
ከ 5 ሰአት በፊት
የሶሪያው የእርስ በርስ ጦርነት በርካቶችን ገድሏል።
ከተሞችን አውድሟል።
የሶሪያውያንን ሕይወት አመሳቅሏል።
በርካቶች ሕይወታቸውን ለማትረፍ ማቄን ጨርቄን ሳይሉ ተሰደዋል።
ጦርነቱ ሲነሳ ኻሊል ገና የስድስት ዓመት ልጅ ነበር።
በምዕራባዊቷ ሶሪያ ሆምስ ውስጥ የታክሲ ሹፌር ከሆኑት ከአባቱ፣ ከእናቱ እና ከሁለት ታናናሽ እህቶቹ ጋር ነበር የሚኖረው።
የሶሪያ ሦስተኛዋ ትልቋ ከተማ የሆነችው ሆምስ ከደም አፋሳሹ ጦርነት በፊት 1.5 ሚሊዮን ሕዝብ ይኖርባት ነበር። በአውሮፓውያኑ 2011 በፕሬዚዳንት ባሻር አል አሳድ ላይ የተነሳው ሕዝባዊ አመጽም ማዕከል ከነበሩት አንዷ ናት።
“እንኖርባት የነበረችው መንደር በሁለት ተራሮች መካከል ትገኛለች። በየምሸቱም በግጭቶች ትናወጥ ነበር” ሲል ኻሊል ያስታውሳል።
“ወታደሮቹ እና አማጺያኑ እርስ በርስ ሲታኮሱም የጦር መሳሪያዎቹ የሚተፉት እሳት በጣም ያስፈራኝ ነበር” ይላል።
ታዳጊው ይኖርባት የነበረችው የሆምስ ከተማ በአማጺያን ቁጥጥር ስር የነበረች ሲሆን፣ በአውሮፓውያኑ 2015 በመንግሥት እጅ ገባች።
ይህንንም ተከትሎ መንግሥት ማንኛውንም የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ወንጀል በማድረግ “በፀረ ሽብርተኝነት ሕግ” በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አሰረ። በቁጥጥር ስር ከዋሉት ውስጥም የካህሊል አባት ኢብራሂም አንዱ ነበር።
ከእስር ከተፈታም በኋላ የአገሪቱ ሁኔታ ያላስተማመናቸው የካህሊል ቤተሰቦች ለስደት ተዳረጉ።
- “የምወልዳትን ልጅ ላለማየት ፈረምኩ” ኢትዮጵያዊቷ ስደተኛ በጣልያን20 ሰኔ 2024
- አዲሱ የጥምር መንግሥት በደቡብ አፍሪካ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ምን ይዞ ይመጣ ይሆን?8 ሰኔ 2024
- ‘ጎልደን ቪዛ’ ምንድነው? የትኞቹ አገራትስ ይሰጣሉ? ለምንስ በጣም አነጋጋሪ ሆነ?3 ሰኔ 2024

የመጀመሪያዋ መዳረሻ አገር ሊባኖስ
ደም አፋሳሹ የሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ 12 ሚሊዮን ሰዎች ተፈናቅለዋል።
ከእነዚህ ውስጥ ከስድስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተበትዋል፤1.5 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ በጎረቤት አገር ሊባኖስ ይኖራሉ።
5.3 ሚሊዮን ገደማ ሕዝብ ያላት ሊባኖስ በዓለማችን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞችን ከሚያስተናግዱ አገሮች አንዷ ናት።
ለኻሊል ቤተሰብም ሊባኖስ የመጀመሪያዋ መዳረሻ ነበረች። ለአንድ ዓመት ያህልም ከሶሪያዊ የቤተሰቡ ጓደኛ ጋር ቆዩ።
ነገር ግን በሊባኖስ ላይ የወደፊት ተስፋን ባለማየታቸው ለቀው ለመውጣት ወሰኑ።
ከዚያም በአውሮፕላን ተሳፍረው በሕጋዊ መንገድ ወደ ቱርክ አቀኑ።
የሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ ቱርክ ስደተኞችን የመቀበል ፖሊሲዋን ክፍት በማድረግ 3.6 ሚሊዮን ስደተኞችን መዝግባ እያስተናገደች ትገኛለች።
በዓለም ላይ ከፍተኛ ስደተኞችን በመቀበልም በአንደኝነት ተቀምጣለች።
ኻሊል እና ቤተሰቡም ከ500 ሺህ በላይ ሶሪያውያን ስደተኞችን በተቀበለችው በመዲናዋ ኢስታንቡል መኖር ጀመሩ።
ለአራት ዓመታት ያህልም በኢስታንቡል ከኖሩ በኋላ በቱርካውያን እና በስደተኞች መካከል ቅራኔዎች እያደጉ በመምጣታቸው ከሕብረተሰቡ ጋር ለመቀላቀል አዳጋች ሆነባቸው።
“ቱርክ እያለሁ ህጻናት ወደ እኔ ይመጡና ‘ለምን ወደ ሶሪያ አትመለስም’ ይሉኝ ነበር። ማልቀሴ ምንም እንደማይለውጥ እና ኑሮዬን መቀጠል እንዳለብኝ ተረዳሁ” ይላል።
በአውሮፓውያኑ 2019 ላይ ቱርክ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሶሪያውያንን በግዳጅ ወደ አገራቸው እየመለሰች እንደሆነ ዘገባዎች መውጣት ጀመሩ። የቱርክ መንግሥት በወቅቱ ይህንን አስተባብሏል።

