የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

26 ሰኔ 2024, 12:09 EAT

የኬንያውያን በአመጽ የተሞላ የተቃውሞ ሰልፍ ዋና ከተማዋን ናይሮቢን አናውጧታል። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች አዲስ የጸደቀውን የፋይናንስ ሕግ ለመቃወም አደባባይ ከወጡ በኋላ ከ10 ያላነሱ መገደላቸው ተዘግቧል።

ከመነሻው ሰላማዊ የነበረው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ ከሟቾች በተጨማሪ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች መቁሰል ምክንያት ሆኗል። ንብረት ወድሟል፤ ዘረፋም ተፈጽሟል።

ኬንያውያን ወጣቶች የአገሪቱ ፓርላማ ያጸደቀው የፋይናንስ ሕግ ኑሮ ያስወድድብናል በማለት ሲቃወሙት ቆይተዋል። የአገሪቱ መንግሥት በበኩሉ አገሪቱ ያለባትን ዕዳ ለመክፈል እንዲሁም ለዜጎች የሥራ ዕድልን ለመፍጠር የግብር ሕጉ የሚያዘው ገቢ ያስፈልገኛል ይላል።

ትልቅ የተቃውሞ ሰልፍ ከተደረገባቸው የኬንያ ከተሞች መካከል ናይሮቢ፣ ኤልዶሬት፣ ሞምባሳ፣ ኪሱሙ እና ናኩሩ ተጠቃሽ ሲሆኑ፣ በሌሎችም አካባቢዎችም ነዋሪዎች አደባባይ ወጥተወል።

ፖሊስ ወስዶታል በተባለው ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ ከ13 ያላነሱ ሰዎች መገደላቸውን ዘ ስታንዳርድ የተባለ የአገሪቱ ጋዜጣ ዘግቧል።

ጋዜጣው 10 ሰዎች በመዲናዋ ናይሮቢ እንዲሁም ናኩሩ እና ኪታሌ በተባሉ ግዛቶች ተጨማሪ ሦስት ሰዎች በፀጥታ ላይሎች መገደላቸውን ገልጿል።

ተቃውሞውን ተከትሎ ከተገደሉት በተጨማሪ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተለያዩ ጉዳት ደርሶባቸዋል። የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ከ145 ያላሱ ሰዎች የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታሎች ተወስደዋል።

ከተቃውሞው እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ሕይወታቸውን ካጡ እና የአካል ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች አብዛኛዎቹ በጥይት የተመቱት ከአገሪቱ ፓርላማ ፊት ለፊት ነው።

ሰልፈኞች ወደ ፓርላማው አዳራሽ ለመግባት ሲሞክሩ
የምስሉ መግለጫ,ሰልፈኞች የፓርላማውን አጥር ጥሰው ከገቡ በኋላ ወደ ምክር ቤቱ አዳራሽ ለመግባት ሲሞክሩ

የፕሬዝዳንቱ ማስጠንቀቂያ

ተቃዋሚዎቹ ሰልፈኞች ቀድመው ባቀዱት መሠረት ማክሰኞ ሰኔ 18/2016 ዓ.ም. በተካሄደው ተቃውሞ ዋና ከተማ ናይሮቢ ውስጥ ትምህርት ቤቶች እና አብዛኞቹ የሥራ ቦታዎች ተዘግተው የነበረ ሲሆን ከተማዋ ጭር ብላ ነበር የዋለችው።

በተለይ የአገሪቱ ፓርላማ በሚገኝበት የከተማዋ ማዕከላዊ ክፍል ውስጥ በብዛት የተሰባሰቡት ተቃዋሚዎች ዋነኛ ግባቸው የነበረው ፓርላማውን መውረር እና በረቂቅ የፋይናንስ ሕጉ ላይ ድምጽ እንዳይሰጥ ማድረግ ነበር።

ፖሊስ ከማለዳ ጀምሮ ወደ ፓርላማው የሚወስዱ መንገዶችን ዘግቶ አስከ እኩለ ቀን ድረስ ተቃዋሚዎችን ከስፍራው ማራቅ የቻለ ቢሆንም፣ የሕዝብ እንደራሴዎቹ ከአንድ መቶ በላይ የተቃውሞ ድምጽ የተሰጠበትን ረቂቅ ካጸደቁ በኋላ የተቃዋሚዎቹ ቁጣ ተባብሶ ነበር።

