው ከፍተኛ ሀሳብ ሲነሳ የነበረው” ብለዋል።
መንግሥትም መፍትሄ ነው ተብሎ ለቀረበለት የድርድር ጉዳይ ‘እቀበላለሁ’ የሚል ምላሽ እንደሰጠ ተሳታፊው ጠቁመዋል።
“’እናንተ [ተሳታፊዎች] መፍትሄ ያመጣል ብላችሁ ካሰባችሁ ድርድር እቀበላለሁ፤ ግን እየተቸገርኩ ያለሁት ከማን ጋር ነው የምደራደረው? ፋኖ አስራ ምናምን አደረጃጀት ነው ያለው፤ እናንተ የጋራ አድርጋችሁ የምታመጧቸው ከሆነ፤ በጋራ ተወካይ መደራደር የሚችሉ ከሆነ መደራደር እንችላለን’ የሚል [ምላሽ] ተሰጥቷል” ብለዋል።
ለዚህም መንግሥትን እና የፋኖ ኃይሎችን ለድርድር እንዲቀመጡ የሚያደርግ የአገር ሽማግሌዎችን ያካተተ 15 አባላት ያሉት “የድርድር አመቻች ኮሚቴ” መመረጡን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
- የመከላከያ እና የፖሊስ አዛዦች ከአማራ ተወላጆች ጋር ባደረጉት ስብሰባ ምን ምን ጉዳዮች ተነሱ?21 ሰኔ 2024
- በአማራ ክልል ሁለት የጎጃም ዞኖች በቀናት ልዩነት “በመንግሥት ኃይሎች” ከ20 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ18 ሰኔ 2024
- እነ አርቲስት አማኑኤል ሀብታሙ በ50 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈቱ ፍርድ ቤት ፈቀደ20 ሰኔ 2024
“ከማኅበረሰቡ የተመረጠ ነው” የተባለው ኮሚቴ ሁለቱን ተፋላሚ ኃይሎች በማቀራረብ ለድርድር “ሁኔታዎችን መፍጠር” ተልዕኮው መሆኑን የጠቆሙት ተሳታፊው፤ ኮሚቴው ሁለቱን ኃይሎች እንደሚያነጋግር ይጠበቃል።
“[መንግሥት እና የፋኖ ታጣቂዎች] በፈለጉት አካል፣ በመረጡት ቦታ፣ በመረጡት ጊዜ፣ በመረጡት አጀንዳ እንዲነጋገሩ፤ የሕዝቡ ሰቆቃ እንዲቆም” ኮሚቴው የማቀራረብ ሥራ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
መንግሥት ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ለንግግር በሬ ክፍት ነው ቢልም በተጨባጭ ስለወሰዳቸው እርምጃዎች ግን የሚታወቅ ነገር የለም።
ባለፉት ቀናት የክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ያተኮሩ ስምንት ‘መድረኮች’ በአዲስ አበባ፣ በጎንደር፣ በደብረ ብርሃን እና በሌሎችም ከተሞች የተደረጉ ሲሆን፤ በውይይቶቹ የመንግሥት አቋምና ሀሳብ ያመዘነበት እንዲሁም የአቋም መግለጫ ተብለው የወጡ መግለጫዎች ይዘት ጥያቄዎች ተነስተውበታል።
የእነዚህ ውይይቶች ማጠቃለያው ነው በተባለው የባሕር ዳሩ ‘የሰላም ጉባኤ’ “የተሻለ” መደማመጥ የታየበት እንደነበር ተሳታፊው ጠቁመዋል።
የባሕር ዳሩን ጉባኤ መጠናቀቅ ተከትሎ “ባለ 10 ነጥብ መግለጫ” የወጣ ሲሆን፤ “የተሳታፊው ሀሳብ” የተንጸባረቀበት እንደነበር ያነሱት ተሳታፊው፤ መግለጫው ከመውጣቱ አስቀድሞ በተወካይ ተሳታፊዎች ግምገማ ተደርጎበታል ብለዋል።
ለአብነትም የድርድር ጉዳይ በስፋት ተነስቶ በመግለጫውም መካተቱ እና በመንግሥት ለፋኖ የሚሰጡ እንደ “ጽንፈኛው” እና “ጃዊሳ” የሚሉ የብይን ስሞች “ጫካ ያሉ ወንድሞቻችን” በሚል እንዲስተካከል መደረጉ “የተሻለ” አስብሎታል።
መግለጫው ስለ ኮሚቴው መቋቋም ባይገልጽም፤ ለሕዝቡ ህልውና ሲባል “[ታጣቂዎች] ጥያቄያቸውን በሰላማዊ መንገድ በውይይትና በድርድር” እንዲያቀርቡ ጠይቋል።
መግለጫው “መንግሥትም ሆደ ሰፊ በመሆን እነዚህ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር በመወያየት እና በመደራደር ለሕዝባችን ሰላም ሲባል በይቅርታ እና በክብር እንዲቀበላቸው ጥሪያችንን እናቀርባለን” ብሏል።
አንድ ዓመት ሊሞላው በተቃረበው የአማራ ክልል አለመረጋጋት በሰላም መፍትሄ እንዲያገኝ የፌደራሉ መንግሥትም ሆነ የክልሉ አስተዳደር ፍላጎት እንዳላቸው በተደጋጋሚ ቢገልጹም፣ እስካሁን በይፋ የሚታወቅ እንቅስቃሴ የለም።