
ከ 4 ሰአት በፊት
የኦክላሆማ ትምህርት ቢሮ በግዛቱ ውስጥ ያሉ የሕዝብ ትምህርት ቤቶች መጽሐፍ ቅዱስን በትምህርት ስርዓታቸው በአስቸኳይ እንዲያካትቱ አዘዘ።
የግዛቱ የትምህርት የበላይ ተቆጣጣሪ የሆኑት ሪፐብሊካኑ ሪያን ዋልተርስ የተላከው መመሪያ “አፋጣኝ እና ጥብቅ ተፈጻሚነትን” የሚፈልግ አስገዳጅ ድንብ ነው ይላል።
መመሪያው ከ11-18 ዕድሜ ባላቸው በሁሉም የሕዝብ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ላይ ተፈጻሚ ይሆናል።
ይህ መመሪያ የወጣው የሉዊዚያና ገዥ በግዛቱ ውስጥ ባሉ በሁሉም የሕዝብ ትምህርት ቤቶች አስርቱን ትዕዛዛት ግድግዳ ላይ እንዲለጠፉ የሚያዝ ሕግ ከፈረሙ ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው።
ዋልተርስ ሐሙስ ዕለት በሰጡት መግለጫ መጽሐፍ ቅዱስ “ታሪካዊ እና ባህላዊ መሠረት” ነው ሲሉ ገልጸውታል።
“ያለ መጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ እውቀት የኦክላሆማ ተማሪዎች የአገራችንን መሠረት በትክክል መረዳት አይችሉም” በማለት በግዛቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መሰጠት ያለበትን ምክንያት ገልጸዋል።
የቀድሞ የሕዝብ ትምህርት ቤት የታሪክ መምህር ዋልተርስ፤ በ2022 “የነቃ ርዕዮተ ዓለምን” መዋጋት በሚል የምርጫ ዘመቻ ካደረጉ እና “አክራሪ ግራ ዘመሞችን” ከኦክላሆማ የትምህርት ሥርዓት ለማስወገድ ቃል ገብተው ተመርጠዋል።
ከ5ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ይተገበራል የተባለው መመሪያ ከሲቪል መብት ተሟጋች ድርጅቶች እንዲሁም ሃይማኖት እና መንግሥት መለያየት አለባቸው ከሚሉ ቡድኖች ትችት ገጥሞታል።
“የሕዝብ ትምህርት ቤቶች ሰንበት ትምህርት ቤቶች አይደሉም” ሲሉ መንግሥትን ከሃይማኖት መለያየት እንዳለበት የሚሠራ ተቋምን የሚመሩት ራቸል ሌዘር መናገራቸውን ኤፒ የዜና አገልግሎትን ዘግቧል።
- ኢትዮጵያ ወታደሮቿ ወደ ሶማሊያ ግዛት ጥሰው ገብተዋል መባላቸውን “መሠረተ ቢስ” ስትል አጣጣለች27 ሰኔ 2024
- አውሮፓ ለመድረስ 11 ዓመታት የፈጀው የሶሪያዊው ታዳጊ ጉዞከ 5 ሰአት በፊት
- በዶክተር ቴድሮስ የሚመራው የዓለም ጤና ድርጅት ዋንኛ ሥራው ምንድን ነው? ምንስ አሳካ?ከ 5 ሰአት በፊት
“ይህ የመማሪያ መጽሃፍ የክርስቲያን ብሔርተኝነት ነው። ዋልተርስ የመንግሥት ስልጣንን አላግባብ በመጠቀም ሃይማኖታዊ እምነቱን በሌሎች ላይ ለመጫን እየተጠቀመበት ነው። ይህ እኛ ባለንበት ሊሳካ አይገባም” ሲሉ አክለዋል።
በአሜሪካ የሃይማኖት ነፃነትን ለማስጠበቅ የሚጥረው ኢንተርፌይዝ አሊያንስ በበኩሉ የኦክላሆማ መመሪያን “ግልጽ በሆነ መልኩ ሃይማኖትን መጫን ነው” ሲል ገልጾታል።
ኢንተርፌይዝ አሊያንስ አክሎም “እውነተኛ የእምነት ነፃነት ማለት የትኛውም የሃይማኖት ቡድን አመለካከቱን በሁሉም አሜሪካውያን ላይ እንዳይጭን መከላከል ነው” ብሏል።
ባለፈው ሳምንት በሉዊዚያና እስከ ዩኒቨርሲቲ ባሉ በሁሉም የመማሪያ ክፍሎች ውስጥ አስርቱን ትዕዛዛት እንዲለጥፉ ከታዘዘ በኋላ የግዛቱ ነዋሪ የሆኑ ዘጠኝ ቤተሰቦች የሉዊዚያና ግዛትን ከሰዋል። አንዳንዶች እንደጠበቁትም ክሱ ረዘም ላለ ጊዜ የሚቀጥል የሕግ ክርክር ይሆናል።
በሲቪል መብት ተሟጋች ድርጅቶች የተደገፈው ክስ እንደሚለው ከሆነ እንዲህ ዓይነቱ ሕግ የሃይማኖት ነፃነትን የሚያረጋግጠውን የዩናይትድ ስቴትስ ሕገ-መንግሥት የሚጥስ ነው።
አስርቱ ትዕዛዛት መለጠፋቸው ተማሪዎች መንግሥት የሚወደውን ሃይማኖት እንዲቀበሉ “ግፊት” ይፈጥራል ሲሉም ተከራክረዋል።
ፍርድ ቤቶች፣ ፖሊስ ጣቢያዎች እና ትምህርት ቤቶች ጨምሮ በሕዝብ ሕንፃዎች ውስጥ አሥርቱ ትዕዛዛት መለጠፋቸው ከዚህ በፊት የሕግ ክርክሮችን ፈጥሮ ነበር።
እአአ በ1980፣ በስቶን እና ግራሃም መካከል በነበረው ክስ የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስርቱ ትዕዛዛት በአንደኛ ደረጃ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲታዩ የሚፈልገውን የኬንታኪ ሕግ ውድቅ አድርጎታል። ይህ ውሳኔ የሉዊዚያናን ሕግን በሚቃወሙ ቡድኖች ተጠቅሷል።