ከፀጥታ ኃይሎች አቅም በላይ የሆኑት ተቃዋሚዎችም የፓርላማውን አጥር ጥሰው በመግባት የመሰብሰቢያ አዳራሹ ድረስ ዘልቀው መግባት ችለዋል። የምክር ቤት አባላቱም ለመሸሽ ተገደው ነበር።

ሁኔታው ከተባባሰ በኋላ የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ባወጡት መግለጫ የፀጥታ ኃይሎች የተፈጠረውን ቀውስ በበቂ ሁኔታ መቆጣጠር ባለመቻላቸው ጦር ሠራዊቱ እንደሚሰማራ አስታወቀዋል።

ቀኑን ሙሉ ከዘለው ተቃውሞ በኋላ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ምሽት 3 ሰዓት ላይ በቀጥታ በቴሌቪዥን በተላለፈ ንግግራቸው “የተደራጁ ሕገ-ወጥ ቡድኖች በሕግ አክባሪ ኬንያውያን ተከልለው የአገሪቱን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አደጋ ላይ ጥለዋል” ብለዋል።

“ኬንያ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ በዴሞክራሲ ሥርዓቷ፣ በሕግ የበላይነት እና ሕገ-መንግሥታዊ ተቋማቷ ላይ ጥቃት ደርሷል” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ የዚህ ዓይነቱ ክስተት “በብሔራዊ ደኅንነታችን ላይ ለሚደርሱ ከባድ አደጋዎች ምላሽ የምንሰጥበትን ሁኔታ የቀየረ ነው” ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ሩቶ “የትኛውንም ዋጋ ቢያስከፍል” መሰል አመጽ ዳግም እንዳይፈጠር የተቻለንን ፀጥታ አስከባሪ አሰማርተናል ብለዋል።

አዲሱ የግብር ሕግ በአገሪቱ ምክር ቤት ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ተግባራዊ ለመሆን የአገሪቱ ፕሬዝዳንት በሁለት ሳምንት ውስጥ ተቀብለውት በፊርማቸው ማጽደቅ ይኖርባቸዋል።

በተቃዋሚዎች በእሳት የተያያዘው የፓርላማው ክፍል
የምስሉ መግለጫ,በተቃዋሚዎች በእሳት የተያያዘው የፓርላማው ክፍል

ቀጣይ ተቃውሞ፣ ሚዲያዎች እና ኢንተርኔት

ምንም እንኳ የኬንያ መንግሥት የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ለመቆጣጠር የአገሪቱን ጦር እና ፖሊስ በሙሉ አቅሙ ቢያሰማራም ኬንያውያን ወጣቶች በተቃውሟቸው እንደሚቀጥሉ እየገለጹ ይገኛሉ።

ኬንያውያን ነገ ሐሙስ ሰኔ 20/2016 ዓ.ም. ሌላ የተቃውሞ ሰልፍ ከማድረግ ወደኋላ እንደማይሉ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሐሳባቸውን እየገለጹ ነው።

የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ ኃላፊነት ወስዶ ተቃዋሚዎችን የሚመራ ቡድን በሌለበት ሰልፍ ኢንተርኔት ትልቅ ሚና እየተጫወት ይገኛል።

ባለፉት ቀናት አዲሱ የቀረጥ ሕግ ኑሮ ያስወድድብናል ሲሉ የቆዩት ኬንያውያን ሐሳባቸውን ሲያሸራሽሩ የቆዩት እና ለተቃውሞ የተሰባሰቡት ትዊተር ላይ በሚያደርጉት ውይይት ነው።

ተቃዋሚዎቹ መልዕክት የሚለዋወጡት እና ውይይት የሚያደርጉት በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ላይ ሲሆን፣ ማክሰኞ ዕለት ተቃውሞው መክበዱን ተከትሎ የኢንተርኔት ግንኙነት መቋረጥ እና ፍጥነት ማጣት አጋጥሞ ነበር።

በመላው ዓለም የኢንተርኔት ግንኙነትን የሚቆጣጠረው ኔትብሎክስ ማክሰኞ ዕለት በኬንያ የኢንተርኔት ግንኙነት መቆራረጥ እንዳጋጠመ ገልጿል። በተለይ ተቃዋሚዎች መረጃ ለመለዋወጥ የሚጠቀሙበት ኤክስ (ትዊተር) ከሰዓት በኋላ የአገልግሎት መቆራረጥ ገጥሞታል።