ጉዞ ወደ አውሮፓ
የኻሊል ቤተሰብም ይህንን በመፍራት ወደ ግሪክ ለመድረስ ወደ ደቡባ ምዕራብ የባህር ዳርቻ ከተማ ወደ ሆነችው ቦድሩም ተጓዙ። ግሪክ ለመግባት ሦስት ጊዜ ሞክረው ሳይሳካላቸው ቀረ።
በአራተኛው ኻሊል እና ቤተሰቡን ጨምሮ ወደ 50 የሚጠጉ ሰዎችን ያሳፈረች ጀልባ በግሪኳ ደሴት ኮስ ደረሰች።
“ህልም መስሎን ነበር። በጣም ተደሰትን አምላካችንን አመሰገንን። እዚህም የወደፊት ሕይወታችንን መገንባት እንችላለን ብለን አሰብን” ይላል።
ነገር ግን ህልማቸውን የሚያጨልም ነገር ተከሰተ። በአውሮፓውያኑ 2020 ግሪክ ስደተኞችን ወደ ቱርክ እያባረረች እንደሆነ ተዘገበ።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በወቅቱም ግሪክ ጥገኝነት ጠያቂዎችን እየበደለች ነው ሲሉ የተቿ ሲሆን፣ የግሪክ ባለሥልጣናት በበኩላቸው ይሄንን አስተባብለዋል።
የኻሊል አባት ኢብራሂም የእነሱ ተራ እንዳይደርስ አስፈራቸው። በዚህ ወቅት ነው ኻሊል ከቤተሰቡ ተነጥሎ ብቻውን ወደ ሌሎች የአውሮፓ አገራት ለመሄድ ሃሳብ ያቀረበው።

የታዳጊው የብቻ ጉዞ
“በመጀመሪያ አባቴ አይሆንም ብሎ ነበር። ነገር ግን ትንሽ ካሰላሰለ በኋላ እንድሄድ ፈቀደልኝ” ይላል።
የ13 ዓመቱ ኻሊል ቤተሰቦቹን ትቶ ከሌሎች ስደተኞች ጋር ወደ አልባኒያ አቀና።
ጉዟቸውንም በመቀጠል ከ165 ኪሎ ሜትር በላይ በእግራቸው ተጓዙ።
ተራሮችን እና ወንዞችን ሲያቆራርጡም ሕይወታቸውን የምታቆይ ትንሽ ምግብ ይዘው ነው።
ስደተኞቹ ቢያንስ የውሃ እጥረት አልነበራቸውም። በውጣ ውረድ የተሞላ ጉዟቸውንም በሞባይል ስልኮቻቸው እየቀረጹ ነበር።
ከሁለት ሳምንታት የእግር ጉዞ በኋላ የኮሶቮ ዋና ከተማ ፕሪስቲና ደረሱ። ብዙም ሳይቆዩ ወደ ሰርቢያ አቀኑ።
ኻሊል እና ሌሎች ስደተኞችም ወደ ሰርቢያ ዋና ከተማ ቤልግሬድ የደረሱት በኅዳር ወር 2013 ነበር። ቤልግሬድ ከደረሰም በኋላ ኻሊል “ጉዞዬን ጨርሻለሁ። ደክሞኛል” የሚል መልዕክት በስልኩ ቀርጾ ነበር።