ከማኅበራዊ ሚዲያዎች በተጨማሪ የኬንያ መገናኛ ብዙኃን ተቃውሞውን በቀጥታ በማሰራጨት እና የተቃዋሚዎችን ድምጽ በማስተጋባት መረጃ በስፋት ሲያሰራጩ ቆይተዋል።

የተባባሰውን ተቃውሞ ተከትሎ የግል የቴሌቪዥን ጣቢያ የሆነው ኬቲኤን በሚያቀርበው ዘገባ ምክንያት ከመንግሥት የመዝጋት ማስፈራሪያ እንደደረሰበት አስታውቋል።

ለ24 ሰዓታት የሚሰራጨው የቴሌቪዥን ጣቢያ ግን፣ ምንም እንኳን የመዘጋት ዛቻ ቢገጥመውም ዘገባዎችን የማቅረብ የጋዜጠኝነት ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ገልጿል።

ቴሌቪዥን ጣቢያው የትናንት የተቃውሞ ዘገባው በዩቲዩብ ብቻ ከ200 ሺህ በላይ ተመልካቾች በቀጥታ ሲመለከቱት ነበር።

ተቃዋሚዎች በጎዳና ላይ
የምስሉ መግለጫ,ተቃዋሚዎች በጎዳና ላይ

ዒላማ የተደረጉ የምክር ቤት አባላት

የትናንቱን የተቃውሞ ስልፍ ተከትሎ በሰው ላይ ከደረሰው ጉዳይ በተጨማሪ አደባባይ የወጡ ተቃዋሚዎች የአገሪቱን ፓርላማ በወረሩበት ወቅት የተወሰነውን የፓርላማ ሕንጻም በእሳት አያይዘዋል።

የፖሊስ እና የምክር ቤት አባላት ተሸከርካሪዎች ወድመዋል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች ፖሊስን ጥሰው ወደ ፓርላማው አዳራሽ ከመግባታቸው በፊት ረፋድ ላይ በአዋዛጋቢው ሕግ ላይ ድምጻቸውን ሲሰጡ የነበሩ የምክር ቤት አባላት ሕይወታቸውን ለማዳን እግሬ አውጪኝ ሲሉ ተይተዋል።

የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን የምክር ቤቱ አባላት በፓርላማው ምድር ቤት ከተሸሸጉ በኋላ ውስጥ ለውስጥ በተገነባው መተላለፊያ ዋሻ ማምለጣቸውን ዘግበዋል።

ከዚህ በተጨማሪም አወዛጋቢው ሕግ እንዲጸድቅ ድምጻቸውን የሰጡ የምክር ቤት አባላት መኖሪያ ቤት እና ንብረት በተቃዋሚዎች ዒላማ ተደርገዋል።

ኪማኒ ኩሪያ የተባሉ የምክር ቤት አባል በናኩሩ ግዛት የሚገኘው ቅንጡ መኖሪያ ቤታቸው በመቶዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ተዘርፏል። በመቀጠልም ድምጽ የሰጧቸው ሰዎች ቅንጡ የፖለቲከኛውን ቤት በእሳት አያይዘዋል።

ዋይናና ጆሮጌ የተባሉ የምክር ቤት አባል የገበያ አዳራሽ እንዲሁ ዒላማ ተደርጎ ተዘርፏል። ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የወጡ ምሥሎች ተቃዋሚዎች ከሱፐር ማርኬቱ ዕቃ ሲዘርፉ እና ፖሊስ ተቀዋሚዎችን ለመበተን ጥይት ሲተኩስ አሳይተዋል።

በኤልዶሬት ከተማ እንዲሁ ባለቤትነቱ የምክር ቤት አባል ነው የተባለ የምሽት መዝናኛ ስፍራ በተቃዋሚዎች ተዘርፏል።

ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ መንግሥታቸው ሰላማዊ ተቃውሞን እንደሚታገስ ገልጸው፤ ነገር ግን በወታቶቹ መካከል ሰርገዋል ያለወቸውን ወሮበሎች እንደሚቀጡ ዝተዋል።

አክለውም የአገሪቱ ኃይሎች የሕዝቡን እና የመንግሥትን ማንኛውንም ንብረቶች ከዘረፋ እና ከውድመት ለመከላከል በእጁ ያለውን ሁሉንም ነገር እንደሚጠቀም አስታውቀዋል።

ተቃዋሚዎች በምክር ቤቱ
የምስሉ መግለጫ,ተቃዋሚዎች በምክር ቤቱ