ወደተሻሉ የአውሮፓ አገራት ለመድረስ የተደረገ ጥረት
ሆኖም ግን ሰርቢያ ከደረሰ በኋላ የጉዞው መጨረሻ አልነበረም። ወደ ኦስትሪያ ወይም ኔዘርላንድ ለመድረስ ነበር ዋነኛ ፍላጎቱ።
የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ድንበሮች ለማቋረጥ አታካች እና ተደጋጋሚ ሙከራዎች አደረገ። ከእነዚህም ውስጥ 11 ጊዜ ወደ ሃንጋሪ፣ ሦስት ጊዜ ወደ ክሮሺያ እንዲሁም አንድ ጊዜ ወደ ሮማኒያ።
ነገር ግን ሁሉም ሳይሳኩ ቀሩ። ለአራት ወራት ያህል አጥንት በሚሰብር ብርድ ውስጥ ያደረጋቸው ረዥም የእግር ጉዞዎች የጤና እክል አስከተሉበት። በመጨረሻም ተስፋ ቆርጦ ቤልግሬድ ለመኖር ወሰነ።
ከአውሮፓውያኑ 2015 ጀምሮ ከተለያዩ አገራት የመጡ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ስደተኞች የባልካን መስመር ተብሎ በሚጠራው መሸጋገሪያ ወደ አውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ለመድረስ ሙከራ አድርገዋል።
የአውሮፓ የስደተኞች እና የግዞተኞች ምክር ቤት በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በሕገወጦች ወይም በፀጥታ እና በድንበር ተቆጣጣሪዎች ከፍተኛ ጥቃት እና እንግልት እንደሚደርስባቸው እና በኢሰብዓዊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚኖሩም ይፋ አድርጓል።
በአሁኑ ወቅት የ17 ዓመት ወጣት የሆነው ኻሊል “ቤልግሬድ የእኔ ከተማ እንደሆነች አይሰማኝም፤ ነገር ግን እዚህ ደስተኛ ነኝ” ሲል ለቢቢሲ ሰርቢያ ተናግሯል።
ላለለፉት ሦስት ዓመታት የሰርቢያ መዲና የኻሊል አዲስ ቤት ሆናለች።
ትምህርት የተማረባት፣ እንግሊዝኛ እና የሰርቢያን ቋንቋ አጥንቷል እንዲሁም በርካታ ጓደኞችን ማፍራት ችሏል።
ጄሱት ሪፊውጂ ሰርቪስ የተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ የበጎ አድራጎት ድርጅት በሰጠው ቤትም ሥዕሎችን ይስላል።
“በግሪክ፣ በአልባኒያ፣ በኮሶቮ የተከሰቱት ነገሮች አድክመውኛል። እዚህ ከመጣሁ በኋላ አረፍ ብያለሁ። መተኛት እችላለሁ እንዲሁም ትምህርት ቤት እሄዳለሁ። ሕይወት ጥሩ ሆናልኛለች” ብሏል።

ከቤተሰብ ጋር መገናኘት
ኻሊል ሰርቢያ በነበረበት ወቅት አባቱ እና እህቶቹ በግሪክ እየኖሩ ነበር።
እናቱ ግን ኔዘርላንድስ ደርሰው በስደተኝነት መመዝገብ ችለዋል።
በዘንድሮው ዓመት መስከረም ላይ ቤተሰቡ እንዲገናኙ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ ኻሊልም ወደ ኔዘርላንድስ አቅንቷል።
ለአራት ዓመታት ያህል ያላያቸውን ቤተሰቦቹንም አገኘ።
በአሁኑ ወቅት መላው የቤተሰቡ አባላት ኔዘርላንድስ ውስጥ ጥገኝነት ተሰጥቷቸዋል። በሚቀጥለው ዓመት ኮሌጅ የሚገባው ኻሊል ኮምፒውተር ፕሮግራሚንግ ለማጥናት አቅዷል።
“አዲስ ጓደኞችን ማፍራት እና ከቤተሰቤ ጋር ሰላማዊ ኑሮ መኖር እንዲሁም ከጦርነት መራቅ እፈልጋለሁ” ሲልም ምኞቱን ገልጿል።
አክሎም “በሕይወቴ ውስጥ ያጋጠሙኝ ተሞክሮዎች በራሴ እንዳምን እንዲሁም የምፈልገውን ሁሉ ለማሳካት ጠንካራ እንድሆን አስተምረውኛል” ብሏል።